Monday, October 29, 2012

አምስተኛው ብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በመላው አገሪቱ በደማቅ ስነ ስርአት ተከበረ

(አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2005)--አምስተኛው ብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በመላው አገሪቱ በደማቅ ስነ ስርአት ተከበረ። በአሉ በተለይ እዚህ በአዲስ አበባ ስታዲዬም የተከበረው በመከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ በኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር፣ በኢትዮጵያ ስካውት ማህበር፣ በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ጓድ ጣእመ ዜማ በመታጀብ በሰልፍ ትርኢት ጭምር ነበር። 

በበአሉ ላይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተቀማጭነታችውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንት፣ ከልዩ ልዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተር በስታዲዮሙ አናት ላይ በማንጃበብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙርንና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ የያዘ ወረቀትም ለበዓሉ ታዳሚዎች በትኗል።

 በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ሰዓት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስት ደመቀ መኮንን አማካኝነት በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በመታጀብ ሰንደቅ አላማ የመስቀል ስነ ስርዓትም ተከናውኗል፡፡ የዘንድሮው አምስተኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የተከበረው "ሰንደቅ አላማችንን ከፍ አድርገን በታላቁ መሪያችን የተጀመረውን ህዳሴ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ነው። 

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ሰንደቅ ዓላማ ያለው አገራዊ ትርጉም ከፍተኛ ነው።

 በየዓመቱ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሕዝቦች እኩልነትና ፈቃደኝነት የተመሰረትች አዲሲቷ ኢትዮጵያ የስኬትና የህዳሴ ጉዞ ማሳያ ምልክት እንደሆነም ገልጸዋል። ሰንደቅ አላማ ከአገር ምልክትነት የላቀ ፋይዳና ትርጉም ያለውና የአገርንና የህዝብ ፍላጎት ለማሳካትና ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ ዋነኛ መሳሪያ እንደሆነም ተናግረዋል።

ነፃነቷንና ልዑላዊነቷን ጠብቃ ለዘመናት የቆየችው አገራችን በድህነትና በኋላቀርነት ዝቅ ብላ እንዳትታይ አዲሱ ትውልድ ጠንካራ የልማት ጀግና መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል። በአገሪቱ የተጀመረውን ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማስቀጠል መላው ህዝብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲገፋበትም ጠይቀዋል። 

 አቶ ደመቀ የህዳሴውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም በአንድ ልብ፣ በእልህና በወኔ ለአገሪቱ የሚጠቅመውን በባለቤትነትና በኃላፊነት ስሜት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። መንግስት በከተማ የህብረተሰቡን ኑሮ ለመለወጥ የስራ አጥነት ችግሮችን በማስወገድ ከተሞችን ለስራና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው በዓሉ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ጠንካራ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል። 

እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ርብርብ የሚቻለውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም አፈ ጉባዔው አሳስበዋል። 

 በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተገኔ ጌታነህ አማካኝነትም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሪቱ ልማት መፋጠን ከመንግሥት ጎን በመቆም ተግባራዊ ለማድረግ በሰንደቅ ዓላማ ስም ቃለ መሓላ መፈጸማቸውን ኢዜአ ዘግቧል። 
Source: ENA

No comments:

Post a Comment