Sunday, August 12, 2018

ግንቡ ፈርሷል፤ የድልድዩም መሰረት ተቀምጧል!!

(Aug 12, (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት))--በየዕለቱ ነገሮች እየፈጠኑ ነው። ኢትዮጵያችን ከውስብስብ ችግሮቿ ይልቅ የስኬት ብስራቶቿ በዝተውላታል። እሰየው ያስብላል። በየዕለቱና በየሳምንቱ በርካታ ተስፋን የሚያጭሩ የስኬት ዜናዎችን እየሰማን ነው። ነግቶ አዲስ ቀን ሲበሰር አዲስ የስኬት ሰበር ዜናዎችን መናፈቅ ጀምረናል። ይህ ትኩስ ዜና የመናፈቅ ስሜት ለወሬ ከመቋመጥ የመነጨ ሳይሆን፤ በመደመር መንፈስ የተቃኘው የመለወጥና የስኬት ዜናን ለመስማት ከመናፈቅ የመነጨ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ባሳለፍናቸው ሳምንታት የሰማናቸው ስኬቶች በዓመታት የማይገኙ ግዙፍ ተስፋዎችን ያስጨበጡ ናቸው። በተለይም በአሜሪካ የተደረገው የመደመር ዘመቻ በስኬት መጠናቀቁ ብዙዎቻችንን በደስታ አስፈንድቆናል። ይህ «ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንስራ» በሚል መንፈስ የተቃኘው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተጉትን ሁሉ ልናመሰግናቸውና ልናደንቃቸው ይገባል። በእርግጥም አሁን የጥላቻ ግንብ ፈርሷል። የድልድዩም መሰረት ተጥሏል።

ይህን ሃሳብ የሚያጠናክር አንድ ተወዳጅ የሆነ የህንዶች አፈ-ታሪክ አለ። በልዩነት በተሞላ የማህበረሰብ አወቃቀራቸው መካከል በጋራ ለመኖር ለዘመናት የተጠቀሙበት የፈጠራ ትረካ እንደሆነ ይታመናል። ነገሩ እንዲህ ነው።

አንዲት በአፈጣጠሯ የተለየች ወፍ ነበረች። ይህች ከአንገቷ በላይ ሁለት ጭንቅላት፣ ሁለት አእምሮና ሁለት አንገት እንዲኖራት ሆና የተፈጠረችው የወፍ ዘሪያ «ቤሩንዳ» ትሰኛለች። ለዘመናት ያክል በዚሁ መልክ ብትኖርም ከዕለታት በአንዱ ቀን ሁለቱ ጭንቅላቶቿ የተለያዩ ሃሳቦችን አራመዱና መግባባት አቃታቸው። በአንድ ሰውነት ላይ መኖራቸውን እስኪዘነጉ ድረስ ተጠላሉ። ከመጠላላት አልፈውም አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት ማውጣት ማውረዱን ተያያዙት።

 ሁለቱም የየራሳቸውን የመጠፋፋት ዘዴ ዘየዱ። ሁለቱም በየራሳቸው ያሰቡት የማጥፊያ ሀሳብ አንደኛውን ጭንቅላት በመርዝ በመግደል ብቸኛ ሆኖ መኖርን ነበር። እናም ሁለቱም አፎች መርዝ አዘጋጁና መርዙን ተሰጣጡ። በውጤቱም ቤሩንዳ የተሰኘችው ልዩ የወፍ ዝርያ ሞት መቋጫ ሆነ። የሁለቱም አፎች ስሌት አንዱን አጥፍቶ አንዱን ካለተቀናቃኝ በህይወት ለማቆየት ቢሆንም ራሱን ለማትረፍ የቻለ ግን አልነበረም።

ክሪሽና የተሰኘችው የምህረት አምላካቸው ለጥላቻ መጨረሻ ማስተማሪያ ይሆኑ ዘንድ ለእነዚህ ባለሁለት አፍ አንድ ወፍ በህይወት እንዲኖሩ ሁለተኛ ዕድል ሰጠቻቸውና ለሌሎች ማስተማሪያ ሆኑ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አፎች በፍቅር ከመኖር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተረድተው ልዩነታቸውን አቻችለው በሰላም ለመኖር ወሰኑ። ይህ የህንዳውያን አፈታሪክ ለህንዳውያን ልዩ መልእክት ነበረው። በልዩነታቸው ላይ ለሚመጣ አለመስማማት የማምለጫ መፍትሔ ሆኖ ለዘመናት በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት አግዝፎ የሚያሳያቸው መነፅር አድርገው ተጠቀሙበት።

 ይሄን አፈ ታሪክ ወደሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስናመጣው ብዙ ቁምነገር እናገኝበታለን። ሀገራችን የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ቋንቋዎችና ባህሎች ተሸምነው የሚደምቁባት ናት። የቋንቋም ሆኑ የባህል ልዩነቶች ውበት እንጅ የመጠፋፊያ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ የቀደሙት ታሪኮቻችን ይነግሩናል።

ይህ የህንዳውያን አፈታሪክ «ግንቡን እናፍርስ ድልድይ እንስራ» ወደሚለው ወቅታዊ እሳቤ ያደርሰናል። ባለመግባባት ለዘመናት ለያይቶን የነበረው ግንብ በመነጋገር በአስተማማኝ ሁኔታ ፈርሷል። አሜሪካ የሚገኘውና በሀገር ውስጥ ያሉት የሲኖዶስ አባላት ለዓመታት ከልሏቸው የነበረውን ግንብ አፈራርሰው ድልድዩን በእምነት መሰረት ላይ አፅንተዋል። እነሱና እኛ የሚባለው ከፋፋይ አስተሳሰብ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ተሽሯል። ውግዘት ተነስቷል፤ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ሥራ መቃናት በጋራ የሚሠሩ መሪዎችና ምእመናን ተፈጥረዋል። በተጨማሪም በውጭ ሀገር ከሚገኙ ዳያስፖራዎች ጋር ለዘመናት ተጋርጦ የነበረውን የመጠላላት ግንብ መፍረሱን አረጋግጠናል። ቀሪው የቤት ሥራ መሰረቱ የተቀመጠውን ድልድይ ማጠናከር ብቻ ይሆናል።

ከታሪካችን የምንረዳው በሀገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጠቧቸው የሚያዩት እውነት የጎረበጣቸው ሁሉ የመጨረሻው አማራጫቸው ስደት ነበር። አለፍ ሲልም እታገልላታለሁ ከሚሏት ሀገራቸው ጋር የጥላቻ ግንብ ሰርተው መቃወምን ሥራ ያደረጉ በርካታ ወገኖች ነበሩ። አሁን ያ ሁሉ አስተሳሰብ ለፍቅር ተንበርክኮ ለአንድነት እጅ ሰጥቷል።

 በውጭው ዓለም የሚገኙ ተቃዋሚዎች ሁሉ ዛሬ የተቃውሞው ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ የሚረዳላቸውን መሪ አግኝተዋል። ልዩነቶችን አጥብበው ለአንዲት ሀገር ብልፅግና መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው አማራጭ ሆኗል።

እናም «ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን መቼም አይቀየርምና» እነዚያ በባእድ ሀገር የነበሩ ወገኖቻችን ለኢትዮጵያና ለመሪዋ ያላቸውን ፍቅር በሚገባ አሳይተውናል። ለሀገራቸው እድገት የሚችሉትን ብቻ ሳይሆን ከሚችሉት በላይ ለማበርከት ቃላቸውን ሰጥተውናል። ቃላቸውን እንደሚያብሩም እናምናለን። አሁን የልዩነትና የመከፋፋል ግንብ ተንዷል።
ችግሮች በግልፅ መነጋገር ከተቻለ ለአንድ ሀገር የሚያስብ ዜጋን ወደ ተቀራራቢ ሀሳብ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር አይተናል። ለሁለት አስርት ዓመታት በጠላትነት የተፈራረጁ ወገኖች ሁሉ ሁለት ሰዓት ባልሞሉ ንግግሮች መግባባትንና የጥልን ግድግዳ መናዳቸውን አሳይተውናል። ይህ እንደ ሀገር ትልቅ ስኬት ነው። ቀጣዩ ሥራ የፈረሰው የጥላቻ ግንብ በይቅርታና በመደመር ስሜት በልፅጎ የሚያሸጋግር ድልድይ መሥራት ብቻ ይሆናል። ድልድዩንም ለመሥራት የሚያስችል መሰረት ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

No comments:

Post a Comment