Tuesday, October 31, 2017

የኦሮሞ ወጣቶች የመጣላችሁንና የመጣባችሁን ለዩ

( ጥቅምት 23, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--ኦሮሚያ በ2008 ዓ.ም አብዛኞቹን ወራት በአመዛኙ ወጣቶች የተሳተፉባቸው የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን እናስታውሳለን። የእነዚህ የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ በተለይ በመሬት ዝርፊያ የተገለፀ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ነበር። በከተሞች መስፋፋት፣ በመሰረተ ልማት መስፋፋት እንዲሁም በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ምክንያት ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ተገቢውን ማካካሻ አለማግኘት፣ የወጣቶች የልማት ተሳታፊ አለመሆንና በአገሪቱና በክልሉ ከሚመዘገበው ዕድገት ተጠቃሚነት ማጣትም ተቃውሞዎቹን የቀሰቀሱ ምክንያቶች ነበሩ።

የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት፣ በእነዚህ ተቃውሞዎች የተነሱትን ጥያቄዎች በተገቢነት ተቀብለዋል። በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ችግር መኖሩን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አስቀድሞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አቋም የያዘበት ጉዳይ በመሆኑ እንደችግር መቀበል አልከበደውም። በተለይ በ2007 ማብቂያ ላይ በተካሄደው 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የህልውና ጉዳይ መሆኑን፣ የሞት ሽረት ትግል ሊካሄድበት እንደሚገባም ተወስኖ እንደነበረ እናስታውሳለን። ኢህአዴግ በዚህ ድርጅታዊ ጉባዔው ባሳለፈው የአቋም መግለጫ፤ 9 ነጥቦችን ይዟል። በአንደኛው ነጥብ ላይ፤

. . .የብዙዎቹ ችግሮቻችን ዋነኛ መንስኤና ምንጭ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጋር የተያያዘ መሆኑን የተመለከተው ጉባኤያችን በቀጣይ ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ሆነው የተለዩትን የመሬት፣ የግብር አሰባሰብ የመንግሥት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አስምሮበታል። በመሆኑም እኛ የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንዲጎለብቱ የፀረ- ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ለመረባረብ ቃል እንገባለን። በሚል ተገልፆ ነበር። በተመሳሳይ የአቋም መግለጫው 9ኛው ነጥብ፤

. . . የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ እየተዳከመ ባለመሄዱ ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጣችን የሚፈለገውን ለውጥ ህዝባዊ እርካታ ለመረጋገጥ እንዳልተቻለ፣ ህዝባችንን ቅሬታ ውስጥ የሚያስገቡና የልማታችን እንቅፋት የሆኑ አድሎአዊ አሠራሮች የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት እንዲሁም ሙስናን የመሳሰሉ ብልሹ አሠራሮች እንዳሉ ጉባዔያችን በአጽንኦት አይቷል። በመሆኑም እኛ የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የድርጅታችን ህዝባዊ መርሆዎችና አሠራሮች እንዲከበሩና የህዝቡን ተሳትፎና ባለቤትነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን በመያዝና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በምርጫ ያከበረንና ችግሮቻችን እኛው እንደምንፈታ በማመንና ግልፅ መልዕክት በማስተላለፍ በድጋሚ እንድንመራው ፈቃድ የሰጠንን የአገራችንን አስተዋይና አርቆ አሳቢ ህዝብ፤ በጠንካራ የተቋማት ግንባታ፣ በግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ለማገልገል በድርጅታችን ፀንቶ የቆየውን የውስጥ ድርጅት ትግል በማቀጣጠልና ህዝቡን በተደራጀ አግባብ በማሳተፍ በመልካም ኣስተዳደር ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቃል እንገባለን። በሚል ተገልጿል።

ይህ የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረውን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድን) ጨምሮ ኢህአዴግ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደልና የሚያስከትሉት ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል መዛባት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወዘተ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በ2008 ዓ.ም ሁከቶች ከመቀስቀሳቸው አስቀድሞ ተገንዝቦ እንደነበረ ያመለክታል። ችግሮቹ መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ህዝብን ማስከፋታቸውንም በሚገባ ተረድቶ እንደነበረ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ሥጋቱን ገልፆ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ህዝባዊ ንቅናቄ ለመጀመር ሲዘጋጅ ነበር በኦሮሚያ ተቃውሞው ድንገት የፈነዳው። ኦህዴድ/ ኢህአዴግ ህዝብ ለተቃውሞ እንዲወጣ ያደረገው ችግር ትክክል መሆኑን አምኖ ችግሩን ለማስተካከል ዳግም ቃል ገባ። የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግርን በማቃለል የህዝብ እርካታ ለመፍጠር በድርጅቱና በመንግሥት ውስጥ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ጀመረ።

አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የተሃድሶው አመራር ነው። የተሃድሶው አመራር በ2009 ዓ.ም ኃላፊነት ከተረከበ በኋላ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመጠራረግ ባደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በመሬት ወረራ፣ በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን እንዲሁም በኢንቨስትመንት ስም ተይዘው ሳይለሙ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ቀድሞ ባለመሬቱ ለነበረው አርሶ አደሮችና ለከተማ ሥራ አጦች በመስጠት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። በመሬት ወረራ ውስጥ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ላይ እርምጃ ወስዷል።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተፈጥሮ የተቸረን የማዕድን ሀብት፣ አንዳችም ተጨማሪ እሴት ሳያክሉበት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ተግባር ሳያከናውኑ እየዛቁ ከበለፀጉ ባለሀብቶች ላይ በመንጠቅ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሠሩበት አድርጓል። በከተሞች መስፋፋትና በልማት ሰበብ ከቦታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮች መብቶችን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።

ተጀምረው ያለአግባብ የተጓተቱና የተቋረጡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተቋማትን ለማስጨረስ የሚቻለውን ያህል ተፍጨርጭሯል። የተሃድሶው አመራር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁሉም የህዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽና መፍትሄ ማስገኘት ባይችልም፣ ለህዝብ ጥቅምና እርካታ የቆመ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ለጥያቄዎቹና ለቅሬታዎቹ ምላሽ መስጠቱ አይቀሬ መሆኑን ህዝብ አምኖ እስኪቀበል ደረስ የለውጥና ልማት አመራር መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል። አሁን በህዝቡና በክልሉ መንግሥት መካከል የሚታየው መተማመን ለዚህ አስረጂ ነው።

ይሁን እንጂ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰበቦች እየተፈለጉ ህገወጥ አድማዎችና ሁከቶች እንዲቀሰቀሱ የማድረጉ ሙከራ አልተቋረጠም። በተለይ ነሐሴ፣ 2009 ዓ.ም የነጋዴዎችን የዕለት ገቢ ግመታ መነሻ በማድረግ ጃዋር መሃመድ በተባለ ግለሰብ፣ አገር ውስጥ ባሰማራቸው ቅጥረኞች አማካኝነት ነጋዴውን በማስፈራራት ሱቆች እንዲዘጉ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ለማድረግ መሞከሩን እናስታውሳለን። ይህ በጥቂት ከተሞች ውስጥ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረ አድማ በህዝቡ ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻሉ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክሮ ተቋርጧል። ልብ በሉ፤ ነጋዴው ማህበረሰብ በገቢ ግምቱና ከዚህ በመነሳት የሚወሰንበት ግብር ላይ ቅሬታ ካለው ይግባኝ የሚልበት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚዘልቅ ሥርዓት ተቀምጦ ነበር። የተሃድሶው አመራር ደግሞ የነጋዴው ማህበረሰብ ቅሬታ እንዲሰማ የማድረግ ቁርጠኝነቱ ነበረው። ይህን ችላ በማለት የተሞከረው አድማ በኦሮሞ ህዝብ ጉዳት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትን ዓላማው ያደረገ ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ አውዳሚ ሁከቶች እየተቀሰቀሱ ነው። የተሃድሶው አመራር ለኦሮሚያ ህዝብ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን በየአቅጣጫው ጥረት በሚያደርግበትና ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ባለበት ወቅት፣ በተለይ ለወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በሚማስንበት፣ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘና ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋ ሰጪ በሆነበት ወቅት የተቀሰቀሰ ሁከት መሆኑን ከበፊቶቹ ልዩ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ክልሉ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ድንበርን ሰበብ በማድረግ በኦሮሞዎች ላይ ግድያ መፈፀሙን እንዲሁም እስከ ግማሽ ሚሊየን የሚደርሱ ኦሮሞዎች ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መፈናቀላቸውን ተከትሎ ኦሮሞዎች ከዳር እስከ ዳር አንድነታቸውን አጠናክረው ወገኖቻቸውን ለመርዳት በተነሱበት ማግስት የተቀሰቀሰ ሁከት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ሰልፎች፣ በህዝብ ሀብት ላይ ውድመትና ግድያዎች የሚፈጸምባቸው ሁከቶች በይፋ ባለቤት የላቸውም። በአውዳሚዎቹ ሁከቶች ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች የተሃድሶው አመራር ምላሽ ለመስጠት እየተረባረበ ከሚገኝባቸው የህዝብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን ጥያቄዎችና ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ያልተሸፈነ ምንም አጀንዳ የላቸውም። ጥቃት እየሰነዘሩባቸው የሚገኙት ዜጎችም ከመንግሥት አስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንፁህ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በኦሮሞዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተፅዕኖ ለመከላከልና ችግሩ በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኝ ለማድረግ የኦሮሞ ህዝብ ከዳር እስከዳር አንድ ሆኖ ከክልሉ መንግሥት የተሃድሶ አመራር ጋር በአንድ አፍ በሚናገርበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑም መታወቅ አለበት።

የአደባባይ ተቃዋሚዎቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ አስመልክቶ የክልሉን መንግሥት በድክመት መጠየቅ ወይም መውቀስ የሚያስችላቸው ምንም አጀንዳ የላቸውም። ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተካሄዱት አውዳሚ የተቃውሞ ሁከቶች በአገር ሽማግሌዎችና በወጣቶች (ፎሌዎች) የተወገዙት ናቸው። እና ይህን የሁከት እንቅስቃሴ የሚመራው ማን ይሆን? አላማውስ ምን ይሆን?

በተለይ ድንበርን ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች ላይ የተፈፀመው በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በኦሮሞዎች ዘንድ የፈጠረው አንድነት፣ በክልሉ መንግሥትና ህዝብ መሃከል የፈጠረው መግባባት ያስደነገጣቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ። ከውጪ ሆኖ ይህን የኦሮሞዎች አንድነት ማፍረስ እንደማይቻል ያውቁታል።

 እናም ጥቂት የሁከት ተልዕኮ አስፈፃሚዎችን አስርጎ በማስገባት የግንዛቤ ጉድለት ያለባቸውን የኦሮሞ ወጣቶች በማነሳሳት የኦሮሞዎችን አንድነት እንዲያፈርሱ የማድረግ ተልዕኮ ሰጥተው የቀሰቀሱት ሁከት ነው። በሌላ በኩል የክልሉ መንግሥት በተለይ በመሬት ወራሪዎች፣ የማዕድን ሀብት በመዛቅ ያለአግባብ የበለፀጉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ወስዷል። በቀጣይም የመሬት ወረራ ሊካሄድ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘግቷል። የመሬት ወረራን የመከላከል ጉዳይ የህዝብ የሚሆንበትን ሥርዓት አመቻችቷል። እንደልብ ሲዘረፍ የነበረው የኦሮሚያን መሬት ካሁን በኋላ የማይቀመስ ሆኗል።

ይህ ብቻ አይደለም። የክልሉ ህዝብና መንግሥት ከክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎች በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶችን፣ ዶላርን ጨምሮ ከአገር የሚወጡ የውጭ ምንዛሪዎችንና ምርቶችን አላንቀሳቅስ ብሏል። ይህ ሁኔታ እነዚህን ዘራፊዎች አበሳጭቷል። በመሆኑም በየአካባቢው ሁከት በመቀስቀስ ትኩረቱን መበተንና የቁጥጥር አቅሙን ማዳከም፣ ክልሉ በሁከትና ግርግር የሕግ የበላይነት ሊረጋጋጥ የማይችልበት የሥጋት ቀጣና እንዲሆን የማድረግ ፍላጎት አላቸው። ይህን ማድረግ የሚያስችለው አይነተኛው መንገድ ደግሞ የዋህ የኦሮሞ ወጣቶችን ለሁከት በማነሳሳት ክልሉን የግርግርና የሕግ የበላይነት የማይከበርበት ቀጣና ማድረግ ነው።

የሰሞኑ የግድያና ንብረት የማውደም ተግባር የሚፈፀምበት ሁከት ምንጭና ዓላማ ይሄው ነው። እናም የኦሮሞ ወጣቶች በራሳቸው ላይ የመጡ ቡድኖች መሣሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው። መንግሥት ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል የሚሏቸው ጥያቄዎች እንኳን ቢኖሩ፣ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንጂ በስሜታዊነት የሌሎች መሣሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው። የኦሮሞ ወጣቶች የመጣላችሁንና የመጣባችሁን ለዩ።
ኢብሳ ነመራ ((አዲስ ዘመን)
 

No comments:

Post a Comment