Saturday, June 30, 2018

የነዳጅ ሀብታችን ለልማትና ለሰላም

(June 30, (ርዕሰ አንቀፅ))-- ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የድፍድፍ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። እነሆ ይሄው ፍለጋ እውን ሆኖ ከሰኔ 21 ጀምሮ ድፍድፍ ነዳጅ በሙከራ ደረጃ ማውጣት እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ «እንኳን ደስ አላችሁ» ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያውያ የምስራች አብስረውናል። በእውነትም ይሄ እጅግ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው- ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ በሙከራ ደረጃ የሚመረተው ድፍድፍ ነዳጅ በቀን 450 በርሜል ነው።ሆኖም ግን በቅድመ ጥናት ሙከራው ከፍተኛ መጠን ያለው መሆኑ ተረጋግጧል።የመስመር ዝርጋታው ሥራ ተጠናቆ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ ሲጀመርም በመጀመሪያው ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት አገር ናት። የተማረውና ሥራ አጥ የሆነው የህብረተሰብ ክፍልም ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው። በተለያየ ጊዜ የሚነሳውና የግጭትና የብጥብጥ ምክንያት እየሆነ ያለውም ከሥራ አጥነቱ ጋር ተዳምሮ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። ይሄ ሁሉ ችግር ተጓዳኝ ምክንያት ቢኖረውም በዋነኛነት ተጠቃሹ ግን የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አነስተኛ መሆን ፣ኢንቨስትመንት አለመስፋፋትና የሥራ ዕድል በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን አዲስ ለተጀመረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻ ምክንያት የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መብዛትና የሥራ ዕድል አለመኖር፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የፈጠሩት ግፊት ነው።

አገሪቱ ዛሬ ያገኘችው የነዳጅ ሀብት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ይፈታል ተብሎ ባይታሰብ እንኳን ለነዳጅ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ ይቀንሳል፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ይከፍታል፤ከአገሪቱ የተረፈው ነዳጅ ወደ ውጭ ተልኮ የውጭ ምንዛሪ ችግራችንን ይፈታል። ይሄ ደግሞ ሲቀናጅ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ያመጣል።

ይሁን እንጂ ነዳጅ ብቻውን የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ያላት አገር ናት። ዋነኛው የኑሮ መሰረቱ ግብርና ነው። በመሆኑም የህልውናችን መሰረት የሆነውን ግብርና ይበልጥ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አማራጭ የለውም። ከዚሁ ጎን ለጎን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በሚደረገው ጉዞ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ፣ ኤክስፖርት በሚደረጉ ምርቶች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። ይሄን እያሳደጉና የተገኘውን የነዳጅ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ድህነት ታሪክ ለማድረግ በህብረት፣ በፍቅር እና በሰላም መንቀሳቀስ ይገባል።

ነዳጅ ለአንድ አገር አንዱና አስፈላጊው ሀብት ቢሆንም በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች የተመለከትነው እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሳይሆን የፀብና የጦርነት ምንጭ ሆኖ ነው።ለዚህ በምሳሌነት ናይጀሪያ፣ ኬንያ እና ሱዳንን ማንሳት ይቻላል። በሱዳን የነዳጅ መገኘት ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ ለጦርነት መነሻ፣ ለሀገሪቱ መከፈል እስካሁንም ድረስ ለብጥብጥና ለዜጎች ስደት ምክንያት ሆኖ ዘልቋል።ይሄ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። «ብልጥ ከሌላው፤ ሞኝ ከራሱ ስህተት ይማራል» የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር በዋነኛነት የሚጠቅመን ለኢትዮጵያውያን ነው። በሌሎች አገሮች የተከሰተው በአገራችን እንዲከሰት መፍቀድ የለብንም፡፡ስለሆነም የተገኘው ሃብት ለልማታችንና ሰላማችን ማዋል ይጠበቅብናል፡፡ለዚህ ደግሞ ህዝብና መንግሥት ተቀናጅተው መስራት ይገባቸዋል።

የተገኘው ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ነዳጅ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያድናል፡፡እንዲሁም ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚገኝበት ነው። ለሥራ አጡ ወጣት የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ ሁሉም ዜጋ የሀብቱ እኩል ተካፋይ የሚሆንበት መሆንም ይገባል። ነገር ግን ነዳጅ ተገኘ ተብሎ በመጥፎ ምሳሌ እንደምናነሳቸው እንደሌሎቹ አገሮች ወደ መስገብገብ የሚገባ ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ፤ ከትርፉ ይልቅ ጥፋቱ ያይላል፡፡ ውጤቱም ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ይሆናል።ስለዚህ የተገኘውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።የተገኘው የነዳጅ ሃብት ለልማት በማዋል ሰላማችንን ዘላቂ እንዲሆን መስራት ተገቢ ነው፡፡

ነዳጅ ተገኘ ተብሎ መቀራመት አሊያም መስገብገብ የሚከሰት ከሆነ የሀብቱ መገኘት አስፈላጊ ሳይሆን ጎጂ ነው፡፡ ካወቅንበት አገራችንን አልምተን የምናድግበት፣ የምንበለፅግበት ነው፡፡ ካላወቅንበት ግን ሰላማችንን የሚያደፈርስ፣ አንድነታችንን የሚያናጋ ስለሚሆን ለሰላማችንና ልማታችን ዘብ መቆም ይጠበቅብናል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ)

1 comment:

Unknown said...

Congratulation! to all Ethiopian.we have to make peace,Good please Ethiopia.

Post a Comment