Friday, January 28, 2011

የሸራተን አዲስ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ሆቴሉ ለአንድ ቁርስ ከሚያስከፍለው ያነሰ ነው አሉ

Reporter, በታምሩ ጽጌ, Wednesday, 26 January 201,
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጀመሩትን የኅብረት ስምምነት ድርድር ከዳር እንዲያደርሱ እያደራደራቸው የሚገኙት የሸራተን አዲስ ሆቴል ሠራተኞችና ማኔጅመንት በደመወዝ አከፋፈል ላይ አለመስማማታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡  

በሆቴሉ ለቁርስ የሚከፈለው የመጨረሻ ክፍያ 361 ብር ሆኖ ሳለ፣ በተለይ የመመገቢያና የተለያዩ የማብሰያ ዕቃዎችን ንጽህና የሚሠሩ ሠራተኞች የወር ደመወዝ 350 ብር መሆኑ አግባብ ባለመሆኑ እየተቃወሙ መሆኑን ምንጮቹ  አረጋግጠዋል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጽዳትና የላውንደሪ፣ አትክልተኞች፣ የጥበቃ ሠራተኞችና ሾፌሮች በሆቴሉ ውስጥ ቁርስ የሚመገብ ሰው 361 ብር እየከፈለ፤ የእነሱ ደመወዝ ከዚያ በታችና ከዚያም ብዙ ከፍ ያላለ ክፍያ መሆኑ የፈጠረባቸው ስሜት ጥሩ እንዳልሆነ፣ በሠራተኛ ማኅበሩ በኩል ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ባስቸኳይ እንዲስተካከልላቸው መጠየቃቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ለሞራላቸውም ይሁን ሆቴሉ ካለበት ደረጃ አንጻር እየተከፈላቸው ያለው ደመወዝ በጣም ትንሽ መሆኑን በመጥቀስ የሠራተኛ ማኅበሩ ሠራተኛውን ወክሎ እያደረገ ባለው የኅብረት ስምምነት ድርድር ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲደራደርና እንዲስተካከል እንዲያደርግ እየተማጸኑ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ሠራተኞች የሚከፈላቸው የወር ደመወዝ 80 በላይ ለሚሆኑ የጽዳት፣ የአትክልትና የዕቃ ጽዳት ሠራተኞች ደመወዝ እንደሚሸፍን የሚናገሩት ምንጮቹ፣ የሥር ሠራተኞች እንደነሱ ይከፈላቸው ሳይሆን አግባብ ያለውና ሁሉንም ነገር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የሚከፈላቸው መነሻ ደመወዝ 350 ብር መሆኑን የሚቃወሙት የሥር ሠራተኞች ብቻ ቢሆኑም፣ ሁሉም የሆቴሉ ሠራተኞች ወቅቱ ያመጣው የኑሮ ውድነትን መቋቋም ስላልቻሉ የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማንሳታቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩና ማኔጅመንቱ ከሚያዝያ ወር 2002 .. ጀምሮ በኅብረት ስምምነቱ ዙሪያ ሲደራደሩ ቆይተው የጽዳት፣ የመስተንግዶ፣ የአትክልተኛ፣ የዕቃ ንጽህና፣ የሾፌር፣ የሴኪዩሪቲ፣ ወዘተ ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ መሻሻል እንዳለበት፤ የኑሮ ውድነቱን በሚመለከት የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄዎች ላይ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እያደራደራቸው መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በማኔጅመንቱ በኩል ጥር 12 ቀን 2003 .. በቢሮው ተገኝተው ድርድር ያደረጉት የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጂያንፒየር ማኒጐፍ ሲሆኑ፣ የደመወዝን ጉዳይ በሚመለከት መወሰን እንደማይችሉ ገልጸው፣ የሆቴሉን ባለቤት ሼክ መሐመድ አል አላሙዲንን ጠይቀው በነገው ዕለት ምላሽ ለመስጠት ከቢሮው ኃላፊዎች ጋር መቀጣጠራቸውን ምንጮቹ አሳውቀዋል፡፡

ችግራቸውና እያነሱት ያለው ጥያቄ ለባለቤቱ ከደረሳቸው ያለምንም ጥያቄ እንደሚያስተካክሉላቸው እርግጠኛ ሆነው ሠራተኞቹ እየተናገሩ መሆኑን የገለጹት ምንጮቹ፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ እውነት አድርገውት የሠራተኛውን ጥያቄ ካቀረቡ፣ በነገው ዕለት አስደሳች ዜና እንደሚሰሙ በእርግጠኝነት እየተናገሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኅብረት ስምምነቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም በሠራተኞች ላይ ስለሚወሰደው የሥነ ሥርዓት እርምጃ፣ የማኔጅመንቱንና የሠራተኛው ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበትና የመሳሰሉት ላይ ገና ስምምነት ላይ አለመደረሱንና ድርድሩ እንደሚጥል ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ሠራተኞቹ እያነሷቸው ባሉት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንድሰጡን የሸራተን አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ጂያንፒየር ማኒጐፍን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ታዳሚዎች በተለይ በርካቶቹ የአፍሪካ መሪዎች ሸራተን ውስጥ በመሆናቸው ሥራ አስኪያጁ በስብሰባና በሥራ ላይ በመሆናቸው ሊያነጋግሯችሁ አይችሉም፤›› የሚል ምላሽ ከፀሐፊያቸው ስለተሰጠን አልተሳካልንም፡፡  

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማኔጀመንት አባል፣ በሠራተኛ ማኅበሩና ማኔጅመንቱ መካከል የተጀመረው ድርድር ሳይጠናቀቅ ምንም ዓይነት መረጃ ለማንኛውም ሚዲያ እንዳይሰጡ ተስማምተው በመፈራረማቸው ምላሽ እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment