Thursday, October 20, 2016

በረጅሙ የግብፅ እጅ አንጠምዘዝ

(ጥቅምት 10, 2009, (አዲስ ዘመን ))በኦሮሞዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት የሚከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በአል ታሪክ የማይረሳ አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሞታል። በመሆኑም፣ በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ሳይከናወን ቀርቷል።

ይህ የሆነው ታላቁን የኢሬቻ በዓል ሁነት ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም ባሰቡ የሽብር ቡድን አባላት ነው። ይህ የኢሬቻን በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክንውን የጠለፈው ቡድን ኢ- ሰብአዊ እርምጃን የወሰደው በድንገት ሳይሆን በከፍተኛ ምስጢር፣ ውስጥ ለውስጥ ሲዘጋጅ ቆይቶ በታቀደና በተደራጀ አኳኋን መሆኑ ግልፅ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አዋኪው ቡድን ረብጣ ዶላር የሚሸቅልበትን አስከሬን ለማግኘት መልካም አጋጣሚ የመፍጠር ዓላማም ነበራቸው። የመጀመሪያው የበዓሉን ሁነት ሙሉ በሙሉ ጠልፎ በኦነግ አርማ ያሸበረቀ የነውጥ የቅስቀሳ መድረክ የማድረጉ ሙከራ አልተሳካም፤ ሁለተኛው ግን ከሞላ ጎደል ተሳክቶላቸ ዋል።

በመሆኑም ታላቁን የኢሬቻ በአል በማደፍረስ የኦሮሞዎችን ባህልና ወግ መጣስ የጀመረው ኦነግ ያሰማራው አዋኪ ቡድን የአባገዳዎችን ትእዛዝ በመጣስ ሁለተኛውን የኦሮሞዎችን ባህል ያለማክበር ጥፋት ፈጸመ። ይህ ለኦሮሞዎች ስርአት - ባህልና ወግ የማይገዛ ቡድን ከአባገዳዎቹ አቅም በላይ ስለነበረ አባገዳዎቹ ስነስርአቱን ለማቋረጥ ተገደዱ።

ይህ የጸጥታ አስከባሪውን ሃይል የሚፈታተን ድርጊት ሳያስቆጣው ሃይልን በሃይል የመከላከል ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበው የጸጥታ አስከባሪ ሃይል አካሄድ ይህም ተግባር የሰው ህይወትን የሚቀጥፍና የተፈነከተ ሰው እንደሚያሳጣቸው የተገነዘቡት የኦነግ የሁከት ተላላኪዎች በታዳሚው ህዝብ እና በሰላም አስከባሪ ሃይል ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው ሰዉ ራሱን ከድንጋይ ለመከላከል እንዲሁም በድንጋይ ውርወራ ወደ ሃይል ጥቃት የተሸጋገረው ሁከት የሚያስከትለው ተመጣጣኝ ሃይል የመጠቀም የሰላም አስከባሪ ሃይል ርምጃ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በማሰብ ራሳቸውን ሊያድኑ በሚችሉበትና ክፍተት ወዳገኙበት አቅጣጫ በማፈግፈግ መሮጥ ጀመሩ።

ይህ አጋጣሚ አዋኪዎቹን አደራጅቶ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ደግፎ ያሰማራቸው ኦነግና የፖለቲካ አቀንቃኞች ነን ባዮቹ የሚላቸው እነጃዋር የሚቸበችቡትን ሞት አስገኘላቸው። በሽሽትና በማፈግፈግ ላይ የነበሩት የበዓሉ ታዳሚዎች በመውደቅና እርስ በርስ በመረጋገጥ እንዲሁም በሃይቁ አቅራቢያ የነበረ የውሃ መውረጃ ገደል ውስጥ ገብተው በአሸዋና አፈር በመታፈን ህይወታቸው አለፈ።

የኦነግ፣ የኦነግ ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ ባዩ ጃዋር መሃመድና የኤርትራ ማህበራዊ ሚዲያዎች ገደል ውስጥ ወድቀው አሸዋና አፈር ተደምስሶባቸው የሞቱትን ሰዎች አስከሬን ተነስቶ እርዳታ ወደሚያገኙበት ስፍራ ተወስደው ሳያበቁ ነበር የአስከሬንና የቁስለኛ ገበያቸውን የጀመሩት። ይህ በራሱ በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት እንዲደርስ የነበራቸውን የረጅም ጊዜ እቅድ ያሳያል።

የግብፅ ቅጥረኛው ጃዋርና የኤርትራ ማህበራዊ ሚዲያዎች ህይወታቸው ካለፈውና ከተጎዱት ሰዎች ቁጥር በላይ እጅግ የተጋነነ የሟችና ቁስለኛ ቁጥር ነበር የሚናገሩት። በኦነግ፣ በጃዋርና በሻዕቢያ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው እስከ 6 መቶ ሰው መሞቱንና ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መቁሰላቸው ነበር። በእርግጥ የሞቱት ሰዎች ግን 55 ነበሩ። (55 ሰው መሞቱ ትንሽ ነው እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እገልጋለሁ።) የቁስለኞችም ቁጥር 100 ብቻ ነበር።

ይሁን እንጂ አዋኪ ቡድኑ የሚወስደውን የሃይል ጥቃት ለመከላከል በምላሹ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ፣ በስፍራው በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመገኘታቸው ጋር ተዳምሮ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሟቾችና ቁስለኞች እንዲኖሩ ሊያደርግ ይችላል በሚል ግምት አቅደውት የነበረውን የሟቾችና የቁስለኞች አሃዝ ነው የነገሩን። የሞትና የመቁሰል ምክንያቱንም በተመለከተ አስቀድመው የገመቱትን ነው የተናገሩት። በተቃራኒው የሃኪም ማስረጃ እንዳመለከተው አንድም በጥይት ወይም በሌላ መሳሪያ ተመትቶ የሞተና የቆሰለ ሰው አልነበረም ነገር ግን እነዚህ የጥፋት ሀይሎች በጥይት ተደብድበው (በከባድ መሳሪያ ጭምር) እንደሞቱ አድርገው ነበር ያወሩት።

ሌላ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተነዛው ውሸት በተለይ የገዳ ስርአትን ምንም ሳይሸራረፍ ጠብቆ ያቆየው የጉጂ ጎሳ አባ ገዳ የሆኑት ኦቦ ጂሎ መልኦ ተገድለዋል የሚል ነው። ይህ በተለይ አባ ገዳቸውን እጅግ በሚያከብሩት የጎጂ ዞን ነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤንና ቁጣን ፈጥሯል። በሆሬ ቡላ ከተማ የተቀሰቀሰው ፖሊስ ጣቢያውን እንዲቃጠልና በቁጥጥር ስር የነበሩ ታራሚዎች እንዲያመልጡ ያደረገው ሁከት መነሻ ይህ አባ ገዳ ጂሎ መልኦ ሞተዋል የሚለው የሀሰት ወሬ ነው። ይህ ወሬ በተወራ ማግስት አባ ገዳ ጂሎ መልኦ በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳልሞቱ ተናግረዋል። በእርሳቸው ምክንያት ሁከት የሚቀሰቅሱ ወጣቶችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል። በኢሬቻ በኣል ላይ የተፈጸመው የሁከት ድርጊት ተገቢ እንዳልነበረም አስረድተዋል።

በሌሎች የኦሮሚያ ዞኖችም እንዲሁ በኦነግና የኦነግ የፖለቲካ አቀንቃኞች በሚያሰራጩት ነጭ ውሸት የተቆጡ ሰዎች ሁከት ተቀስቅሷል። በተለያዩ ዞኖች አንዳንድ ከተሞች የተቀሰቀሰው ሁከት ምንም አይነት የመብት ጥያቄ አልቀረበበትም። ከዚህ ይልቅ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ የግለሰብ ንብረቶችን፣ የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችንና ተንቀሳቃሽ ንብረታተቸውን በእሳት አጋይቶ በማውደም ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር የስራ እድል ማጣት ሆኖ ሳለ ለዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ተቋማትን ማውደም መድረሻው ምን እንደሆነ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። መድረሻው ማውደም ነው፤ የገዛ ሃገርን ማጥፋት። ይህ የሆነው የሁከቱ ጠንሳሾች ኢትዮጵያን በሁከት እንድትወድም ማድረግ የሚፈልጉ ግብጽን የመሳሳሉ ሃገራት የሚገኙ ቡድኖች መሆናቸው ነው። ሰሞኑን በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ይህን በተጨባጭ ያስረዳሉ። ግብጽ ኢትዮጵያን በእርስ በርስ ግጭት የማፍረስ ዓላማዋ መነሻ በአባይ ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን አይነኬ የባለቤትነት መብት ማስጠበቅና፤ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የመገንባት አቅም እንዳይኖራት ማድረግ፣ ከተቻለም በእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቱ ለዘለዓለም ፍትሃዊ የአባይ ወንዝ ውሃ ተጠቃሚነት መብቷን እንዳትጠይቅና በመብቷ እንዳትጠቀም ማድረግ ነው።

የኤርትራ መንግስት የግብጽን ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ ለማስፈጸም በተላላኪነት ያገለግላል። የኤርትራ መንግስት የግብጽ ኢትዮጵያን የማዳከም ከተቻለም የማጥፋት ተልእኮ ተቀብሎ የተላላኪነት ተግባሩን በእነ ግንቦት 7 በኩል ለማስፈጸም መወሰኑ ምንም አይገርምም። የግብጽ ዓላማ የኤርትራ መንግስት ከያዘው ኢትዮጵያን ከማተራመስ ስትራቴጂ ጋር ስለሚጣጣም።

