Sunday, October 22, 2017

የብር ዋጋ መውረድና የወጪ ንግዱ መንታ ገጽታ

( ጥቅምት 10, (አዲስ ዘመን, ዜና ትንታኔ))--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቅምት 1 ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ የብር ዶላርን የመግዛት ዋጋን በ15 በመቶ ዝቅ ያደረገ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም አንድ ዶላር ይመነዘርበት የነበረው 23 ነጥብ 41 ብር ወደ 26 ነጥብ 93 ብር ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡ ይህም ለአገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ዕድል እንደሚከፍትና የውጭ ባለሀብቶችን ወደ አገር ውስጥ በመሳብ ለማልማት እንደሚያበረታታ በርካቶች ይናገራሉ፡፡

የወጪ ንግዱ ማደግ ያልቻለው በቂና ጥራት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ውስን ምርቶች ብቻ መላካቸው፣ መዳረሻ አገራትን ማስፋት ባለመቻሉ እንጂ የምንዛሪ ዋጋ ዝቅ በማለቱ ብቻ አለመሆኑንም በርካቶች ይገልጻሉ፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በፊስካል ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት የፊስካል ፖሊሲ ጥናት ቡድን መሪ አቶ ፍሬህይወት ሀንዳሞ እንደሚሉት፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች መታየት ያለባቸው አጠቃላይ ፋይዳቸው ሲሆን፤ ብር ዶላርን የመግዛት ዋጋው በ15 በመቶ እንዲወርድ መደረጉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተዳከመውን የወጪ ንግድ የሚያነቃቃበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አገሪቱ እያስፋፋችው በምትገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ ያደርጋል፡፡ ይህም ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ጎብኚዎች ጥቂት ዶላር ይዘው መግባት እንዲችሉ ስለሚያደርግ ቱሪዝሙን ከመደገፍ አኳያም የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት እ.አ.አ. 2017 መጨረሻ የዓለም ኢኮኖሚ የ3 ነጥብ 6 እንዲሁም በ2018 እ.አ.አ. የ3 ነጥብ 7 የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ አስቀ ምጧል፡፡ ይህም የወጪ ንግዱ እንዲበረታታና ላኪ አገራት ምርቶቻቸውን በብዛት እንዲልኩ ዕድል ስለሚፈጥር ይህን ለመጠቀም የምንዛሪ መጨመር ባለሀብቶች የተለያዩ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ በማምረት እንዲልኩ ስለሚያስችል አዎንታዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ ፍሬህይወት አብራርተው፤ በዚህ ረገድ አገሪቱ ምርቶችን ማምረት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መገንባቷና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ታሳቢ የተደረጉ መሆኑ ከዓለም ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል በወሳኝ ወቅት ላይ የተደረገ ጭማሪ መሆኑን ያመላክታል ይላሉ፡፡

የብር ዋጋ መውረድ ከፊሲካል ፖሊሲ አንጻር ደግሞ ከአገራዊ ምርት ድርሻ፣ ከአገር ውስጥ ገቢና ወደ ውጭ ከሚላከው ምርት አኳያ ሊመዘን ስለሚችል የብድር ጫናን ይቀንሳል የሚሉት ባለሙያው፤ በጥንቃቄ ካልተያዘ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡ ይህም የኑሮ ውድነቱ በመጨመር በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የምንዛሪ መጨመር ለሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግብዓቶች ዋጋ ላይ መጠነኛ ለውጦችን ስለሚያስከትል መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ ካልቻለ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡

የምንዛሪ ዋጋን ከፍ ማድረግ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል ቢችልም በከፍተኛ የዋጋ ንረት ኢኮኖሚያዊ ግሽበትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነጥቦች ግን ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለአብነት የነዳጅ ዋጋና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሌሎች ግብዓቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ውድ መሆን የምንዛሬ መጨመርን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ ግሽበትን ይፈጥራሉ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች አገሪቱ የምታስገባቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው እንደመሆናቸው የሚፈጠረው የዋጋ ንረት ጤናማ ነው የሚሆነው በማለትም አቶ ፍሬህይወት ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ፍሬህይወት ገለጻ፤ በአገር ደረጃ ነጋዴው ህብረተሰብ አንዳንድ ሸቀጦችን ወደፊት ሊወደዱ ይችላሉ በሚል እሳቤ ከገበያ እንደጠፉ በማስመሰል የሚደብቅበትና በውድ ዋጋ ለመሸጥ የሚሞክርበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል ይህን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ከምግብ ጋር በተያያዘ ግን መጪው ጊዜ መኸር እንደመሆኑ የሚያሰጋ ነገር አይኖርም፡፡ ሆኖም ዋጋን መከታተል፣ የብር እንቅስቃሴን መመጠንና ቁጠባን በወለድ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ተክኤ አለሙ፤ የአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ የሚቀንሰውና የሚጨምረው የብር ምንዛሪ ዋጋን በመቀነስ ብቻ አይደለም፡፡ ከዶላር ምንዛሪ አንጻር የብር ዋጋ መውረዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ በመጨመር የሰው ፍላጎት እንዲቀንስና በአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም ቢያደርግም የወጪ ንግዱን ለማሻሻል ግን ብቸኛ አማራጭ አይደለም፡፡ ውጤቱም በአጭር ጊዜ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም የወጪ ንግዱን ለማሻሻል ከምንዛሪ ዋጋ መጨመር ባሻገር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በብዛት ማምረትና ጥራታቸውን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

«የወጪ ንግዱ እንዲቀዛቀዝ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ምርቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን በተሻለ ጥራት መላክ አለመቻሉና እሴት ያልተጨመረበት መሆኑ ነው፡፡ ይህም መዳረሻ አገራትን ለማስፋት እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ለአብነት ወደ አውሮፓ አገራት ለመላክ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ የምንዛሪ ለውጡ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ መሰረታዊ አይሆንም» በማለት ዶክተር ተክኤ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዶክተር ተክኤ ማብራሪያ፤ የብር ዋጋ መውረድ ለአገር ውስጥ አምራቾች ብዙ ብር እንዲያገኙ ቢያደርግም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን አገር ውስጥ በማምረት መጠቀም እስካልተቻለ ድረስ የንግድ ሚዛኑ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም የገቢ ንግዱን ለመቀነስ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ በስፋት የሚመረቱበትና ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውሉበት አግባብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት ሪፖርት በአገሪቱ ላለፉት ዓመታት የወጪ ንግዱ አፈጻጸም የተቀዛቀዘበት ምክንያት በምርት ጥራት ጉድለት፣ በቂ የሆነ ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ያለመቻል፣ በውስን ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ መዳረሻ አገራትን አለማስፋት በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደነበሩ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የአገሪቱ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው እየቀነሰ መምጣቱ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ምክንያት በመሆኑ በወጪና ገቢ ንግድ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብና የወጪ ንግዱን ለማሳደግ የምንዛሪ ለውጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ፤ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ከምንዛሪ ማሳደግ ባሻገር በምርት ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ፣ እሴት የተጨመረበትና በቂ የሆነ ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ፣ በአገር ውስጥ ምርቶች መጠቀም፣ የምርቶችን ስብጥር ማብዛት እንዲሁም መዳረሻ አገራትን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
ዑመር እንድሪስ  (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment