Monday, June 25, 2018

ማመስገን መሰልጠን ነው፤ መግደል መሸነፍና መዋረድ ነው!

(June 25, (ርዕሰ አንቀፅ))--ምስጋና የሚለውን ቃል መዝገበ ቃላት ሰፊ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ጥናት ተቋም ባሳተመው መዝገበ ቃላት አመሰገነ ማለት «ለሥራው መልካም ሥራ ተገቢው ቦታ ተሰጠው»ይለዋል፡፡

ማመስገን መልካም ነገር ነው፡፡ ቢቻል ለተደረገልን ብቻም ሳይሆን ገና ለሚደረግልንና ላልተደረገልንም ጭምር ልናመሰግን ይገባል፡፡መልካም ነገሮችን ሰርተው መልካም ነገርን ያስተማሩንን ማመስገን እርካታው ከተመስጋኙ በላይ ላመስጋኙ ይሆናል።

ደራሲ ጆን ሄንሪ ጆዌት «ምስጋና ክትባትና ፀረ መርዝ፤ እንዲሁም የቆሰለውን የሚጠግን መድሃኒት ነው» ሲሉ፤ ዌስተር ኢክሃርት የተባለው የክርስቲያናዊ ፀሀፊና የሐይማኖት ተመራማሪ «ሕይወትህን ሙሉ የምታቀርበው ብቸኛ ፀሎት አመሰግናለሁ ከሆነ በቂ ነው» ብለዋል። ነብዩ መሐመድም «ለሆነልህ ሁሉ በቂ ምስጋና ማቅረብ የተደረገልህ ነገር ስለመቀጠሉ ማረጋገጫ ያስገኝልሃል» ማለታቸው ይጠቀሳል።

የመልካም ስራ መገለጫው ብዙ ነው፡፡ የመልካም ሰው መገለጫው በምድር ላይ እያለ ሽልማትን ሳያስብ ያከናወናቸው በጎ ተግባራት ናቸው፡፡ በምድራችን ላይ መልካም ሥራን ሠርተው በመልካምነታቸው ስንጠቅሳቸው የምንኖር ብዙ መልካም ሰዎች አሉን፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መልካም ስራቸውን ዘንግተን ወይም አንቋሸን መልካምነታቸውን ሳንገላልጥላቸው ወደ የማይቀረው ዓለም የሸኘናቸውም የዛኑ ያህል ብዙ ናቸው፡፡መልካም ሥራ ለእራስ እርካታ ተብሎ የሚሠራ ቢሆንም ሰዎችን በመልካም ሥራቸው ማመስገኑ ሌሎች ብዙ መልካም ሠሪዎች እንዲፈጠሩ ያግዛልና ትናንት የተደረገው አስደናቂ የምስጋና በዓል መነሻ እንጅ መጨረሻ እንደማይሆን ይታመናል፡፡

የምስጋና ሰልፉ የተጠራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ሦስት ወራት ባልሞሉ ጊዜያት በአገር ውስጥና በውጭ እያከናወኑት ላሉት አወንታዊ እርምጃ እና ላስመዘገቡት ውጤት እውቅና ለመስጠት ነው። እንዲሁም የጀመሩት ለውጥ ዘላቂ እንዲሆን ለማገዝ ታስቦ ነው፡፡ ህዝቡም ለስኬቶቻቸው የሚመጥን ምስጋና አቅርቦላቸዋል። ይህ እንደሀገር የሚያስመሰግን ተግባር ሆኖ በታሪክ ሊመዘገብ የሚገባው ተግባር ሊሆን ይገባል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ክስተት የሚመስሉ ስኬቶችን እንደሀገር ተጎናፅፈናል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ ከተፈጠረው አንጻራዊ መረጋጋት በላይ በዲፕሎማሲው መስኮች እየተሳካልን ነው፡፡ ስልጣናቸውን በፍቅርና በይቅርታ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ስኬታማ እየሆኑ ነው፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በግብጽ፣ በጅቡቲ፣ በኡጋንዳ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ በሶማሊያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ፈርጀ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን አስመዝግበው ተመልሰዋል፡፡ የሀገራቱን ወዳጅነት ከማጠናከር ባለፈ በኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ላይ ያተኮሩ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡ በተለይም ለዓመታት በጥርጣሬ ይተያዩ የነበሩትና የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለማቀራረብ የተደረገው ጥረት ተሳክቶ የኤርትራ መንግሥት ልዑኩን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መወሰኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የዲፕሎማሲ ብቃት ያስመሰከረ ነው።

