Monday, April 30, 2012

ዳያስፖራው ስለራሱ እንጂ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ያልጠየቀበት መድረክ

(Sunday, 29 April 2012, Addis Ababa)--ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየትና ለችግሮች በጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ በአንድ መድረክ የተቀመጡት ሚያዝያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡

በመድረኩ ዳያስፖራው ያሉበትን ብሶቶች ሲገልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይኼ ያስፈልገዋል እያለ አልነበረም፡፡ ይልቁንም እኔ ወይም ዳያስፖራው የሚሉ በግለኝነት ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችና ብሶቶች ጎልተው ተደምጠዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተመራው መድረክ ከ300 በላይ ታዳሚዎች የተገኙ ሲሆን ለባለሥልጣናቱ ጥያቄዎችን ማቅረብ የቻሉት ደግሞ 30 ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡ ጠያቂዎቹ የአዳራሹን ታዳሚ ሁሉ ይወክላሉ ባይባልም ለሚያነሷቸው ብሶቶችና ቅሬታዎች አንዳንዴም ለሚሰጧቸው አስተያየቶች ከመድረኩ የደመቀ ጭብጨባዎች ሲቸራቸው ነበር፡፡

ከካናዳ ከመጡ አምስት ዓመታትን እንዳስቆጠሩ የተናገሩት ግለሰብ በአገሪቷ የተንሠራፋውን ሙስና፣ ቢሮክራሲና ብልሹ አሠራር ጠቅሰው ‹‹የዳያስፖራ ኮምፕሌን [ቅሬታ ሰሚ] ኮሚቴ ይቋቋምልን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ታዳሚውም በጭብጨባ ነበር ድጋፉን የገለጸው፡፡

የብልሹ አሠራርና የቢሮክራሲ ሰለባው ዳያስፖራው ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ወጥተው ለማያውቁት ብዙኀኑ ኢትዮጵያውያን ቢሆንም ኢትዮጵያውያን እየተጎዱ ነው፣ ለሙስና፣ ለብልሹ አሠራርና ለቢሮክራሲ ተጋልጠዋልና አብረን በጋራ ችግሩን እንፍታ የሚል ሐሳብ አልተሰነዘረም፡፡

ዳያስፖራው የኖረበት አገር ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር የተሻለና የውጭውን አገር የአሠራር ልምድ ያማከለ እውቀት ይዞ ይገባል ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም መድረኩ ላይ ጥያቄ ለማቅረብ ከቻሉት ታዳሚዎች ከአብዛኞቹ ችግር አለ የሚል እንጂ የመፍትሔ ሐሳብ ይዞ ብቅ ያለ የለም፡፡

አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅም ሆነ አፍሪካ ሙስናን፣ ብልሹ አሠራርን፣ ቢሮክራሲንና የፍትሕ መጓደልን ለመቅረፍ የተከተሏቸው መልካም አሠራሮች አሉ፡፡ ጠንካራ ሙያዊ ማኅበራትን ማቋቋም፣ ጠንካራ የንግዱ ማኅበረሰብ ማኅበራትን ማቋቋም፣ ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራትን ማቋቋም፣ የፍትሕ አካሉን ሊቆጣጠርና ትክክል አይደለህም የሚል ጠንካራ ማኅበራትን ማቋቋም በየመንግሥት መሥርያ ቤቱና በንግድ ማኅበረሰቡ በኩል አሉ የተባሉ የሙስና የብልሹ አሰራር፣ የፍትሕ መጓደል ችግሮችን ለመታገልና ለመፍታት እንዲሁም የሕዝብን ድምፅ ለማሰማት የሚያስችሉ ቢሆንም ዳያስፖራው ይህንን ሲያነሣ አልተደመጠም፡፡ እንደ አጠቃላይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት የሚበጀውን አሰራር ሊቀይስ የሚችል በየሙያው የተደራጀ ኮሚቴ አቋቁመን አብረን እንሥራ ሲልም አልተደመጠም፡፡ በአብዛኛው ንግዱና ኢንቨስትመንቱ ላይ ያጋጠሙትን ችግሮች ገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ ከ30 ዓመታት በላይ በፈረንሳይና በሌሎች አገሮች መኖራቸውን የገለጹት እንስት፣ ‹‹የሰነፍ አገር የሰነፍ ሕዝብ ስለሆነ ወደኋላ ቀረን እንጂ መንግሥት የራሱን ጥረት እያደረገ ነው›› ሲሉ በጥቅል አገሬውን ወቅሰዋል፡፡ የወገናቸው ሁኔታ ስላስደነገጣቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ሳይሠሩ መቀመጣቸውንም ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች የሕዝብ አገልጋይ ቢሆኑም እንደሚያመናጭቋቸውና እንደማያስተናግዷቸው የግብረገብ ችግር እንዳለና ‹‹አንቱ›› እንደማይሏቸው በብስጭት ሲናገሩ የመድረኩ ተሳታፊዎች አጉረምርመውባቸዋል፡፡ እሳቸው ግን በመቀጠል የግብረ ገብ ትምህርት ይሰጥ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የግብረ ገብ ትምህርት መሰጠቱ ለአገር እንደአገር ለዜጋውም እንደ ዜጋ ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም እኚሁ አስተያየት ሰጭ የመጡበት የሰለጠነው አገር ምን አይነት አሠራርን ተከትሎ ሕዝቡን እንደሳቸው አባባል ‹‹ከስንፍና›› እንዳወጣ በየመሥርያ ቤቱ ምን አይነት የአሠራር ዘዴ ተከትሎ ለተጠቃሚው የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደሚሰጥ አልጠቆሙም፡፡ ይልቁንም ‹‹ቁጭ›› ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአሠራር ክፍተቶች ጎልተው ይታዩባቸዋል፣ ችግሮችንም ለረዥም ጊዜም መፍታት ያልቻሉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሉ ከተባለም ሌሎች አገሮች አስተዳደርን ጨምሮ በሌላ አካል እንደሚያሠሩ ሁሉ በኢትዮጵያም መንግሥት ብቻውን በየመሥርያ ቤቱ ሙስናውን ለመግታት፣ መልካም አስተዳደሩን፣ ሥነ ምግባሩን የደንበኛ አያያዙን ብቻውን ለመሥራት ከሚታገል ቁጥጥሩን ለሌሎች ድርጅቶች እንዲሰጥ ወይም አብሮ እንዲያከናውነው የሚል ሐሳብ አላቀረቡም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በእቅድ እየሠራ ቢሆንም ሕዝቡ ካሉበት የመጠጥ ውኃ፣ የመንገድ፣ የቤት፣ የጤና ተቋማት፣ የትምህርት ጥራት፣ የተደራራቢ ታክስ፣ የዋጋ ግሽበትና ሌሎችም ችግሮች ገና አልተቀረፉለትም፡፡ ይህ ደግሞ አገር ውስጥ ገብቶ ለሚሠራውም ሆነ በውጭው ለሚኖረው ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የተደበቀ አይደለም፡፡

ሆኖም በውይይቱ ላይ በውኃ ቴክኖሎጂው የተሰማራው በውሃ ዘርፍ፣ በትምህርት ላይ ያለው በትምህርቱ ዘርፍ፣ በጤና ላይ የሚሠራው በጤና ዘርፍ፣ በምሕንድስና ላይ ያለው በምሕንድስናው ዘርፍ… ብሎ በየዘርፉ ኮሚቴ አቋቁመን የተጀመሩ ልማቶች ላይ ተሳትፎ እናድርግ፣ በተቻለን አቅም አብረን እንሥራ፣ አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊም እንደሰለጠነው ዓለም የመልካም ኑሮ ተጠቃሚ ይሁን ብሎ ያነሣ አልነበረም፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊውና ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያ ገብቶ በትምህርት፣ በጤና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖኖሉጂ፣ በፊልምና በሌሎችም እየሠራ ቢሆንም ከሚሠሩት ሥራ ጎን ለጎን እንደየሙያ ዘርፋችን ተዋቅረን ለአገሪቷ አጠቃላይ ለውጥ የምናመጣበት መንገድ ይመቻችልን ብሎ የጠየቀም አልነበረም፡፡

የውይይቱ ታዳሚ ወይም ያልታደመውም ሆነ ውጭ ያለው የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሚያገኝበት አጋጣሚ ለምን የግል ጉዳዩን ብቻ ያነሣል የሚል ተቃውሞ ባይኖርም ለምን ስለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግርም አይጠይቅም? የሚለው ግን ለዳያስፖራው በጥያቄ የሚተው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከዳያስፖራው ጋር የተደረጉ የቀድሞ ውይይቶችም የሚያሳዩት ይህንኑ ‹‹የራሳቸውን ጉዳይ›› የማንሣት አካሔድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም አከባበር ወቅት ዳያስፖራው የቤት መሥሪያ መሬት፣ የመኪና ታክስ ማበረታቻ ያነሣቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ይህ በአሁኑ ስብሰባም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች አንዳንዱ ዳያስፖራ የሚወተውተው አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም በመኪና ላይ የተጣለው የግብር መጠንም ሆነ የመኖርያ ቤት እጦት የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ነው፡፡ በተለይ የመኖርያ ቤት ችግር ከዳያስፖራውም የበለጠ በአገር ቤት በዝቅተኛ ደመወዝ ተቀጥሮ ለሚሠራው የኅብረተሰብ ክፍል በቤት ኪራይ እንዲኖርና ደመወዙም ስለማይበቃው ከወር ወር በሞዴል (ብድር) እንዲጨናነቅ ያደረገ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ቤት ‹‹መከራየት ወይም መግዛት›› ቢያቅተው ወደመጣበት ሔዶ ከሁለቱ ባንዱ አማራጭ ይኖራል፡፡ አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህ እድል አለው ወይ? ብሎ መመልከት ከዳያስፖራው ይጠበቃል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የቤተሰቡ ጥገኛ ሆኖ ለመኖር የተገደደው በቤት እጦት ጭምር ነውና፡፡

መኪና ከታክስ ነፃ የማስገባት እድሉም ቢሆን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊም ሊጠይቀው የሚችለው መብቱ ነው፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራውም ሆነ አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ እኩል ይስተናገዳል፡፡ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን የማያስጠቅም የታክስ ማበረታቻ በመኪና ላይ አይኖርም፡፡

በውይይቱ ከስዊድን መጥተው በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያ ‹‹እውቀታችንን የምናስተላልፍበት ማዕከል ይቋቋምልን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጭ ደግሞ በየሜዳው የወደቁ ጧሪ የሌላቸው አዛውንቶች የማኅበረሰብ ዋስትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንዲመቻች ለምን በዕድገትና የልማት ዕቅዱ አልተካተተም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች ኢትዮጵያዊውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደ ዳያስፖራም ሊነሡ የሚገባቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በተለይ የእውቀት ሽግግር ማዕከሉ መቋቋም በኢትዮጵያ ክፍተት አሉባቸው የሚባሉ አሠራሮችን ለማጥበብ ያስችላልና፡፡

‹‹የባንክ ብድር ይመቻችልን በአሜሪካ የኖረ ሁሉ መኪናውን ሳይቀር በብድር የመግዛት ልምድ እንዳለው ይታወቃል›› በማለት ሐሳብ የሰጡም ነበሩ፡፡

ከባንክ ብድር ወስዶ መሥራቱ መስፈርቱ እስከተሟላ ድረስ አገር ውስጥ ላለው ኢትዮጵያዊም ቢሆን ክፍት ነው፡፡ ሆኖም ዳያስፖራው በነፃ መሬት ተሰጥቶት ብድርም ወስዶ መሥራት የሚፈልግ ከሆነ አስተዋጽኦው የሚጎላው ምኑ ላይ ነው? አገር ውስጥ ካለው ኢትዮጵያዊስ ለምን በተለየ ተጠቃሚ ይሆናል? ኢትዮጵያ የምትፈልገው የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚኖረው አስተዋጽዖስ እንዴት ይገለጻል?
Source: Reporter
 Home

No comments:

Post a Comment