Monday, September 12, 2011

ኀብረተሰቡ የልማት ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው የሃይማኖት መሪዎች አስገነዘቡ

(ጳጉሜን 6 ቀን 2003 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--ኅብረተሰቡ በአገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ በአዲሱ ዓመት የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው የክርስትና ሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ። የሃይማኖት አባቶቹ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕከቶች አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት መላው ኀብረተሰብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ ያለመታከት ለስኬታማነቱ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል።  

አገሪቱ የጀመረችው የዕድገትና የልማት ዕቅድ የድህነት መቋጫና የብልፅግና ማረጋገጫ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

 በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየጎለበተ የመጣው የሕዝቦች የእርስ በርስ መከባበርና መተማመን፣ በአንድነትና በስምምነት ለአንዲት አገር ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት በጋራ መነሳሳት የማይናወጥ የብልጽግና መሠረት እንደሆነም አመልክተዋል። በሕዝቦች መካከል ያለው ኀብረት፣ ስምምነት፣ መከባበርና መተማመን የተጀመሩ የልማት ተግባራትን በማጠናከር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ጊዜው ሩቅ እንደማይሆን ፓትርያርክ ተናግረዋል።
 
በተሰናባቹ ዓመት የነበረውን አጠቃላይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግባራትን በመመርመር ያልተከናወኑ ሥራዎችን በአዲሱ ዓመት በእጥፍ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ለአገሪቱ ዕድገት ታላቅ ራዕይ የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግቡን እንዲመታ በጸሎትና በሥራ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በትምህርት፣በጤናና በሌሎች የልማት ዘርፎች የተገኙት ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ 

በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የምግብ እጥረት የደረሰባቸው ወገኖችን፣ ድሆችን፣ አቅመ ደካሞችንና ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት ሊደገፉ ይገባዋል ማለታቸውን ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዋቅስዩም ኢዶሳ እንደተናገሩት ለአገሪቱ ዕድገትና ብልጽግና በተዘረጉ የተለያዩ የልማት ዕቅዶች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልጋል። አዲሱ ዓመት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለልማት ዕቅዱ ስኬታማነት በንቃት የሚሳተፍበትና ለአገርና ለወገን መልካም ለመሥራት የሚነሳሳበት ዘመን እንደሆነም ገልጸዋል።


ታመው በአልጋ ላይ ያሉትን፣ የሚንከባከባቸው ወላጅ አጥተው በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕጻናትን፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በመርዳት በዓሉን ማክበር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። መንግሥት በአየር ንብረት መዛባት ለተከሰተው ድርቅ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
 
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኀብረት ዋና ፀሐፊ ቄስ አለሙ ሼጣ በበኩላቸው መንግሥት ልማትን ለማፋጠን፣ ድህነትን ታሪክ ለማድረግና አገሪቱን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር በሚያደርገው ጥረት ኀብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ገልጸዋል።
 
በተለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እውን ለማድረግ ኀብረተሰቡ ያበረከተውንና በማበርከት ላይ ላለው የዜግነትም ሆነ መንፈሳዊ አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ በሚደረገው የነፍስ አድን እንቅስቃሴም በመሳተፍ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment