Friday, October 16, 2015

ፍርድ ቤቱ በአምስት የዞን 9 ጦማሪያን ላይ ዛሬ ብይን ሰጠ

(ጥቅምት 5/2008, (አዲስ አበባ))--የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት አምስት የዞን 9 ጦማሪያን ላይ ዛሬ ብይን ሰጠ።

ጦማሪያኑ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ወንጀል ተከሰው የነበሩ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ ከሚገኙት አስር ግለሰቦች መካከል አምስቱ ቀደም ሲል ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል።

ችሎቱ በዛሬው ውሎው በሌለችበት ጉዳዩዋ እየታየ ያለው ሶልያና ሽመልስ እና የሌሎች አራት ተከሳሾችን ጉዳይ ተመልክቷል። በዕለቱ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ቃል እና ተከሳሾች ለፖሊስ የሰጡትን ቃል በንባብ አሰምቷል።

በተከሳሾች መኖሪያ ቤት በብርበራ አገኘሁት ብሎ በክሱ አያይዞ ያቀረባቸው ማስረጃዎችንም በንባብ ማሰማቱን አጠናቅቋል። ችሎቱም ተከሳሾች ሊከላከሉ ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው ዛሬ ላይ ብይን ሰጥቷል።

በዚህ መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃነ እና 8ኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል። በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ የተከሰሰበት የፀረ ሽብር ክስ ተሰርዞ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 257/ሀ እንዲቀየር ብይን መሰጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment