Tuesday, July 31, 2018

የደመርነውን መቀነስ ለምን?

(July 31, (አጀንዳ, የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ))--ሐምሌ 7 እና 8 ቀን 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ልዩ ቀን ሆኖ በታሪክ ማህደር ሰፍሮ ይታወሳል። ሁለቱ አገራት ከሃያ ዓመታት በላይ የዘለቀውን መቃቃር የጥላቻን ግንብ አፍርሰው በመካከላቸው የነበረውን ጥቁር መጋረጃ ቀደው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በፍቅር ከፍተዋል። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ፊት አውራሪነት ምናልባትም ከወር በፊት የታሰብ የማይመስል የሚመስለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በፍቅርና ይቅር ባይነት ነብስ ዘርተውበታል። ይህም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር የተወደሰና ለዓለም በምሳሌነት የሚጠቀስ ሠናይ ተግባር መሆኑን ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ሲያራግቡት ከርመዋል።

ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ የነበረው ሥነ - ሥርዓት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን በደስታ እንባ ያራጨ ለሁለቱም አገራት ህዝቦች በርካታ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትርጉምና ተስፋ የታየበት ነበር።

መደመር ምን ያህል ረቂቅ እንደሆነ በሳይንሳዊ መንገድ ከሃሳቡ ጠንሳሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አንደበት በኮመኮምንበት ምሽት ደስታችንን በቅጡ እንኳን አጣጥመን ሳንጨርስ በማህበራዊ ሚዲያው የተዘራው እሾህ ስጋት ሆኖ እንቅልፍ ሲነሳን አድሯል። በጥቃቅን ምክንያቶች አጋጣሚን ተጠቅሞ መደመርን የሚገፋ የዘረኝነት ጥላ ዳግም በማህበራዊ ሚዲያው ሲዘራ ማየት እያመመን ከእንቅልፍ ጋር ታግለናል።

በወቅቱ በማህበራዊ ሚዲያው የተስተጋቡ እሰጥ አገባዎች መጋነን ባይኖርባቸውም በእለቱ መቀጨት ሲገባቸው በቀጣይ ቀናትም አጀንዳ ሆነው መቀጠላቸው የወደ ፊቱን ከማሰብ አኳያ ስጋትን መጫራቸው አልቀረም። በማህበራዊ ሚዲያ እንደ ቀልድ የተጀመረ ነገር በፍጥነት ተዛምቶ ኋላ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከባድ ከመሆኑ አኳያ ብዙዎችን አሳስቧል። ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው እየተራመደ ያለው ልዩነት አመክንዮን ያማከለና የሰከነ ክርክር አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የብሔር አሰላለፍን እየያዘ መምጣቱ ነው።

ለዘመናት የኖረውን አብሮነት እና አንድነት ማጎልበት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እና አሁን የደረስንበትን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችሉ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መከራከር ሲገባ፣ በህዝቦች መካከል ልዩነቶችን የሚያሰፉ፣ ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ፣ የህዝቦችን መተማመን የሚሸረሽሩ፣ አንድነታችንን ሊጎዱ የሚችሉ ትንንሽ የልዩነት ጉዳዮችን በማጉላት ላይ እየተጠመዱ ይገኛሉ። እንደዚህ ዓይነት ገንቢ ያልሆነ ንትርክ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አሁን የደረስንበትን የለውጥ ምዕራፍ ወደኋላ እንደሚጎትት መታወቅ አለበት።

በሚሌኒየም አዳራሽ መድረክ ላይ የሙዚቃ ዝግጅቶቻቸውን ባቀረቡ አርቲስቶች መነሻነት የተጀመረው የብሽሽቅ ፖለቲካ ሳምንቱን በፖለቲካ ሹመትና በስፖርት መድረክ ሳይቀር ሲስፋፋ ተመልክተናል። የአርቲስቶችን የዘር ሐረግ መዞ በመድረኩ ያዜሙትን ወይንም ያስተላለፉትን መልዕክት ቃላት እየሰነጠቁ መነቋቆር በማህበራዊ ድረ ገፆች አንድነትና ፍቅርን ለማይፈልጉ ብሔርን ከብሔር ማጋጨት አላማቸው አድርገው ለሚንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን ሲፈጥሩ ተመልክተናል። በዚህም ሳይበቃ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ጋር ተያይዞ የዘር ሐረግ እየተመዘዘ የቃላት ጦርነቱ ሲጦፍ አይተናል። ከወደ እግር ኳሱም መንደር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቋጨቱን ተከትሎ ነገሮች ከዘረኝነት ጋር እየተቆራኙ መናጨቱ ፋሽን ሆኖ ነበር።

ከአርቲስቶቹ ጉዳይ ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ሹመቱና የእግር ኳሱ መንደር ስህተቶች ተፈጥረዋል አልተፈጠሩም ብሎ መሞገት ሳይሆን እነዚህን ጉዳዮች ወደ ዘር ፖለቲካ አምጥቶ መበሻሸቅን ምን አመጣው ? ችግሮችን በሠለጠነ መልኩ መተቸትና መንቀፍ እየተቻለ ይህ የሆነው እከሌ ብሔሩ እንደዚህ ስለሆነ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስን ምን አመጣው? በእነዚህ ሽኩቻዎች መካከል ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት አርፈው ለማይተኙ ጥላቻ ሰባኪዎች መጠቀሚያ ለምን ይኮናል? ትናንት ተደመርን ብለን አደባባይ አልበቃ ብሎን የፈነጠዝን ዛሬ አንድነታችን በቅጡ ሳይጠነክር የተያያዘ እጃችንን አላቀን በመሃል ንፋስ እንዲገባ ለምን እንፈቅዳለን ? መደመራችንስ እስከ ምን ድረስ ነው? ወይንስ መደመር ሳይገባን ነው ተደመርን እያልን ያለነው?

በደፈናው ሁላችንም ተደምረናል ብለን መንገድ ከመጀመራችን በፊት እስከ ምን ድረስ እንደተደመርን ራሳችንን መፈተሽ ያለብን አሁን ነው። ምክንያቱም የውሸት ከሆነ የተደመርነው ሄዶ ሄዶ በዜሮ እንዳይጣፋ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም።

ተደመርን ስንል ይቅር ተባባልን፤ ተደመርን ስንል ተፋቀርን የሚያለያዩንን ነገሮች ወደ ኋላ ትተን አንድ የሚያደርጉንን አጥብቀን ያዝን ማለት ነው። መደመር ጥላቻን፤ ዘረኝነትን፤ ክፋትና ምቀኝነትን እንዲሁም ስግብግብነትን ማራቅና መጠየፍ ነው። መደመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሂሳባዊ ስሌት ካብራሩትም በላይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመር ውስጥ መቀነስ፤ ማባዛትና ማካፈል እንዳለ ነግረውናል። መደመር ፍቅርን፤ አንድነትና መተሳሰብን፤ ይቅርባይነትና ለወገን ተቆርቋሪነት ነው። መቀነስ ጥላቻን፤ ዘረኝነትን፤ ስግብግብነትና ሌብነትን ነው። ፍቅርን፤ አንድነትንና መተሳሰብን እንዲሁም ጥበብን መደመር ከዚያም ማባዛትና ለወገን ማካፈል ነው። ይህን ብለን ከተደመርን በጥቃቅን ነገሮች መነሻነት ወደ ዘረኝነት ለመሄድ ለምን እንዳዳለን?

ይቅር ባይነት የመደመር የማዕዘን ድንጋይ ነው። የተደመረ የበደለውን ከልቡ ይቅር ይላል። በዚህ ስሌት ውስጥ ተበዳይ ያለፈ በደሉን አንስቶ ታሪክ በማጣቀስ ወደ ኋላ ተመልሶ ወቃሽና ከሳሽ አይሆንም። በዳይም ካለፈ ታሪኩ ተምሮ ዳግም ላለመበደል ይጥራል፤ ሌሎችም በዳይ እንዳይሆኑ ዘብ ይቆማል። በዚህም ቂም በቀል ቦታ አይኖረውም። በሙዚቃ፤ ኳስና ሌሎች እዚህ ግባ በማይባሉ ነገሮች በሚፈጠሩ ጥቃቅን ጉዳዮች አንዳችን አንዳችንን ታሪክ አስታውሰን ቃላት እየሰነጠቅን የምናብጠለጥል ከሆነ ምኑን ተደመርነው? አንዱ ወደ ጥፋት መንገድ ሲያመራ ሌላው አስተምሮ ከመመለስ ይልቅ ተከትሎት ወደ ገደል የሚያመራ ከሆነ፤ ነገሮች ወዳልሆነ አቅጣጫ ሲያመሩ ተው ባይ ከሌለ፤ ብዙ መልካም ጎዳዮችን በጉያችን ሸሽገን መጥፎ ነገሮች ሚዛን እንዲደፉ ከፈቀድንላቸው የት ልንደርስ ነው? በብሽሽቅ የት ድረስ ተጉዘን የምንናፍቃትን የተሻለች ኢትዮጵያ ልንመለከት ነው? በትንንሽ ቀዳዳዎች ሰላምና አንድነታችንን ለማይፈልጉ አንገት ማስገቢያ ዕድል ከፈጠርን አሁንም የወደ ፊቱ አስፈሪ ይሆናል።

የሚገርመው ነገር ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያው ሲረጭ የነበረው መርዝ መነሻው አርቲስቶችን ከማፎካከር ይሁን እንጂ ለመበሻሸቅ በር የከፍተነው ራሳችን ነን። ለዚህ ደግሞ አለማወቅ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በእለቱ በየትኛውም አርቲስት ላይ ጥፋት ነበር ወይንም ለሽኩቻ የሚያበቃ ስህተት ነበር ለማለት ይከብዳል። ሁሉም አርቲስቶች በሚያዜሙበት ቋንቋ ፍቅርና አንድነትን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን ከመስበክ በቀር አንድን ብሔር ከሌላው ለብሽሽቅ የሚያበቃ ሲፈፅሙ አልታዩም። ይሁን እንጂ አንዳንድ አዋቂነን ባዮች ምንም ባልገባቸው ነገር በማህበራዊ ሚዲያው ያንፀባረቁት ሃሳብ ለሽኩቻው መነሻ ሆኗል። ይህም ሌሎችን ስሜታዊ በማድረግ የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲይዙና አሉታዊ ምላሽ እንዲያንፀባርቁ አድርጓቸዋል። ይህ ክፍተት ወይንም ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተፈጠረው አለመግባባት አንድነትን ለማፍረስ የፌስ ቡክ ሰሌዳቸው ላይ አፍጥጠው ለሚጠብቁት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።

አንድነትን ለመናድ የተፈጠረውን የፍቅርና ይቅር ባይነት መንፈስ ለማደፍረስ የሚሹ አጋጣሚው ተፈጠረላቸው እንጂ አጋጣሚውን አልፈጠሩትም። አዋቂ ነን ባዮች ባልገባቸው ነገር ወይንም እርግጠኛ ባልሆኑበት ጉዳይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሲደሰኩሩ አስተምሮ መመለስ ይቻል ነበር። ከዚህ ይልቅ ታሪክና የዘር ሃረግን እየመዘዙ መናቆር ተፈጠረ። በመማማርና በውይይት ሊቋጭ የሚችል ጉዳይ ለቀናት አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል ተፈቀደለት። ይህም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ላይ ብዙ ጥያቄ ያስነሳ ብቻም ሳይሆን ለወደ ፊቱም ባለማወቅ እንዳንጠፋበት ያሰጋ ጉዳይ ነው። ማህበራዊ ሚዲያ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ በአግባቡ ካልተጠቀምነው ጉዳቱም ያን ያህል የከፋ እንደሚሆን ግልፅ ነው። ይህን ካልተገነዘብን ስለ አንድነት እያወራን አንድነትን ለማይፈልጉ መጠቀሚያ እየሆንን መቀጠላችን የግድ ይሆናል።

በመንግሥትም ይሁን በግለሰቦች ደረጃ የተለያዩ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የተለያዩ ስህተቶችም ይፈፀማሉ። ማንም ቢሆን ፍፁም አይደለምና በየትኛውም ደረጃ ስህተቶች እንደሚኖሩ ማመን ግድ ነው። እነዚህን ስህተትና ክፍተቶች መንቀፍና መተቸት ወይንም ማጋለጥ ለድርድር አይቀርብም። ይሁን እንጂ ትችቶችን የምናስተጋባበት መንገድ በተለይም ከዘረኝነት የፀዳ ሌሎችን ሊያስተምር በሚችል መልኩ ቢሆን መልካም ነው። ስሜታዊነት የተሞላባቸው ብሔር ተኮር ትችቶች ተያይዞ ገደል ከመግባት በዘለለ የሚፈይዱት ነገር አይኖርም።

ሮም በአንድ ጀንበር ተገንብታ እንዳላለቀች ሁሉ የምናልማት ኢትዮጵያም ነገ ተፈጥራ ልናያት አንችልም። ተደምረናል ያልንለት የአንድነት መንፈስም ለመሸርሸሩ ጊዜ እንደፈጀ ሁሉ እንደ አለት ጠንክሮ እንዳባቶቻችን እንድናየው ጊዜ ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እያሳዩት ያለውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጎዳና ለመደገፍ ከምንም በላይ ትዕግስት ሊለየን አይገባም። ከምንም በላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰበኩት የአንድነት መንፈስ በውስጣችን ማኖር የግድ ነው። ይህን ወደ ጎን ትተን እንከተለዋለን ማለት ትዝብት ላይ ይጥላል። ዲያቆን ዳንዔል ክብረት እንዳለው «ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ከቻልን አብረን እንሩጥ፤ ካልቻልን እንከተለው፤ ይህም ካቃተን እንቁም እንቅፋት እንዳንሆን»።

ማህበራዊ ሚዲያውን ለመልካም ነገር እንጠቀመው፤ አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን እንስበክበት። በአሉባልታዎች መነሻነት ወይንም በግለሰቦች አስተሳሰብ ምክንያት ስሜታዊ ምላሾችን በማንፀባረቅ አንድነታችንን ወደ ሚሸረሽር ጎዳና አንጓዝ። ተደምረናል እያልን የደመርነውን ፍቅር፤ ሰላም፤ አንድነትና ይቅር ባይነትን መቀነስ፤ የቀነስነውን ዘረኝነት፤ ጥላቻና ክፋትን መደመር፤ የቀነስነውን ማባዛት ከዚያም ማካፈል « ታጥቦ ጭቃ» እንዲሉት ዓይነት እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ይቅር ባይነት ከልብ ሲሆን አንድነት ይፈጠራል። አንድነት ሲኖር ሰላም ይፈጠራል። ሰላም ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን መላው የዓለም ህዝብ ውድ ዋጋ እንኳን ከፍሎ ማግኘት የማይችለው የህይወት ቁልፍ ነው። እንደ አለት የከበዱ ግዙፍ አገራዊ ችግሮችን ተሸክመን አብዛኛውን ጊዜያችንን በማህበራዊ ሚዲያው ሽኩቻ ማጥፋት ዞሮ ራሳችንን ማጥፋቱ አይቀርም። ምዕራባውያን ወደ ውህደ ተዓለም (globalization) እየተንደረደሩ እኛ ቃላት እየሰነጠቅን፤ ከጉልህ የጋራ አንድነታችን ይልቅ ታሪካዊ ቀዳዳዎችን እየፈለግን መጓዝ የታሪክ ተወቃሽም ያደርገናል። ልዩነት ይኖራል፡፡ አንድ ቤተሰብ ውስጥም ልዩነት ይኖራል፡፡ በልዩነት ተከባብሮ፣ አንድ የሚሆኑበት ነገር ላይ አብሮ መስራት ግን ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ለመመለስ፤ ካልሆነም ቢያንስ በረሃብና በችግር የሚሰቃዩ ንፁሃን ዜጎችን ለመታደግ ዓይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› እንዲሉ ከችግራችንና ከድህነታችን በላይ ለጥቃቅን ልዩነቶች ቦታ ሰጥተን መነቋቆር እንደ ሰው ለሚያስብ ሰው ልብ ይሰብራል፡፡ ስለሆነም ትንንሽ የልዩነት ሀሳቦችን አጉልተን ከመጨቃጨቅ ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ትልልቅ ሀሳቦች ላይ ማተኮር፣ ጥርጣሬን የሚያሰፉ ጉዳዮችን ከማጉላት ይልቅ መተማመንን ለማጎልበት፣ ጥላቻ፣ መራራቅ እና ለግጭት የሚጋብዙ ሃሳቦችን ከማራመድ ይልቅ ፍቅር፣ መቀራረብ እና ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት ለሁላችንም ይጠቅማል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ቦጋለ አበበ))

No comments:

Post a Comment