Wednesday, December 13, 2017

የሺሻ ነገር

(Dec 13, (አጀንዳ))--ሺሻን አብዛኞቻችን እናውቀዋለን። አዲሳችን አይደለም፤ ዛሬ ስሙን ቀይሮ ሺሻ ተብሎ ተውቦ በቆንጆ ዕቃ አሸብርቆ፣ትንባሆም በቅመም ተደርቶ፣ በፓኬት ታሽጐ መጣ እንጂ ያው «ጋያ» ስንለው የኖርነው ነገር ራሱ ነው። በእርግጥ ብዙ ነገሩ ተቀይሯል። በደቡብና በጋምቤላ ክልሎቻችን ያሉ ህዝቦች ከቅል በተሰራ ማጨሺያ ውስጥ ከታቹ ውሃ ከመሃሉ ትንባሆ ከላዩ እሳት እየተደረገበት ማማሰያ በመሰሉ ቀጭን የእንጨት ቧንቧ እየተሳበ እየተንደቀደቀ ይጨሳል።

ጭሱ በአፍ በአፍንጫ ሲንቧለል የሚሰጠው ውስጣዊ /አካላዊ፣መንፈሳዊ/ ርካታ መኖሩን የሚመሰክሩ ሱሰኞች ቁጥር ቀላል አይደለም። ከጥቂት ዓመታት በፊት የሺሻ ዕቃውና አባሪው ቁሳቁስና ግብዓት የሚገኘው ዓላማው ኑሯቸው በሰመረላቸው ጥቂት ባለአዱኛዎች ቤት ውስጥ ብቻ ነበር። አሁን አሁን ግን የሺሻ ዕቃ /መደአ/ በአብዛኛው ሰው ቤት ውስጥ ይገኛል።

ሺሻ በሃይማኖት ደረጃ ሲታይ የሙስሊሙ ቁጥር የበዛ ይመስላል እንጂ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ተጠቃሚዎች ናቸው። በጾታ ደረጃ ሲታይ የወንዱ ቁጥር የሚበልጥ ሊመስለን ይችላል፤ ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ግን የሴት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከእጥፍ ድርብ በላይ ጨምሮ በተለይ የኢስላማዊ ከተሞች ሴቶች በአብዛኛው የሺሻ አጫሾች ሆነዋል። በቤተሰብ ቁጥጥር ስር ያሉትንና «እናጭስ» ቢሉ የእናት ግልምጫና የአባት ቁንጥጫ ለሚያሳስባቸው «የተጨቆኑ» ወጣት ሴቶች አመቺ ባለመሆኑ ይህን ችግራቸውን የተገነዘበላቸው እሳት የላሰ ነጋዴ «ለእነሱ ሲል» የሺሻ ማጨሻ ቤቶችን አዘጋጀላቸው። በኢስላማዊዉ ሸሪዓ ክልክል የሆነውን የወንዶችና የሴቶችን ተደባልቆ የመገኘትና አብሮ የመዋል ገደብ በሲሻ ምክንያት እየጣሰ በይፋና በድብቅ አገናኝቶ እንዲያጨሱና እንዲጫጫሱ ቦታና ሁኔታ አመቻችቶላቸዋል። እዚህም እዚያም።

በመካከለኛው ምስራቅና በአረቢያ ባህር ሰላጤ አካባቢ አገሮች በብዙ ብዙ ከተሞች ውስጥ ስትዘዋወሩ የምታዩት ይህንኑ ነው። በጣም ትገረማላችሁ! የት እንዳላችሁ ጭምር ግራ ይገባችኋል፤ እውነት እስላማዊ አገር ውስጥ ነው ያለሁት ያሰኛችኋል። የቁርዓንና የሃዲስ ትምህርት በሚሰጥበት፣ መስጊዶች መድረሻዎች እንደ አሸዋ በፈሉበት፣ ሙስሊም መሪዎች ባሉበት፣ ሙስሊም ልሂቃን /አሊሞዎች/ ጢማቸውን ያንዠረገጉና ሱሪያቸውን ያሳጠሩ ሙጠዋ ሙዕሚኖች ተቆጥረው በማያልቁበት አገር ውስጥ ያላችሁ ፈጽሞ አይመስላችሁም። የሺሻ ማጨሻ ቤቶች ብዛትም የወንድና የሴት አጫሾች መአት ሲታይ ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ መለየት እስኪሳነን ድረስ ግራ ያጋባናል፤ ግራ ያጋባቸው!

የሺሻ ሁኔታ ግራ አጋቢነት ጉዳዩ እንዲጠናና እንዲመረመር የሚያስገድድ በመሆኑ በርካታ ጥናቶች እየተካሄዱበት የሚገኝ አንድ የምርምር ዘርፍ እየሆነ ነው። እስካሁን የተገኙ የጥናት ሠነዶች ይፋ ለመሆን ያልተጠናቀቁ በመሆናቸው አንዳንድ የየአካባቢው ጋዜጦችና መጽሄቶች የየራሳቸውን ዘገባዎች ለማዘጋጀት ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጉዳዩ ዘልቀው ባይገቡም ለመረጃ ያህል ገረፍ ገረፍ እያደረጉ የሺሻን ጉዳይ ደባብሰውታል። ላይ ላዩንም ቢሆን ጥናት ካካሄዱ መጽሄቶች መካከል በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው «አል-ኡስራ» የሚባለው ነው።

አጥኚዎቹን በየአገሩ ልኮ በግብጽ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በባህሬን አሰማርቶ የሺሻን ነገር አስጠንቷል። ብዙዎቹ አገራት ሺሻ የሚጨስባቸውን ሻይ ቤቶች፣ ካፊቴሪያዎች ወይም ለዚሁ ተብለው በየግለሰቦች ቤቶች የተከፈቱ ክፍሎችን ለመቆጣጠር መንግስት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤት አላስገኘም። የሺሻ ዕቃዎችን /መደአ/ እና አባሪ ቁሳቁሶችን ከያሉበት እየለቀመ ቢያቀጥልም ሳምንት ሳይሞላው ሺሻው በእጥፍ ጨምሮ ይገኛል።

ልጆቹ ቀምሰውታል፣ አጣጥመው በሱስ ተጠምደዋል፣ ሴቶቹ መዋያና መደበሪያቸው አድርገውታል። በይፋ ቢከለከል በድብቅ ያገኙታል፣ መውጫ መግቢያውን አጥንተውታል። የአገባብና የአወጣጡን ስልት ተክነውበታል። እቤት ሲገቡ ወላጆቻቸው እንዳያውቁባቸው የማድረጊያውን ዘዴ ያውቁበታል። የተሻለ ዘዴ /ስልት/ ከሌለን በስተቀር የሺሻ ነገር አስቸጋሪ ነው።

በዚህ የሺሻ ባህር እንደ ግብጽ ወጣት ሴቶች እስከ አንገቱ የተነከረበት የዓለም ክፍል የለም፤ የግብጽ ወጣት ሴቶች ሥራ ያላቸውና የሌላቸው የኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ገና ለምንም የማይታሰቡ የሚመስሉ ህፃናት ሴቶች ሁሉ መዋያቸው በየሺሻ ቤቶች ውስጥ ነው። ያውም ከወንዶች ጋር ተቀላቅለው! በግብጽ የሚገኙ ሺሻ ቤቶች በዝነኛና ታዋቂ የፊልም ተዋንያን / አክተሮችና በታዋቂ ፊልሞች ስም የሚጠሩ ናቸው። «ለያሊ አል ሂልሚያህ» ፣ «በይነል ቀሲረይን»፣ «ሱከሪያህ»፣ «ቢንተ ሱልጣን» ... ወዘተ በመባል የሚታወቁ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሺሻ ቤቶች አሉ። « ቢንተ-ሱልጣን» በመባል የሚባለው ሺሻ ቤት /ካፌቴሪያ ፣ መቃሂ/ ባለቤቱ ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ሙስጠፋ ሁሴን ነው። በፊልም ሥራው ከፍተኛ ታዋቂነት ያለው አዲል ኢማም በፎቅ ቤቱ ሥራ /ግራውንድ/ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ተደባልቀው የሚርመሰመሱበት ሺሻ ቤት አለው። በተለይማ የንጉስ ፋይዘል ጐዳና የሚባለው አካባቢ ደግሞ የመሐንዲስ ሰፈር /ሃይ አል ሙሐንዲስ/ የሚባለው ሰፈር ከያለበት የመጣው የወጣት ሴቶች ሰራዊት ሺሻውን ሲጐትት የሚውልበት ቀውጢ ሰፈር ነው።

« አም አብዶ» የሚባለው ሺሻ ቤት ስመጥር የሚባሉት የፊልም አክተሮችና አዘጋጆች የሚበዙበት፣ ስለ ሥራቸው የሚያወሩበት፣ የሚደራደሩበትና ስምምነት የሚፈራረሙበት ሥፍራ በመሆኑ እነሱን ለማየት ከእነሱ ጋር ለመዋል ለመተዋወቅና ለመዳራት ወጣቱ የሴት ሰራዊት በግብረ ኃይል በግብር ኃይል እየሆነ የሚተምበት ነው። እዚሁ መሐንዲስ ሰፈር /ሃይ ኦል ሙሐንዲስ/ ውስጥ «መቅሃ ሁሴን» የሚባልና ሌሎችም ትላልቅ ሺሻ ቤቶች ሲኖሩ «ኦል-አራቢ» በተባለው ጉዳና ላይማ ህዝቡ መኖሪያ ቤቱን በሙሉ ወደ ሺሻ ቤቶች የቀየረ እስኪመስል ድረስ ብዛቱ እጅግ አስፈሪ ነው።

እነዚህ እንግዲህ ወንዱና ሴቱ በአንድ በር ገብቶ አንድ ላይ ተቀምጦ ሺሻ ሲምግ የሚውልባቸው ቤቶች ሲሆኑ፤ ሌሎች ደግሞ የሴቶችና የወንዶች በሮች የተለያዩ ሆነው ውስጥ ግን በአንድ ላይ ተደባልቀው የሚውሉባቸው «ጨዋ መሳይ» ሺሻ ቤቶች ናቸው። በማንኛውም ሃይማኖት ዘንድ በተጠላ አቀማመጥ ፊጽሞ ተቀባይነት በሌለውና ግብረገብነትን ባልተከተለ ሁኔታ ያለ ሀፍረት/ ሃያአ/ ሺሻ ሲጫጫሱ የሚውሉባቸው ሺሻ ቤቶች እጅግ በርካታ ናቸው። ስድ የፍቅርና የወሲብ ሙዚቃዎችና ቪዲዮዎች እየተላለፉ እንደ ልብ ይደመጣሉ፤ ይታያሉ።

ኃይለኛ ጉልበት ባላቸው / ሀርድ ኮር/ የወሲብ ፊልሞች ባህር ውስጥ ገና በጣም ህፃናት ሴቶችና የወጣትነት እድሜያቸው እንደ እሳት ያቀጣጠላቸው አፍላ ሴቶች በቅንዝር ስሜት ፊታቸው ቀልቶ ከንፈራቸው አብጦ ወንድ ለመምረጥ እንኳ ጊዜ ሳይኖራቸው ከማንም ጋር ምንም ሆነው የነገ ህይወታቸውን ዞር ብሎ ለማየት ፋታ በሚነሳ እብደት ውስጥ ወድቀው ይታያሉ። ልብ በሉ ባለጌ ዘፈን ለመስማትና ስድ የወሲብ ፊልም ለማየት ብላ የሄደች ወጣት የለችም፤ ሁሉም የሄዱት ሺሻ ፍለጋ ነው። ለሺሻ ብለው ነው ከወላጆቻቸውና ከጓደኞቻቸው ያዩትን ፊትለፊት ሊያጨሱ ያልደፈሩትን ሺሻ ፍለጋ ሄደው ነው ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያላዩትን ነገር አይተው ፈጣሪ በልባቸው ውስጥ ያኖረላቸውን የሀፍረት መከናነቢያ በገዛ እጃቸው ቀዳደው ጥለው የፈለጉትን ሆነው ወደቤት የሚመለሱት። አብዛኞቹ ሴቶች ሺሻ ያወቁት ወይም በንጥረ ነገሩ /ሙአሰል/ ሽታ ፍቅር ላይ የወደቁት ጓደኛዋን ተከትላ እሷን እያየች ጓደኛዋ እንድትወዳትና እንድታምናት የተለየ ቁርኝትና የጓደኝነት ምስጢር እንዲኖራት ወይም ሰለጠነች እንዲያስብላትና አሪፍ ለመሆን የቻለች እየመሰላት የገባችበት ነው፡፡

ለሺሻው ለራሱ ሲሉ ወይም ጓደኛቸውን ተከትለው ከሚሄዱት በተጨማሪ ሺሻው በአነስተኛ ገንዘብ መገኘቱንና አንድ ሺሻ አዝዘው ብዙ ሰዓት ተቀምጠው ለማሳለፍ ስለሚመቻቸው የሚሄዱ በርካታ ወጣት ሴቶች አሉ። ካፍቴሪያ ቢገቡ ለስላሳ መጠጥ፣ ጭማቂ ወይም ወተት ይዘው ስንት ሰዓት መቀመጥ ይቻላል? በዚህ ላይ የወሲብ ፊልም የለ! የብልግና ዘፈን የለ! እዚያ የሚታየው አልጀዚራ ብቻ ነው፡፡ እሱ ደግሞ ፖለቲካ ይበዛበታል፤ ቢከፍቱት የአለም ወሬ ነው! ስለሶሪያ ነው! ስለ ፍልስጤም ነው! መሪዎች መጡ ሄዱ ነው! ተፈራረሙ ነው! ይህ ለለጋዎቹ ወጣት ሴቶች አይመችም። ስለዚህ ይሄዳሉ! የት? ሺሻ ቤት፡፡

ግብፅን በምሳሌነት ጠቀሰን እንጂ ሺሻ ቤቶች በየሀገሩ እንደ አሸን ፈልተዋል፤ ኩዌት ብትሄዱ በተለይ ከሳዳም ወረራ ወዲህ ጉድ ነው፡፡ የካሊድ ጐዳና በሚባለው የከተማይቱ አካባቢ ብቅ ስትሉ ምድረ የኮሌጅ ተማሪ ሴት እንደ ጉድ ተገጥግጦ ሺሻውን በአፍ ለጉሞ ታገኙታላችሁ። ሴቱ ሥራ የለውም እንዴ? እስክትሉ ድረስ ትገረማላችሁ፡፡ ሺሻ የማታጨስ ወጣት ሴት ትገኛለች ወይ? ብላችሁ ራሳችሁን ለመጠየቅ ትገደዳላችሁ፡፡ ኩዌት ውስጥ ቤተሰብ መሃል ቴሌቪዥን እያዩ ጊዜ ለማሳለፍ እንኳ ሺሻ መኖር አለበት፡፡ እቤት ሺሻ! እውጭ ሺሻ! ታዳጊይቱ ልጅ ከሺሻ ማምለጫ ዘዴ የላትም ፡፡

በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የአካባቢው አሳ አስጋሪዎች እየተሰባሰቡ ወሬ ሲጠርቁ የሚውሉባቸው ሻይቤቶች (መቃሂ) ከዱሮ ጀምሮ መኖራቸው የታወቀ ነው። የመጀመሪያው ሻይ ቤት (መቃሂ) «ረኢስ አል ኸይመህ» ኢማራህ ውስጥ የተቋቋመው በ1956ነው፡፡ በዱባይ ኤምሬት (ኢማራህ-ዱባይ) የሺሻ ቤቶች ቀን ከሌሊት ክፍት ናቸው፡፡ ሻርጃ (ኢማራህ ሻሪቃህ) ሺሻ ማጨስ በ1990ዎቹ ገደማ ክልክል ነበር፡፡ ለነገሩ አቡዳቢና ዱባይም ከልክለው ነበር፤ ሺሻ ማጨስ የሚፈልጉ የሻርጃ (ሻሪቃህ) ሰዎች ወደ ዱባይ ኤሚሬት እየሄዱ ነው የሚያጨሱት። ሺሻ ለማጨስ ከሻርጃ ዱባይ ለመሄድ ከአምስት ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ ዱባይ ከየኤምሬቱና ከውጭ የሚመጣውን የሺሻ ሱሰኛ ሁሉ ታስተናግዳለች።

በአብዛኛው የሚጨሰው ሌሊት ሌሊት ላይ ነው። ዱባይ ውስጥ «ለሴቶች ብቻ» የሚባል ሺሻ ቤት የለም፡፡ ድንገት ዱባይ ከሄዳችሁ «ፈይሻዌ» እና «አል ሲብሲናህ» የሚባሉትን ሺሻ ቤቶች ሰላም በሉልኝ። ከሊባኖስና ከሶሪያ ጭምር የሚመጡ የሺሻ ሱሰኛ ሴቶች በሙሉ መቆሚያቸው እዚያ ነው፡፡ ባህሬን ደግሞ የባሰበት ነው፡፡ ሺሻ ቤቶች በሙሉ በወጣት ሴቶች ተወርረዋል፡፡ በውስጡ ካርታ አለ! ቼዝ አለ! ቁማር በቁማር ነው። የሴቶች በየሺሻ ቤት መገኘትና ማጨስ በሁሉም ሀገሮች ተቀባይነት የለውም ፡፡ ነገር ግን ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ መጀመሪያ ገደማ ገና ሲያቆጠቁጥ መቆጣጠር ስላልነበረ ዛሬ ከመንግስት አቅም በላይ ሆኗል፤ የህዝቡ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ የማይነቀል ሰንኮፍ ሆኗል።

ህብረተሰቡ አይወደው፣ ህጉ (ሸሪአው) አይፈቅደው፣ የሺሻ በሽታ «ሳይቃጠል በቅጠል» እንዲሉ ሺሻን አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ማስቆም ካልተቻለ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እኛም ከነአቡዳቢ፣ ዱባይ፣ ካይሮ፣ አሜሬት፣ ባህሬን ተርታ መሰለፋችን አይቀርም። ሺሻ የቤተሰብ የወጣቶች በተለይ የሴቶች ጠንቅ ነው። ሺሻ የእድገት፣ የልማት፣ የትምህርት፣ የፈጠራ ተነሳሽነት ጠንቅ ነው አጥብቀን ልንታገለው ይገባል። ነገ ሳይሆን ዛሬ! ዛሬ በቸልተኝነት የምናልፈው ይህ የሺሻ ሰይጣን ነገ የሁላችንንም በር እያንኳኳ ልጆቻችንን ሊነጥቀን ይመጣል። አትጠራጠሩ!
ግርማ ለማ  (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት )
 

No comments:

Post a Comment