Sunday, August 12, 2018

ዳያስፖራውን የአገሩ ጉዳይ ባለቤት የማድረግ ጉዞው ሊጠናከር ይገባል

(Aug 12, (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት))--በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአንድም በሌላ ምክንያት ከአገራቸው ርቀው በባዕድ አገር ዕውቀትና ጉልበታቸውን እያፈሰሱ ህይወትን ይገፋሉ፡፡ አበው “ምን ቢከፋ ዘመድ፤ ምን ቢጠም መንገድ” እንዲሉ፤ እነዚህ ዜጎች በሁኔታዎች ግፊት በአካል ከአገራቸው ርቀው ለመኖር ቢገደዱም፤ ኢትዮጵያዊነት ተፈትሎ በሕብር የተገመደ የማይበጠስ ድር ነውና ሃሳብና ልባቸው ሁሌም ከአገርና ሕዝባቸው ጋር ለመሆኑ ያፈሯትን ጥሪት ለአገራቸው ከማለት አለመቆጠባቸውን መጥቀሱ በቂ ይሆናል፡፡ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር ጉዞ ወቅት የታየው የዳያስፖራው ስሜትም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ዳያስፖራ እንደየ አካባቢው ሁኔታ የራሱን ምክንያት ሊያቀርብለት በሚችል ነገር ግን ሁነቶችን ባላገናዘበ መንገድ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚሸረሽሩ አደረጃጀት ፈጥሮ አንድ ላይ እየኖረ ግን ዕርስ በዕርሱ ተለያይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነቱንና ኢትዮጵያዊ ወገኑን አብዝቶ እየናፈቀ አጠገቡ ያለ ወንድሙን በጥላቻ ዓይን እየተመለከተ ኖሯል፡፡ አንድ ሆኖ ሕብረቱን በማጠናከር አገራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት ይልቅ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ ወዘተ. ኮሚዩኒቲ በሚል በፈጠረው አደረጃጀት ዕርስ በዕርሱ ተነቃቅፎ፣ አልፎ አልፎም ቢሆን በባዕዳን አገር ለራሱና ለአገሩ የሚያሰጠውን ክብር ዝቅ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ተከፋፍሎ በፈጠረው አደረጃጀት ልክም አገሩን ሲደግፍና ሲነቅፍም ታይቷል፡፡

 ምንም እንኳን በዚህ መልኩ በውስጡ የተከፋፈለ ማንነትን የያዘ ዳያስፖራ ቢሆንም፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ግንባታ ውስጥ ያለው ሚና የማይተካ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የአገሩ ጉዳይ ባለቤትም ነው፡፡ እናም ይህ ኢትዮጵያዊ ባለው አቅም፣ ዕውቀትና ገንዘብ በአገሩ የልማትና የዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ ተደምሮ የማይተካ ድርሻውን እንዲያበረክት መሠራት እንዳለበት ታምኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” በሚል እሳቤ በዶክተር አብይ አህመድ የተመራው ልዑክ በሰሜን አሜሪካ ያደረገው ጉዞ የዚህ ተግባር አብይ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ጉዞ የታለመለትን ዓላማ ያሳካና በውጤት የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ ለዚህ ስኬት እንዲበቃ ግን ከ14 በላይ ህዝባዊ መድረኮችና ከ23 በላይ ከልዩ ልዩ ታላላቅ ግለሰቦች እና አካላት ጋር የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ስለመካሄዳቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

“ስንደመር የምናምር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ቀን ማብሰር እንችላለን፤ እኛ ስንደመርና ስንጠነክር ዓለም ሁሉ እጁን ይሰጠናል” በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤ የተቃኘው ይህ የውይይት መድረክ፤ ፍቅርና አንድነትን ማምጣት ትልቅ ትግልን ያውም ራስን ማሸነፍን የሚጠይቅ መሆኑም ግንዛቤ የተያዘበት፤ ሁሉም ራሱን መግዛት ሲችል ኢትዮጵያውያን ዳግም የዓድዋን ታሪክ መድገም እንደሚችሉ የተነገረበት ነው፡፡ በዚሁ ልክ ተቃኝቶም የጥላቻን ግንብ በማፍረስ የፍቅር ድልድይ ለመገንባት ሁሉም ራሱን በማሸነፍ በፍቅር ሊደመር፤ የአገሩ ጉዳይ ባለቤት ሆኖም ሊሠራ እንደሚገባ የጋራ ሃሳብ የተንጸባረቀበትም ነበር፡፡

 በዚህ መልኩ የተደረሰው የጋራ መግባባት መልካም ቢሆንም፤ ዳያስፖራውን የአገሩ ጉዳይ ባለቤት የማድረግ ጉዞ ግን የአንድ አካል ተግባር ብቻ አለመሆኑን ተረድቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም “መሪዎች በተለያየ አገር የህዝብ ድምጽ ሳጥን ይሰርቃሉ፤ እንደ ዶክተር አብይ ግን የሰረቀ የለም፤ የህዝብን ልብ ሰርቀዋልና፤ እናም ሥራውን ለዕርሳቸው ብቻ አንተውም፤ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣለን፤” የሚል ሃሳብ ከዳያስፖራው አንደበት ያስደመጠው ይህ መድረክ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአገሩን ጉዳይ በኃላፊነት ወስዶ ሊሠራ፣ ዕርስ በዕርሱም ሊተሳሰብ እንደሚገባና ለሁሉም የምትበቃ የጋራ ኢትዮጵያን ለመገንባትም የጋራ ቃልኪዳን የተገባበት ነው፡፡

 ይሁን እንጂ ይህ መግባባቱ የሚዘልቀው፣ ቃል ኪዳኑም የሚጸናው፣ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ቀና ሃሳቡን፣ የፍቅር ልቡን፣ ጉልበት፣ ዕውቀትና ገንዘቡን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ማዋል፤ የገጽታዋ ምሣሌ፣ የዲፕሎማሲዋም አምባሳደር መሆን ሲችል ነው፡፡ ለኢትዮጵያ እኔ ሳይሆን እኛ የሚል እምነት እንደሚያስፈልጋት አውቆ ልዩነቱንና መከፋፈሉን ትቶ በአንድ ላይ ጉልበት ፈጥሮ የድህነቷን ካባ ለማውለቅ ሲተጋ ነው፡፡ በምክንያት ታግዞ ለአገሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የሚውል በሳል ሃሳብ በማቅረብ፤ ለእነዚህ ሁሉ አገራዊ ጉዳዮች ከቃል ያለፈ ተግባር ለህዝቡ በማሳየት በማረጋገጥም ነው፡፡

 የዳያስፖራው ፍላጎትና ቁርጠኝነት ግን ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችልም ዕሙን ነው፡፡ እናም ይህ ዳያስፖራ ኃላፊነት እንዲወስድ ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ የሚሆንበትን ዕድልና ሁኔታ ማመቻቸት ይጠይቃል፡፡ ይህ የቤት ሥራ ደግሞ በቀዳሚነት የመንግሥት ሲሆን፤ የውጭ ግንኙነት ሥራውን የሚያከናውነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ራሱን ለዚህ በሚያመች መልኩ በማደራጀት ጭምር የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ህዝቡም ቢሆን ይህ የዳያስፖራ ማህበረሰብ የራሱ አካል፣ ወንድምና እህት መሆኑን ተገንዝቦ በፍቅር ሊቀበለው፤ የልማትና ዕድገቱ አጋር አድርጎ ሊመለከተውና በዚሁ ልክ አምኖ ሊቀበለው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን የጥላቻው ግንብ መፍረሱ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የመደመር ድልድይ መገንባቱ ዕውን ይሆናል፤ የዳያስፖራው የአገሩ ጉዳይ ባለቤትነትም ይጠናከራል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

No comments:

Post a Comment