Friday, October 27, 2017

ኢትዮጵያውያን መማር ያለብን ከራሳችን ስህተት ሳይሆን ችግር ከደረሰባቸው አገራት ቢሆን ብልህነት ነው

( ጥቅምት 20, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--በየትኛውም ስፍራ ያሉ በጥላቻ የተሞሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በአገር ውስጥ አንዱ ካንዱ ጋር ሲጋጭ ዳንኪራ ይረግጣሉ፡፡ ሱማሌ ኦሮሞን፣ ኦሮሞ አማራን እንደጨፈጨፈ፣ የብሔር ግጭት እንደተጀመረ፣ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንደተጣላ፣ በመንግስት ላይ እንዳመፀ አስመስለው ያራግባሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ መንስዔው ሕዝብ የመንግስትን አገዛዝ ባለመፈለጉ እንደሆነም ለማሳየት ይሞክራሉ፤ ይህ ግን የእነርሱ ህልም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ከልማትና ከዕድገት ካገኙዋቸው መልካም ቱርፋቶች ባሻገር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ በፖለቲካው መስክ ያስገኘው ውጤት በዋናነት የሚጠቀስ ይሆናል።

ማንም ያሻውን ይበል እንጂ የሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝቦች መብት የተከበረባት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ በልማት እየገሰገሰች ያለች፣ ዜጎች ተዋድደውና ተፋቅረው የሚኖሩባት አገርን መፍጠር ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት፣ በሥልጣኔ ማማ ላይ የምትገኝ እንጂ፤ በዚህ ዘመን በየትኛውም ጫፍ ያሉ አክራሪና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እንደሚያራምዱት እኩልነት፣ መከባበር፣ ሠላም፣ ልማት፣ ዕድገት፣ መረጋጋት፣ የጠፋባትና የእርስ በርስ የፖለቲካ ግጭት ውስጥ የገባች እንዳልሆነች በግልፅ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በጎሣና በዘር ቅራኔ በመፍጠር የተጠመዱ አክራሪ ተቃዋሚዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው የኢትዮጵያን ጥፋት የዜጎቿን እልቂት ይናፍቃሉ፡፡ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ደግሞ ያለ የሌለ ሃይላቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡ የጥፋት ዓላማቸውን ለማስፈፀምም ወጣቶችን በተለያዩ መንገዶች እየደለሉ ለጊዜውም ቢሆን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ የለየላቸው የአገሪቱ ጠላቶች በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃንና የክልል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የተጣለባቸውን የዜግነት ግዴታና ለህብረተሰብ ደህንነት የማሰብ የሞራል ኃላፊነት በመዘንጋት ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ተግባር ተሰልፈው የጥፋት መልዕክተኛ ሲሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡

ሰሞኑን በሶማሌ ክልልና በበደሌ አካባቢ የተነሱ ግጭቶችን ምክንያት በማድረግ መረጃ ለህዝብ እናደርሳለን በሚል በአይናቸው ያላዩትንና በተጨባጭ መረጃ ያላረጋገጡትን በሰበር ዜና ሲያሰራጩ አድምጠናል፤ ተመልክተናል፡፡

ይህንን መሰሉ ተግባር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የግል መገናኛ ብዙሃን እንደ አሸን በፈሉበት ዘመን ለሃያ አምስት ሳንቲም የጋዜጣ ትርፍ ትልቅ የአገር ምስጢር ሲያባክኑ፣ መንግስትን ሲያዋርዱ፣ ግለሰቦችን መብታቸውን ሲጥሱ፣ ሽብርተኝነትን ሲያራምዱ፣ የአገሪቱን እድገት ሲያንኳስሱ፣ ለህብረተሰቡ መልካም ኑሮ ተቃራኒ የሆኑ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከርመው ህብረተሰቡ እንደማይጠቅሙት ተረድቶ አንቅሮ ሲተፋቸው በራሳቸው ጊዜ ሲጠፉ ታይቷል፡፡

የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጭ ከአንድ ቦታ ሊቀዳ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም እንኳ በአንድ ቦታ የተከናወነ ድርጊት ስለ ትክክለኛነቱ ተገቢ ማጣራት ተደርጎበትና ተአማኒነቱ ተረጋግጦ፣ ለአገርና ለህብረተሰቡ ያለው ጠቀሜታ እንዲሁም ለሕብረተሰብ በሰላም የመኖር የሚያበረክተው ፋይዳ ተመዝኖ መሰራጨት ሲገባው ለወሬ በመሽቀዳደም ሀሰተኛ ዘገባ ማስተላለፍ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የመተላለቅ ጥሪን እንደመጋበዝ ይቆጠራል፡፡

በአፍሪካ በተለይም በሩዋንዳ በሁለት ጎሳዎች መተላለቅ ከስምንት መቶ ሺ በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋት መነሻ የሆነው መገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ቅስቀሳ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን ችግርን መማር ያለብን ከራሳችን ስህተት ሳይሆን ስህተት ውስጥ ገብተው ችግር ከደረሰባቸው አገራት ቢሆን ብልህነት ነው፡፡

ዛሬ ሰላም በሰፈነባት ኢትዮጵያ ካለምንም ስጋት በደህንነት ሰርተው እየኖሩ፤ የሰላምንና የገንዘብን ጥቅም ለይቶ ማወቅ ተስኗቸው ለአገሪቱ ብጥብጥን የሚመኙ አያድርገውና አንድ ቀን ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የወጣ ነገር ቢኖር ውለው ለማደራቸው እንኳ ዋስትና የላቸውም፡፡ በውጭ በዴሞክራሲ አገር ያሉ ፅንፈኛ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መላ ቤተሰባቸውን ሳይቀር በጉያቸው ሸሽገው በሰላም እየኖሩ ተበጣበጡ እያሉ የሚቀሰቅሱት ወላፈኑ አያገኘንም ብለው አስበው ይሆናል፤ ነገር ግን ያሰቡት በእነርሱ የጠበበ አእምሮ ልክ እንጂ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርቆ አሳቢነት ልክ ባለመሆኑ መላው ሕዝብ አብሮ ከኖረው፣በሃይማኖት፣በጋብቻና በባህል ከተሳሰረው ወገኖቹ ለመተላለቅ የሚነሳበት ምክንያት አይኖረውም፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም በመረጃ ማሰራጨት መብት ሰበብ ጫፍ የያዘ ወሬ አንጠልጥሎ ከመሮጥ ለሕዝብ የሰላምና አብሮ መኖር ጠንቅ የሆኑ ዘገባዎች ጠቀሜታቸው ተመዝኖ መተላለፍ ወይም ማስቀረት እንዳለባቸው በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ሙያው ከሚፈቅደው ስነ-ምግባር ውጭ የተሳሳተና ያልተጣራ መረጃ በማሰራጨትም የአገሪቱ ተጨባጭ እውነታ ላይ ጥላሸት እየቀቡ ትክክለኛውን ምስል ማበላሸት፣ ጉዳትን መጋበዝ እንጂ በዚህ አይነቱ የተጋነነ ዘገባ መገናኛ ብዙሃኑም ሕዝብም አይጠቀሙም፡፡

ሕዝብ ዛሬ ሌሎች አገሮች ያላቸው የሰላም እጦት፣ ያለመረጋጋትና መበታተን ሁኔታን በተነፃፃሪነት በማየት ጥቅሙንና ጉዳቱን የሚመዝንበት አእምሮ አለው፡፡ በእጁ ያለውን ሰላም አጥፍቶ ጦርነት የሚመኝበት ፍላጎት አይኖረውም፡፡ የውጭ ቅጥረኛ የሆኑት የሰላም ጠንቆችም በአጋጣሚ የሚፈፅሙት የጥፋት ተግባር ወገናቸውን የሚጎዳ፣ አገራቸውን ወደ ድህነት የሚመልስ መሆኑን ተረድተው ወደ መልካምነት ሊመለሱ ይገባል፡፡
 (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment