Wednesday, November 08, 2017

ልዑላኑን ያልለየው የፀረ -ሙስና ትግል

( ጥቅምት 29, (አዲስ ዘመን))--የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ወደ ስልጣን ከመጡ ብዙም አልቆዩም። ይሁንና በአብዛኞች ዘንድ የአመራር ክህሎትና አቋማቸው በእጅጉ እየተወደሰ ይገኛል። የ32 ዓመቱ ልዑል በተለይ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ስልጣን በያዙ ብዙም ሳይቆዩ በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣትና ዘመናዊት ሳውዲ አረቢያን እውን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ አገሪቱ ለውጥ ማሳያት ጀምራለች። ከዚህ ቀደም ስትከተለው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲና አመለካከት ቀይራለች፡

በልዑሉ አቋምና ውሳኔ በባህረ ሰላጤዋ አገር ከተደረጉ አበይት ለውጦች መካክልም በተለይ በኢኮኖሚ ፖሊሲው መስክ፤ አገሪቱ ለዘመናት ስትከተለው የነበረውን በነዳጅ ላይ መሠረትና ጥገኝነቱን ያደረገ የኢኮኖሚ ኡደት ብዙም ርቀት እንደማያስኬድ ታሳቢ በማድረግ የተቀረፀው አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም ቀዳሚ ሆኖ ይጠቀሳል።

በማህበራዊ ዘርፍ ደግሞ፤ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩና ስቴዲየም ገብተው ጨዋታ እንዳይከታተሉ ለዘመናት ሥራ ላይ አውላው የነበረውን ጨቋኝ ህገ ደንብ ሰርዛለች። ይህ ውሳኔም ለልዑሉም ይሁን ለአገሪቱ በተለይ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ አድናቆትን አዥጎድጉዶላቸዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የልዑሉ አቋምና ውሳኔ ካሳያቸው ለውጦች አንዱ የፀረ ሙስና ትግል ነው። የዓለማችን የነዳጅ ሀብት ማማ ተደርጋ በምትቆጠረው አገር የሕዝብ ሀብት በሙሰኞች ለጉድ ይዘረፋል። ሙስናም የበርካታ ወገኖች ዋነኛ የምሬትና የለቅሶ ምንጭ ነው። በርካታ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ምንም እንኳን በአገሪቱ መዋዕለ ነዋያቸውን ሥራ ላይ ለማዋል ፍላጎቱ ቢኖራቸውም የፈለጉትን እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆነው ይኸው ሙስና ነው። በርካታ ወገኖችም ከአገሪቱ እምቅ ሀብትና ከምታገኘው ገቢ አንፃር ሕዝቡም ሆነ ኢኮኖሚው በሚፈለገው ደረጃ ላይ ላለመድረሱ ሙስና ቀዳሚው ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

እናም ልዑሉ ስልጣን በተረከቡ በቀናት ልዩነት በአገሪቱ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በዋነኝነት ሊወገድ ይገባዋል ያሉት ነቀርሳ ሙስና ነው። ሰውየው በወቅቱ፤ «መንግሥታቸው በሙስና ወንጀልና ፈፃሚዎች ላይ ምንም ዓይነት ኀዘኔታ የለውም። ድርድር አያደርገም። የልዑል ቤተሰብም ሆነ ፖለቲከኛ፤ ነጋዴም ሆነ ማንም ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከመጠየቅ አያምልጥም ነበር» ያሉት። ይህ ንግግራቸው ደግሞ ቃል ብቻ አልነበረም። ሰውየው ወደ ተግባር ለመቀየርም ብዙም ጊዜ አልወሰዱም። የሙስና ወንጀል ከአገሪቱ ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ዓላማው ያደረገ በእርሳቸው የሚመራ አዲስ የፀረ ሙስና ኮሚቴ አዋቀሩ።

በ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን የሚመራው ይህ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ይፋ መሆኑን ተከትሎም ከሰሞኑ በርካታ ልዑሎች፤ የመከላከያ አመራር አባላት፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ የንግድ ሰዎች እንዲሁም ክፍተኛ የመንግሥት ሹማምንቶች በሙስና ተግባር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ኮሚቴውም ካሳለፍነው ቅዳሜ አንስቶ በጀመረው ንቅናቄ እስካሁን 49 ግለሰቦችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከልም 11 ልዑሎች፣ አራት ከፍተኛ ሚኒስትሮችና አስር ቀደም ሲል አገሪቱን በተለያዩ የሚኒስትርነት ማዕረግ ያገለገሉ ግለሰቦች ይገኙበታል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት 11 ልዑሎች ውስጥም በእንግሊዝ ለንደን «ሳቭዌይ» የተሰኘ እጅግ ዘመናዊ ሆቴል ባለቤት የሆኑትና በአፕልና ትዊተር ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውና ጠቅላላ ሀብታቸውም ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ የሚነገርላቸው መልቲ ቢሊየነሩ ልዑል አልዋሌድ ቢን ታላል ይገኙበታል።

የቀድሞ የፋይናንስ ሚኒስትር ኢብራሂም አልሳፍ፣ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አዴል ፋኪህ፣ የቀድሞ የሪያድ አስተዳዳሪ ልዑል ቱርኪ ቢን አብደላህ፣ የኤም ቢሲ ቴሌቪዥን ባለቤቱ አልዋድ አል ኢብራሂም፤ የሳዑዲ ቢንላዲን የኮንስትራክሽን ኩባንያ የበላይ ኃላፊ ባከር ቢን ላዲን እንዲሁም የቀድሞ የንጉሣውያን ችሎት ኃላፊ ካሊድ አልቱዋጂ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አዲስ የተቋቋመው ይህ የጸረ ሙስና አካል በሙስና የተጠረጠሩ ማናቸውንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል የእስር ማዘዣ የማውጣትና የጉዞ እገዳ የማድረግ ስልጣንም ተሰጥቶታል፡፡ እንደ መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባም በሙስና ወንጀል ተጠርጠረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ሁሉም ለየብቻቸው በተለየ ሁኔታ በእስር ላይ ይገኛሉ።

አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት ምን ይህን ይህን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጡ በሚል መሆኑ ታውቃል። ይሁንና አንዳንዶች ከፖለቲካ ጋር እያስተሳሰሩት ይገኛል። የፀረ ሙስና ትግሉ የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል ተክትሎ የአገሪቱ መንግሥት እንዳስታወቀው፤ የፀረ ሙስና ትግሉ ዋንኛ ዓላማ ግልፅነት፤ ተጠያቂነት፤ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው።

የአልጋ ወራሹ መሰል ተግባር በተለይ ከኢኮኖሚ ልዕልናዋ በተጓዳኝ ዘመናዊት ሳውዲ አረቢያን በመፍጠሩ ሂደት በበርካታ ወጣት የሳዑዲ ዜጎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው። አገሪቱን ለመለወጥ የገቡትን ቃል ለመጠበቃቸው ማረጋገጫ እንደሰጠ ብዙዎች መናገር ጀምረዋል። የአገሪቱ መንግሥት የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ በርካታ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ እንዲጎርፉ ምክንያት እንደሚሆን ታምኖበታል። ልዑላኑን ያልለየው የፀረ ሙስና ትግል ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደናቂ ሆኗል።

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ልዑሉ ወደ ስልጣን ከመጡ ብዙም ባይቆዩም፤ ለውሳኔዎች እጅግ ፈጥነዋል እናም በተረጋጋና በበሰለ መንገድ አካሄዳቸውን መፈተሽ አለባቸው ሲሉም አስተያየታቸው ሰጥተዋል። በተለይ ከየመንና ከዋነኛ ጎረቤቷ ኳታር ጋር ያለውን ቁርሾ በሰከነ መንገድ ማሰብ እንዳለባቸው ምክር አዘል አስተያየት ሲሰጡ ተስተውለዋል። ዘገባው የቢቢሲ፤የአሶሽዬትድ ፕሬስ እና ሲ ኤን ኤን ነው።
ታምራት ተስፋዬ (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment