Monday, November 20, 2017

አንድ ስንሆን እንጠነክራለን- ስንለያይ እንሰበራለን!

(ኅዳር  11, 2010, (አዲስ ዘመን))--አገራችን ኢትዮጵያ ልጆቿ ቀደም ሲል ጀምሮ በአትንኩኝ ባይነት ድንበሯን አስከብረው፣ እርስ በርሳቸው ተከባብረውና ተፋቅረው የሚኖሩባት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተከፈለላት መስዋዕትነት ሰላሟ በመረጋገጡ በዕድገት ጎዳና እየተራመደች ያለች አገር ናት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳ አብሮ ብዙ ነገር መናገር ይቻላል፡፡ ከረሃብ ምሳሌነት ወጥታ ዓለምን ባስደነቀ የልማት ጎዳና ግስጋሴዋ በአርዓያነት መጠቀሷ የሚያንጨረጭራቸው ጠላቶቿ ደህንነቷንና ሰላሟን ባይመኙላትም በጎውን የሚመኙላትና የሚወዷት ልጆቿ ግን ሁሌም እንደ ዓይናቸው ብሌን ይጠብቋታል፡፡

በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት ያሉ አክራሪና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በአገሪቱ እኩልነት፣ መከባበር፣ ሠላም፣ ልማት፣ ዕድገት፣ መረጋጋት የጠፋባትና የእርስ በርስ የፖለቲካ ግጭት ውስጥ የገባች አስመስለው ይስሏታል፡፡ የጎሣና በዘር ክፍፍል በመፍጠር የተጠመዱ ባላንጣዎቿ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው የኢትዮጵያን ጥፋት፤የዜጎቿን እልቂት ይመኛሉ፡፡ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ደግሞ ኃይላቸውን አስተባብረው በገንዘባቸው ቅጥረኞች ገዝተው እያሰማሩ በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የጥፋት ከበሮ ይደልቃሉ፡፡

ባለፈው ዓመት የሕዝብን ሰላም ለማናጋት በፈጠሩት ቀውስ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በጥፋት እንዲሳተፉ በመመልመልና በማሳተፍ ሕዝብን ለጉዳት ንብረትን ለጥፋት ዳርገዋል፡፡ መንግሥት የአገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅና በሕዝብ ሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ ስጋት ለመቀልበስ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

አንዳንድ ወገኖች «በአዋጁ ምክንያት ብዙ ሰው እየታሰረ ነው፤ በትክክል ወንጀለኞች ናቸው የተባሉት በሙሉ ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ነው የሚገኙት፤ የአዋጁ ጠቀሜታው ምን ድረስ ነው? ሰላምን ለማምጣትስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሲያነሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ የሕብረተሰቡን ሰላም ሲያናጉ የነበሩትን አደብ አስገዝቶ ጥፋተኞችንም የእጃቸውን አሰጥቶ ውጤታማነቱን አሳይቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በአኗኗር፣ በባህልና በመሳሰሉት እኩል ናቸው፡፡ ይህንን የአንድነት ልዩነት አክብረው አብረው ለመኖርና በጋራ ለማደግ የሚያስችሉ የጋራ እሴት አክብረው በመፈቃቀድ ላይ በተመሰረተ አንድነት በመኖር ላይ ሲሆኑ በሌላ ወገን ደግሞ የህዝቦችን በጋራ ተፋቅረውና ተማምነው መኖር የማይፈልጉት ጠላቶች የሃሰት ወሬ እያናፈሱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናቆር ሲታትሩ ይታያል፡፡ ለዚህም ማሳያ በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች አንዱ ብሄር በሌላው ላይ ጥቃት እንደፈጸመ አስመስለው አሉባልታ በማራገብ የእርስ በርስ እልቂት ሲናፍቁ ተስተውሏል፡፡ ህዝባችን ግን በተለመደ አስተዋይነቱና አርቆ አሳቢነቱ እነርሱ የጥፋት ኃይሎቹ የተመኙትና የወጠኑት እንዳይሳካላቸው አድርጎ አሳፍሯቸዋል።

ከሰሞኑ ከተለያዩ የኦሮሚያ ቦታዎች የተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ወጣቶች እንዲሁም የየክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ከአማራ ብሔረሰብ ወገኖቻቸው ጋር አንድ መሆናቸውን ለማሳየት ወደ አማራ ክልል በመጓዝና የምክክር ጉባዔ በማካሄድ ለከፋፋዮች ቦታ እንደሌላቸው ያስገነዘቡበት አኩሪ ተግባርም የሀገራችንን ጠላቶችን የእፍረት ካባ ያከናነበ ታላቅ ገድል ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን ዛሬ ሌሎች አገሮች ያጋጠማቸው የሰላም እጦት ፣ ያለመረጋጋትና የመበታተን አደጋ እንዲሁም በአሸባሪዎች የሚጠፋውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በተነፃፃሪነት በማየት ጥቅሙንና ጉዳቱን መዝነው በእጃቸው ያለውን የአገራቸውን ሰላም ከመንከባከብ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተገንዝበዋል፡፡

የሁሉ ቋንቋ፣ ባህል አንዳችም ቀዳዳ የለም። ሰሞኑን በአማራ ክልል የታየው የአንድነት መንፈስ በመላ አገሪቱ ላሉ ዜጎችም ሆነ በአገር ውጭ ላሉ ወገኖቻችን ያስተላለፈው መልዕክት እጅግ የላቀ በመሆኑ ይህንኑ አንድ የመሆን ምሳሌነት በማስፋት በሁሉም ክልል የሕዝቦችን አንድነት የሚያጎለብት ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም «አንድ ስንሆን እንጠነክራለን-ስንለያይ እንሰበራለን!» የሚለውን ብሂል ዛሬም እንደ ትናንቱ ተግባራዊ ልናደርገው ይገባልና!
አዲስ ዘመን

No comments:

Post a Comment