(እሁድ, 10 ሰኔ 2012, አዲስ አበባ)--የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአዲስ አበባ ስታድየም ከማዕከላዊ አፍሪካ አቻው ጋ ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ 0 አሸነፈ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በውጤቱ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል፡፡ በአዲስ አበባ ስታድየም እሁድ ሰኔ 3/2004 በተደረገው ጨዋታ ሳላህዲን ሰዒድ በ36ኛ እና 88ኛ ደቂቃዎች ለኢትዮጵያ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥሯል፡፡
ሰላህዲን በተለይም ሁለተኛውን ግብ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በመቆጣጠር ከተከላካይ ጋ ተጋፍቶ ብቃቱን ባስመሰከረ መልኩ ነበር ያገባው ፡፡ ሰላህዲን ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር አቻ የወጣችበትን ግብ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠሩም ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ
ከደቡብ አፍሪካ ጋ ባለፈው ሳምንት ባደረገችው ጨዋታ ከሜዳዋ ውጭ ነጥብ ተጋርታ በመመለሷ የተነቃቃው የስፖርት
ቤተሰብ በዕለቱ ስታድየሙን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሙላት በጋለ ሀገራዊ ስሜት ድጋፉን ሲገልፅ አምሽቷል፡፡
በተለይም በጨዋታው ፍፃሜ አካባቢ የተቆጠረችው ግብ የተመልካቹን ስሜት እጅግ በማነቃቃቷ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከስታድየም በወጡ ደጋፊዎች የድጋፍ ጭፈራ ደምቀው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ባለችበት ምድብ ሰኔ 2/2004 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና ጋር ባደረጉት ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በዚህም
ምክንያት ኢትዮጵያ ምድቡን በ4 ነጥብ መምራት ችላለች፡፡ ማዕከላዊ አፍሪካ በ3 ነጥብ ሁለተኛ ስትሆን ደቡብ
አፍሪካ በ2 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ ቦትስዋና ደግሞ በ1 ነጥብ የመጨረሻ ደረጃውን ይዛለች፡፡
ውጤቱ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2014 ብራዚል ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ያላት እድል ላይ ተስፋ ፈንጥቋል፡፡
Source: ERTA (ሪፖርተር ሙሉጌታ ኩሳ)
No comments:
Post a Comment