ኢትዮጵያዊ የሆኑት ኦነግ፣ ግንቦት 7ና ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች የግብጽን ኢትዮጵያን የማፍረስና በአባይ ውሃ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት እንዳይኖራት የማድረግ ስምምነት አስገራሚም አሳዛኝም ነው። አስገራሚና አሳዛኝ ሆነም አልሆነም ነገሩ እውነት ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ከግንቦት 7 መስራችና መሪ ያፈተለከው የ500 ሺህ ዶላር እርዳታ በኤርትራ በኩል የተሰጠ ቢሆንም ምንጩ ግን ግብፅ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ እርዳታ በቋሚነት የሚሰጥ ነው። ለዚህም ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች የተለቀቀውን የግብጽና የኦነግን የወዳጅነት ጉባኤ በአስረጂነት ማንሳት ይቻላል።

ኦነግ ከህዝብ ፍቃድ ውጭ ገንጥሎ የሚገዛው ሃገር የመመስረት እቅዱ በኢፌዴሪ ህገመንግስት መክኗል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ከሌሎች ጋር በመቻቻል፣ በመከባበርና በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት ኢትዮጵያን በፍቃዳቸው መስርተው፣ የዚህች ሉዓላዊ ሃገር የስልጣን ባለቤቶች ሆነው የመኖር መብታቸው በህገመንግስቱ ተረጋግጧል።

ህገመንግስቱ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህ አልስማማ ካላቸው ጥያቄው የህዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥ ስርአትና ህዝበ ውሳኔ የመገንጠል መብታቸውን በዋስትናነት አስቀምጧል። ይህ ደግሞ የኦነግን ህልም አመከነው። በመሆኑም የሚገዛው ቁራጭ ሃገር የማግኘት፣ የህዝቡን ፍላጎትና ፍቃድ ያላገናዘበ ምኞቱን ለማሳካት የሃይልና የሽብር መንገድን መርጧል። ይህ በድብቅ የወሰነው ሳይሆን በይፋ ያሳወቀው ነው። በህዝብ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ሳያሳስበው በሽብርተኝነት፣ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባባር ወዘተ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ከግብፅ ጋር የፈፀመው ያልተቀደሰ ጋብቻ መድረሻም ይሄው ነው።

ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ መፈጸም የሚያስችል እድል የሌላት ግብጽ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ በመግባት ሃገሪቱን ለማፍረስ በጥላቻና በስልጣን ጥም የታወረ ቡድን ያስፈልጋታል። ይህን ዓላማ ለማስፈጸም ገበያ ላይ ኦነግንና ግንቦት 7ን አገኘች፤ በቀላሉም በገንዘብ ገዛቻቸው። ግንቦት 7ን ከኦነግ የሚለየው የአሃዳዊ ስርአት አቀንቃኝ መሆኑ ነው። በአሃዳዊ ስርአት ሊገዟት የምትችለውን ኢትዮጵያ መመለስ ካልተቻለ ትጥፋ የሚል አካሄድ እየተከተሉ ነው።

ከኤርትራ መንግስት ጋር ተወዳጅተው ከግብጽ በሚላክ ገንዘብ ኢትዮጵያን በሽብር ለማተራመስ የሚጥሩት ለዚህ ነው። በአጠቃለይ ኦነግ የተገነጠለች ኦሮሚያ ተስፈኛ ስትሆን ግንቦት 7 ደግሞ ኦሮሞን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ቀልጠው በአንድ ማንነት የተጨፈለቁባት አሃዳዊ ኢትዮጵያ ተስፈኛ ነው። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ነው የሚፈልጉት። ግብፅ ደግሞ ይህን አጥብቃ ትፈልጋለች።

ገዳዩን ከማጠቃለላችን በፊት አንድ ነገር እንበል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ማወቅ የሚገባው ነገር አለ፤ እሱም እነዚህን ጥቃቅን ሰበቦች መነሻ በማድረግ፣ ተገቢ የወጣቶችን ጥያቄዎች በመጥለፍ በተቀነባበረ አውዳሚ ሁከት እንዲፈነዳ የማድረግ ተግባር እየተለመደ ከመጣ ችግር ጀርባ፣ በተለይ ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ያለች መሆኑን። ግብጽ ይህን የምታደርገው ከተቻለ ኢትዮጵያን በማውደም፣ ካልሆነ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም አቅም የሌላት ደሃ እንድትሆን በማድረግ የአባይ ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን አይነኬ የባለቤትነት መብት ዋስትና ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ እንንቃ፤ አንታለል።
ከአዲስ ዘመን

በጋራ ጥረታችን ህዳሴያችን እውን ይሆናል!!!

No comments:

Post a Comment