Wednesday, April 18, 2012

ኢትዮጵያውንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል

(ሚያዝያ 9 ቀን 2004 (አዲስ አበባ)--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ- ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በሚቀጥለው ሳምንት ውይይት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሙሉጌታ ከሊል ዛሬ በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ ውይይቱ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ በአገራዊ ጉዳዮችና በልማት ተሳትፎአቸው በገጠማቸው ችግሮች ተወያይቶ መፍትሄ ለመፈለግ ነው፡፡ በውይይቱ ወደ አገር ውስጥ ከመጡ፣ በአገር ውስጥ በተለያየ የልማትና የሙያ ዘርፎች ከተሰማሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ጋር የዳያስፖራውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት በመንግሥት በመወሰድ ላይ ባሉት አበረታች እርምጃዎች ላይ መረጃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአገር ወስጥ በሥራ የተሰማሩና በበዓል ምክንያት ወደ አገር ውስጥ የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን የውይይቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ዳይሬክተሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በውይይቱ ለመካፈል የሚፈልጉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፍልውሃ በኩል ባለው በር በመገኘት መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ሚያዝያ 16/2004 በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በዳያስፖራ ፖሊሲ በተለያዩ ሀገሮች ካሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ውይይት በማካሄድ ግብዓት መሰብሰቡንና በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ሰባት ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡንም አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

ገንዘቡ የተሰባሰበው በሚኒስቴሩ አማካይነት በውጭ በሚገኙ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች አማካይነት መሆኑንም አስረድተዋል። በሚኒስቴሩ የዳይስፖራ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈይሰል ዓሊ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በየዓመቱ የኢትዮጵያን
ዳያስፖራ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በግንባር በመገናኘት የውይይት መድረኮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ በውይይቱ ላይ እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
Source: ENA

No comments:

Post a Comment