Friday, February 16, 2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ

(የካቲት 08/2010, (ኢቢሲ))--ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፍላጎታቸው እና ፍቃዳቸው ከሀላፊነታቸው ለመነሳት የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ይቀበላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።



ጠቅላይ ሚንስትሩ ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት ለመነሳት ለንቅናቄው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅርበው እንደተቀበላቸው እና ይህም ለማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ ይፀድቃል ብለው እንደሚጠብቁም ነው የተናገሩት።

ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ለመነሳትም ጠቅላይ ሚንስትሩ ለግንባሩ ምክር ቤት መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል። ጥያቄያቸው የመጨረሻ ውሳኔውን የሚያገኘው በኢህአዴግ ምክር ቤት እንደሚሆንና ጥያቄያቸውን ተመልክቶ ምላሹን በቅርቡ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁም ገልፀዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በሀገሪቱ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ለመስጠት የቻሉትን ማድረጋቸውን ተናግረው፥ አሁን ስልጣን የሚለቁትም በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግና መፍትሄ አካል መሆን አስፈላጊ ነው ብለው በማመናቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ያቀረቡት ጥያቄ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስም በስራቸው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልፀዋል
ኢቢሲ

No comments:

Post a Comment