በተለይም ለዓመታት በእስር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን እያስፈቱ መመለሳቸው የተለየ ክብር የሚያሰጣቸው ስኬት ሆኗል፡፡ ካስፈቷቸው ዜጎቻቸው ጋር በአንድ ጣራ በፍቅር መምጣታቸው ደግሞ በርግጥም የሚናገሩትን በተግባር ያሳዩ አስብሏቸዋል። የዜጎች መብት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በተለያየ መንገድ የታገሉ ፖለቲከኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሃፊዎች፣ ምሁራን… ወዘተ ከእስር ማስፈታታቸው ለምስጋና የሚያበቃቸው ሌላው ተግባር ነው።

ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የተሰራው ሥራ በጣም አበረታችና ሊደነቅ የሚገባ ነው። ይህን ጥሪ ተከትሎም ነፍጥ አንስተው ሲዋጉ የነበሩ ድርጅቶች ሳይቀሩ ሠላማዊ ጥሪውን መቀበላቸው የስኬቱ ማሳያ ነው።

በተለይም የህግ የበላይነት ከማስፈን፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችን ከማስከበር፣ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ፣ የመሰብሰብ መብት እና የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል። እነዚህን ስኬቶችም የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረትና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአድናቆት መልዕክት መላካቸው በርግጥም ስኬቱ ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አውቅና ያገኘ ተግባር መሆኑን ለማረጋገጥ እንችላለን።

ጀርመናዊው ጳውሎስ ፖልማን በብሩህ ተስፋ ስለተሞሉ መሪዎች ሲናገር‹ ‹የፖለቲካ መርሆዎቻችን ከፍ ያሉ ኃላፊነቶች አሉባቸው፡፡ ነገር ግን እንደማንኛውም የህይወት ውጣ ውረድ ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት ሊሳካላቸውም ላይሳካላቸውም ይችላል፡፡

እንደ ዜጋ የእኛ ድርሻ መሪዎቻችንን እንዲሳካላቸው በቂ ድጋፍ መስጠት ነው›› ይላል፡፡ በርግጥም በድህነት ውስጥ ለኖርን ህዝቦች ፍላጎታችን ብዙ በመሆኑ ጥያቄዎቻችንን በአንድ ጊዜ ለማሟላት እንደማይቻል ይታመናል፡፡ ያም ሆኖ አሁን ለተጀማመሩት ዲፕሎማሲ ስኬቶችም ሆነ አንፃራዊ ሠላም መፈጠር የነገ የተስፋ መንገድ የሚያመላክቱ ናቸውና ልናመሰግናቸው፣ ልናደንቃቸው ብሎም ልናግዛቸው ይገባል።

ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ፍቅር ፣ ሰላም ፣ አንድነትን እና ይቅር መባባልን ሰብከዋል። እንዲሁም በተግባር ዘርና ሀይማኖት ሳይለዩ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር እየተማከሩ የህዝብ ጋር ወገንተኛ መሆናቸውን በተጨባጭ በማስመስከራቸው ምስጋናው ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም።

ሁልጊዜም መልካም ሠሪዎች እንዳሉ ሁሉ መጥፎ አሳቢዎችም አይጠፉምና በምስጋና ሰልፉ ላይ በእኩይ ዓላማ ተነሳስተው የሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ይህ ደግሞ አሸባሪነት ነው። መንግሥት በአፋጣኝ በአሸባሪዎቹ ላይ እርምጃ ወስዶ ለህዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ)

No comments:

Post a Comment