Friday, June 12, 2015

በየመን በተቀሰቀሰው ጦርነት ከ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች በቅርቡ ወደ አገራቸው ይገባሉ

(ሰኔ 4/2007, (አዲስ አበባ))--በየመን በተቀሰቀሰው ግጭት የተነሳ ስጋት ያደረባቸው 1ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

26 ዜጎች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከስደት የተመለሱት ዜጎች ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀወስ እንዳይዳረጉ የማቋቋም ዝግጅት እያደረግኩ ነው ብሏል። በአገሪቱ ያለውን ግጭት በመሸሽ ወደ አገራቸው መግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ዝግጅቱ መጠናቀቁን በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ግደይ ኃይሉ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ዜጎቹ በሚቀጥሉት ቀናት በመርከብ መንቀሳቀስ እንደሚጀምሩም ቆንስላው አስረድተዋል። "የመን ውስጥ አውሮፕላኖችና ሮኬቶች ቦምቡን እያዘነቡት ነው። መንግስት ዜጎቹን ከዚህ አሰቃቂ ጦርነት ለማውጣት ሌት ቀን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ከአሰቃቂው ጦርነት አምልጠው አገራቸው የገቡት ዜጎች ወደ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳይገቡ መንግስት ሁኔታዎች ሊያመቻች እንደሚገባም ቆንስላው አሳስበዋል ።

በየመን የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ሊቀመንበር ነብይ በለጠና ተመላሽዋ ወጣት ሃና ሃይሉ በሰጡት አስተያየት ዜጎችን ከሞት አፋፍ ላይ ማትረፍ ከባድ እንደሆነ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሰሩ ቦምብ እየፈሰሰባቸው ዜጎችን ለማስመለሰ ያደረጉት ጥረት እንደሚያኮራ አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ እንደሚሉት ወጣቱ ትውልድ የስደት ሰለባ እንዳይሆን መንግስት የጀመረውን የማደራጀት ሥራ ስደትን ለመግታት  ሁነኛ አማራጭ ነው ተመላሾችን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር ህገ ወጥ ስደት እንዲቆም ሚናው የጎላ ይሆናል ብለዋል።

ወጣቶችም ስደትን አማራጭ ከማድረጋቸው በፊት ሰክነው በልማት ጎዳና ባለችው አገር ላይ ሰርቶ መለወጥ እንዳለባቸውና ያለውን እድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ ተመላሾቹ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛ ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ሲራጅ ረሺድ እንዳስታወቁት በአስቃቂው ሁኔታ የመን ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አገራቸው የማስገባት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከየመን፣ደቡበ አፍሪካ፣ ሊቢያና ዚምባብዌ የተመለሱትን ስደተኞች ለማቋቋም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ እንዳመለከቱት ተመላሾቹ  ከሞት አምልጠው ዳግም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ የማቋቋም ሥራዎች ይከናወናሉ። ሥራው ተመላሾቹ ከችግር ከመታደጉ ባለፈ ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ሰርቶ የመለወጥ ተሰፋ እንዲሰንቅ በማድረግ ከስደትና እንግልት እንዲድን ያግዛል ብለዋል።

ከ2001 እስከ 2006ባለው ጊዜ ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ዓረብ አገሮች መግበታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ዜጎችን ከአገር የሚያስወጡ ይህንን ዓይነት ድርጊቶች ለመከላከልም 30 የሚሆኑነነነ ማሰልጠኛ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ተቋማቱ ዜጎች ህገ መንግስታዊ የመንቀሳቀስ መብታቸው ሳይገደብ በቂ እውቀት ሰንቀው ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሚፈልጉበት ተዘዋውረው እንዲሰሩ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አቶ ግርማ አብራርተዋል።

ዛሬ እኩለ ቀን ወደ አገራቸው የተመለሱት ከሳዑዲ ዓረቢያ ተነስተው በካርቱም በኩል የመጡ ናቸው። በውጭ በስደት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እስካሁን በተደረገው ጥረት ከየመን ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች አገራቸው ተመልሰዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

1 comment:

Anonymous said...

THANK YOU OUR GOVERNMENT YOU MADE US BE PROUD. PROUD TO BE ETHIOPIANS......... THEY USE TO SAY, IT IS ONLY THE USA WHO CARE ABOUT/FOR THIER CITIZEN BUT, ETHIOPIA DID IT AGAIN BEFORE FROM SAUDI AND NOW FROM YEMEN. THANK YOU AGAIN AND AGAIN GOD BLESS YOU LONG LIVE EHADG

Post a Comment