Thursday, October 20, 2016

ኢትዮጵያ አባይን የመጠቀም መብት የግብፅን ይሁንታ አትጠብቅም

(ጥቅምት 10, 2009, (አዲስ ዘመን))-- ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ጥረታቸው እውን ወደመሆን እየተቃረበ ያለ ፕሮጀክት ነው። እንዲህ ያለ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በታዳጊ አገር የውስጥ ገቢ ብቻ ሲገነባ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የሚል ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ባልችልም በግሌ ለማጣራት ባደረኩት ሙከራ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች ታዳጊ አገሮች የሚገነቡት በብድርና እርዳታ ብቻ ነው።

ይሁንና ኢትዮጵያ የባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እየገነባች ያለችው በህዝቦቿ ነው። የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም አላት የምትባለው ግብጽ እንኳን የአስዋን ግድብ ስትገነባ የብድር አገልግሎቱን ያቀረበው የቀድሞው የሶቭየት ህብረት መንግስት ነበር።

ይህ ፕሮጀክት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ፖለቲካዊ እንድምታውም የጎላ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫም ነው። በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን እንዲጎለብት ያደረገ፣ ህዝቦች በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል ያመላከተ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

ይህ ፕሮጀክት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ከኢትዮጵያ ባለፈም በአካባቢው አገሮች በተለይ በተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው። በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመን እንዲጎለብት ያደርጋል። ኢትዮጵያ ይህን ፕሮጀክት ስታቅድ ጀምራ ስታራምደው የቆየችው “ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል” የሚለው መርህ አሁንም እየተከተለችው ነው። ይህ አቋም ትክክለኛ በመሆኑ በሁሉም የተፋሰሱ አገራት ዘንድ ተቀባይነት አለው በሚባል መልኩ ድጋፍ አገኝቷል። የኢትዮጵያ አቋም በተፋሰሱ አገራት መካከል አንድነትና መተባበር እንዲዳብር የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የወንዙን ዘላቂ ህይወትም አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ አቋሟን ማንም አገር አድርጎት በማያውቀው መልኩ ፕሮጀክቱ በገለልተኛ አካል እንዲገመገም ፍቃደኝነቷን አሳይታለች። ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ አቋም በታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ እዚህ ግባ የማይባል ጉዳት ከ85 በመቶው በላይ የሆነውን የወንዙን ውሃ አመንጪ አገር ተጠቃሚ ማድረግ ነው።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተፅዕኖዎችን ለመገምገም በቅርቡ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በካርቱም ከስምምነት ደርሰዋል። ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ ትክክለኛና ፍተሃዊ በመሆኑ ስምምነቱን ተቀብላለች። የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴዎች በህዳሴው ግድብ ላይ ሁለት የተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶች እንዲካሄዱ የኢትዮጵያ መንግስት ፍቃደኛ ሆኗል። ይህን ጥናት እንዲያደርጉ በሶስቱም አገራት ከስምምነት የተደረሰው ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች ናቸው።

ግብጽ በስምምነቱ ወቅት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግብርናዋ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዲገመገም በልዑኳ በኩል በተደጋጋሚ ስታቀርብ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም። ግብጽ የአባይን ውሃ በአብዛኛው ብቻዋን በሚያስብል መልኩ ለዘመናት በመጠቀሟ ሳቢያ ወንዙን የብቻ ንብረቷ አድርጋ በመቁጠር ሌሎች የተፋሰሱ አገራት የመጠቀም መብታቸውን ለመቀበል ከብዷት ነበር። ግብፅ ለኮሚቴው በተደጋጋሚ ስታቀርብ የነበረው «የህዳሴው ግድብ በግብርና ስራዬ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ እንዲገመገምልኝ» የሚለው ጥያቄ በጋራ ስምምነቱ ወቅት ውድቅ መደረጉ የአገራችን አቋም ትክክለኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማሲውንም አቅም የሚያሳይ ነው።

የአሁኑ ስምምነት ከዚህ ቀደም የነበሩ ስምምነቶች አካል ነው። የህዳሴው ግድብ እንደተጀመረ በኢትዮጵያ ጋባዥነት በሦስቱ አገሮች ማለትም በሱዳን፣ ግብጽና ኢትዮጵያ መካከል የበለጠ መተማመንን ለመፍጠር በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ለዓመት የዘለቀ ጥናት ተካሂዷል። ተጨማሪ ጥናቶችም በቀጣይ እንደሚካሄዱ ሶስቱ አገራት በምክረ ሐሳብነት ተስማምተው ነበር፡፡ በምክረ ሐሳብነት የቀረቡት ነጥቦችም አንደኛው ግድቡ በሱዳንና ግብፅ ላይ የሚፈጥረው የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የግድቡ የውኃ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ሒደት ነው።

ጥናቶቹን ለማካሄድ ከተወዳደሩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለው ተቀማጭነቱ ፈረንሣይ የሆነ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የጥናቱን 70 ከመቶ እንዲያከናውን፣ እንዲሁም ይኸው ኩባንያ ለአጠቃላይ ጥናቶቹ ሕጋዊ ተዋዋይ ተደርጐ መመረጡ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ኩባንያ ጋር በመተባበር የጥናቶቹን 30 በመቶ እንዲያከናውን የተመረጠው አርቴሊያ የተባለ ተቀማጭነቱ በዚያው በፈረንሣይ የሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያካሂዱት የተፅዕኖ ግምገማ ግድቡ በግብፅ ግብርና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሊጨምር ይገባል በማለት ግብፅ ያነሳችው ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ሲያከራክር የቆየ ቢሆንም በመጨረሻ ይህ ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ኩባንያዎቹ ጥናቶቹን ለማካሄድ የሁለት ወራት ቅድመ ዝግጅት ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ጥናታቸውን አጠናቀው ለሶስቱ አገራት ኮሚቴ እንዲያስረክቡ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለኩባንያዎቹ 4 ነጥብ5 ሚሊዮን ዩሮ በጥቅሉ የሚከፈል ሲሆን ወጪውን ሦስቱ አገሮች በእኩል ድርሻ እንደሚሸፍኑት ታውቋል፡

ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት በግብጽ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ለኢትዮጵያ በአባይ የመጠቀም መብትን ማንም ሊሰጣትም ሆነ ሊነሳት አይቻለውም። ግብጽና ሱዳን በወንዙ የመጠቀም ያላቸውን መብት ኢትዮጵያም ሊኖራት የግድ ይላል። ይሁንና ኢትዮጵያ ፕሮጀክቷን በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲገመገም መፍቀዷ የሚያሳየው ግድቡን በተመለከተ ትክክለኛ መርህ መከተሏን ያረጋግጣል። ፕሮጀክቱን ያስገመገመ በተፋሰሱ አገራት የተለመደ አካሄድ አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብፅ አቻዎቻቸውም ሆነ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ፕሮጀክቱ በታችኞቹ የተፋሳሰ አገራት እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና የቀድሞ የግብጽ መንግስታት የአባይን ጉዳይ በተሳሳተ መልኩ በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ በማድረጋቸውና የግብጽ ሚዲያዎች በሚያራግቡት የተሳሳተ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያራምደውን ፍትሃዊ የመጠቀም አቋም ለመቀበል ቸግሯቸው ነበር።

“ሌባ እናት ልጇን አታምንም” እንደሚባለው የግብጽ መንግስታት እንደራሳቸው እየመሰላቸው የመንግስትን መግለጫ መቀበል ተስኗቸው ነበር። ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ውዲህ እውነታው አግጦ በመውጣቱ የግብጽ መንግስት ብቻ ሳይሆን በርካታ ግብጻዊያን ጭምር የኢትዮጵያን መብትና አቋም በመረዳታቸው እውነታውን መቀበላቸውን ማየት ተችሏል።

አባይ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብት ሆኖ ሳለ ግብጻዊያን በአባይ ላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሲያለሙ ለማንም አማክረው አያውቁም። በተለይ ኢትዮጵያ መብት እንዳላት የግብጽ መንግስት አስቦት አያውቅም ነበር። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው አገራችንም አቅም ፈጥራ በጋራ ሃብቷ ላይ መጠቀም እንደምትችል ማሳያቷ ለሁላችንም ትልቅ ኩራት ነው። እንደ እኔ አገራችን እንዲህ ያለ ተጽዕኖ መፍጠር መቻሏ በራሱ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው በራስ የመተማመን ስሜት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የፈለገችውን የማልማት መብት ቢኖራትም የሌሎች ተፋሰስ አገራትን መብት ችላ በማለት የራሷን ጥቅም ብቻ ለማራመድ አልሞከረችም። ይህ አይነት የኢትዮጵያ መንግስት አቋም የመነጨው መንግስት ከሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። ይህ የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ መንግስት ህዝባዊነት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገሮች ህዝቦች ጭምር መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ ፍትሃዊነትን የሚያሰፍን በመሆኑ በማንም ቢመረመር በማንም ቢፈተሽ ስጋት አይፈጥርበትም። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በውጭ አካል እንዲጠና ፍቃድ የሰጠችው። በቅርቡ በሶስቱ አገራት የተደረሰው ስምምንት በግብፅና በሱዳን መንግሥታት ላይ መተማመንን መፍጠር ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ገልጿል።

የጥናቶቹ ሒደት ከግንባታው ሒደት ጋር ጎን ለጎን እንደሚከናወን፣ የጥናቱ ውጤትም በግድቡ የግንባታ ሂደትም ሆነ ይዘት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ እንደማይኖር የኢትዮጵያው ተወካይ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከመጀመሪያም ይዛው የተነሳችው ፕሮጀክት በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙሀን የግድቡ ግንባታ እንደቆመ ወይም የይዘት ለውጥ እንደሚደረግበት አድርገው በመዘገብ የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም እንዲህ ያሉ ማደናገሪያዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተጀመረበት ፍጥነትና በተያዘው እቅድ መሰረት እየተከናወነ ነው። ማንም ሊያቆመው የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በውስጥ አቅም የሚገነባ ፕሮጀክት ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ ከተሰበሰበው ገንዘብ ግማሽ ያህሉ በመንግስትና በግል ተቋማት ካሉ ሰራተኞች እየተሸፈነ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሁኔታ እስካሁን ከተሰበሰበው 8 ቢሊዮን ብር ውስጥ 4 ነጥብ 27 ቢሊዮኑ ከተቀጣሪ ሰራተኞች የተገኘ ነው። ይህ ትልቅ አስተዋጽዖ ነው።

ከዚህም ባሻገር ሰራተኛው ይህን ያህል ገንዘብ መቆጠብ መቻሉ በራሱ ትልቅ አቅም መፍጠር ነው። ግድቡ እስኪጠናቀቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ አሁንም እጅግ ወሳኝ ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ከሃይል ማመንጫ ባሻገር “የእንችላለን ስሜት” በህዝቦች መካከል እንዲፈጠር አድርጓል። በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን አንድነት አጠናክሯል፤ ቁጠባ ባህላችንንም እንዲጎለብት አድርጓል፣ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመን ይፈጥራል፣ የወንዙም ዘላቂ ህይወት ይረጋገጣል። እንግዲህ ይህን በርካታ ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክት ከዳር ማድረስ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።
ከአዲስ ዘመን 

ጽሑፉ የፀሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን።

No comments:

Post a Comment