Monday, March 16, 2015

አሰቃቂውና አስጨናቂው ስደት

(መጋቢት 7, 2007, (አዲስ አበባ))--«ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይጓዛሉ፡፡ የሁሉም ምክንያት አንድ ነው፤ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎቻችንን ከባህር የወጣ ዓሣ ከማድረጉም በላይ ለበረሃው እረሞጫ ዳርጓቸዋል፤ ለራስ ወዳድ አሰሪዎች የደም እንባ ግብር ከፋይ አድርጓቸዋል፡፡

በ2006 ዓ.ም ሳውዲ ዐረቢያ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በአዋጅ ከአገሯ አስወጥታለች፡፡ «ውጡ!» ብላ በሰላም ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረጓንም በሚዲያ አስነግራለች፤ ነገር ግን ከመከረኞቹ ስደተኞች ብዙዎች ጭንቅላታቸው እንደጉቶ እየተፈለጠ፣ አንገታቸው እንደጌሾ አገዳ እየተቆረጠ የሕይወት ዋጋ እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡ እህቶቻችን ችጋር ይዟቸው፣ ድካም ሲያንጠራውዛቸው በወጡበት ጠራራ ፀሐይ ገንዘባቸውን ተቀምተው በአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሰብአዊ ክብራቸውን ሲገፈፉ አይተናል፡፡ በወቅቱ ሳውዲ ዐረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በአዋጅ የመለሰቻቸው ወገኖች ቁጥር ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ይህ ቁጥር ከአንዲት አገር ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱትን ኢትዮጵያውያን ብዛት የሚያመለክት ነው፡፡ ያልተመለሱት ወገኖቻችን ምን ያህል ይሆኑ? ተደብቀው የቀሩት፤ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በየሆስፒታሉ የሚሰቃዩት፤ በጨለማ እስር ቤት የሚማቅቁት ምን ያህሉ ይሆኑ?

የዛሬ ዓመት 2006 ዓ.ም የካቲት ላይ ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለሥራ በተሰማሩባት የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ውስጥ ሔጄ በነበረበት ወቅት ያጋጠመኝን ገጠመኝ መሠረት አድርጌ ትዝብቴን እንደሚከተለው ላሰፍር ወደድኩ፡፡ አንዲት ውሎዋና አዳሯ በሥራ የተወጠረ እህታችን ነበረች፡፡ ይህቺ እህታችን እጅግ ከፍተኛ የጉልበት ሥራ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ያለ እንቅልፍ በከፍተኛ የጉልበት ሥራ ስትቃትት ቆየች፡፡ ልጅቷ በአራተኛው ቀን ላይ እንቅልፍ ጣላት፤ ከሥራ ስትመለስ ተኝታ ያገኘቻት አሠሪዋ በንዴት ትጮህባትና ትቀስቅሳታለች፤ ልጅት ደንግጣ ስትቆም በጥፊ ትቀበላታለች፤ እጇ ላይ በገባው ዕቃ ሁሉ ደጋግማ ትመታታለች፡፡ ልጅቷ ብሶቷን በሆዷ ይዛ ከሰዓታት በፊት የወለ ወለችውን የግድግዳ መስታወት ደግመሽ ወልውይ ተብላ መወልወል ጀመረች፡፡

ቀን መሽቶ አሳዳሪዎቿን እራት አበላች፡፡ እርሷ እንደተራበች ወደሥራዋ ተመለሰች፡፡ ድጋሚ የምትሠራውን ሥራ ስትጨርስ ግን ቀን የደረሰባት ድብደባ ድጋሚ እንዳይደርስባት በማሰብ ማድቤት ውስጥ ኩርምት ብላ ተቀመጠች፤ በእንቅልፍ ማጣት የተነሳ አእምሮዋ በጭንቀት ተወጠረ፤ ጤናዋ ታወከ፤ መጮህ ጀመረች፤ የቤቱን ዕቃ ማተረማመስ ቀጠለች፤ አሠሪዋ መጥታ ድጋሚ ትደባደባት ጀመር፡፡ የደረሰባትን የአእምሮ ጤና ችግር በመዘንጋት ቀን ለፈጸመችባት ድብደባ ምላሽ ዕቃዎቿን እየሰባበረች መበቀሏ እንደሆነ አመነች፡፡ ከባሏ ጋር ተባብራ እየጎተተች ከግቢ ውጪ ጥላት በር ዘጋችባት፡፡

ያች ምስኪን ልጅ የምትወድቅበት አልነበራትም፡፡ የዱባይን ጎዳናዎች በባዶ እግሯ እየሮጠች ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ሰባት ግዛቶች አንዷ ወደሆነችው ሻርጃ ግዛት ውስጥ ገባች፡፡ የት እንደምትሄድ አታውቀውም ነበር፡፡ ህሊናዋን ያሳታት የጭንቀት መንፈስ ሲለቃት ራሷን ስታ ወደቀች፡፡ በአጋጣሚ ራሷን ስታ የወደቀችበት ቦታ አቡሽካራ መናፈሻ በሚባል አካባቢ ላይ በሚገኝ አፓርትመንት አካባቢ ነበር፡፡ በዚህ አፓርትመንት በጃዛ ቤት (ሐበሾች ተሰብስበው የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት) ነበር፡፡ ከዚህ ጃዛ ቤት ወጥተው ወደሥራ ለመሄድ የወጡ አንዲት ሙስሊምና አንዲት ክርስቲያን ወጣቶች ወድቃ ያገኟታል፤ ኢትዮጵያዊነታቸው አስገድዷቸው ጃዛ ቤታቸው አስገብተዋት ወደሥራቸው ይሄዳሉ፡፡

በጭንቀት የአእምሮ መታወክ የደረሰባት ልጅ ቤት ውስጥ በወገኖቼ መሐል ነኝ ብላ ትተኛለች፡፡ ነገር ግን በጃዛ ቤቱ ውስጥ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ከአንዲቷ ጋር ፍቅር ይዞኛል እያለ የሚመላለስ አንድ ፊሊፒንሳዊ በቤቱ ድንገት ተከሰተ፡፡ ያቺን ምስኪን አስገድዶ በመድፈር ለሌላ ተጨማሪ የአዕምሮ ሁከት ዳረጋት፡፡ በመሐል ለእረፍት ወደ ጃዛ ቤቱ የመጣችው የፊሊፒንሳዊው ወዳጅ ድንገት ከተፍ ትላለች፡፡ እወድሻለሁ የሚላትን ሰው ከልጅቷ ጋር መርፌና ክር ሆኖ በማየቷ ክፉኛ ተናደደች፤ ያቺ ምስኪንም ጥፊዋን አስተናገደች፤ ስድቧንና እርግጫዋን ተቀበለች፡፡ በዚህን ጊዜም ልጅቷ ከጃዝ ቤቱ በመውጣት እየሮጠች ወረደች፡፡ አንጀቷ እስኪቆስል እያለቀሰች፤ እግሯን እየጎተተች በሻርጃ ሰፋፊ ጎዳናዎች ላይ ከወዲያ ወዲህ ትቅበዘበዛለች፡፡

በመጨረሻም የፍጥነት መንገድ በሆነው አስፓልት መሐከል ላይ ዘላ ትገባለች፡፡ ጎን ለጎን ሆነው በሰዓት በመቶ ሃያ ኪሎ ሜትር የፍጥነት ወሰን ከሚሄዱት መኪናዎች አንዱ እንደኳስ ያጎናታል፡፡ ደርቦ የመጣው ሌላው መኪና ደግሞ ይቀበላታል፡፡ በፍጻሜው ብሶቷን የምትተነፍስበት የአፍታ ቅጽበት ሳታገኝ ጸጥ አለች፡፡ የድሃ ጉልበቷ የሀብታሞችን ቤት እንዳቀና ሁሉ የድሃ ደሟ የሀብታም መኪና የሚንፈላሰስበትን መንገድ አጠበ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፤ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ቆይታዬ የሰማሁት ብቻ ሳይሆን ሆስፒታል ድረስ ሄጄ በዓይኔ ያየሁት የብዙ ወገኖቻችን ስቃይ አለ፡፡ በተለይ የነፃ የሕክምና አገልግሎት በሚሰጥበት ረሽድ ሆስፒታል ውስጥ ብቻ ወገኖቻችን ከስቃያቸው ብዛት ሞት እየናፈቃቸው የአልጋ ቁራኛ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በተለይ አንደኛዋ ልጅ በሆስፒታሉ ከአራት ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡ ይህቺን ልጅ ከሌሎች ህሙማን ለየት የሚያደርጋት በሆስፒታል ያላት ቆይታ አይደለም፡፡ በፍፁም መናገር አትችልም፤ ጉሮሮዋ ተቆርጧል፤ ምግብ የምትወስደው አንጀቷ ላይ በቀዶ ጥገና በተገጠመላት ምግብ መቀበያ አማካይነት ነው፡፡ ይህቺ ልጅ ከሌሎች በተለየ መልኩ የምትደነቅበት ነገር አላት፡፡ ጉዳቷ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ በሆስፒታሉ ያላት ቆይታም ረዥም ከመሆኑ አንጻር አምላኳን በፍጹም አታማርርም፡፡ ሁሌም ከፊቷ ላይ ፈገግታ አይጠፋም፡፡ ለዚህ አሰቃቂ ችግር የተዳረገችው በረኪና ጠጥታ ነው፡፡

 ለምን «በረኪና ጠጣሽ» ብዬ ስጠይቃት «እሱን መናገር አልፈልግም» ብላ ጻፈችልኝ፡፡ ሦስት ጊዜ ሄጄ ጠይቄያታለሁ፡፡ በመጀመሪያ ጊዜ ለቴሌቪዥን ፕሮግራም ልቀርፃት ነበር የሄድኩት፡፡ በቀረፃው ወቅት አንድ ሰው «ለምን ራስሽን ለማጥፋት ሞከርሽ?» ብሎ ጠየቃት፡፡ ፈገግታዋ ይሄኔ ጥይም አለ፡፡ እኔም እንዳየሁት በቅርብ የሚያውቋትም ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ ይቺ ልጅ ፈገግታዋን የምታጣው ይህ ጥያቄ ሲነሳ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጥ ልጅቷ ዛሬ በአገራችን ቀዳሚ ከነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በአንዱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ያሉ ፕሮፌሰር የእህት ልጅ ነች፡፡ ይሄ ይሆን ያስከፋት? ዘመድ ያላት ሆና ጠያቂ ማጣቷ? የኢትዮጵያዊነት መስመሯ ላይ የተረጋገጠ የክብር ጋሬጣ ኖሮባት ይሆን?...

አሁን ባለኝ መረጃ ይህቺ ወጣት በዚያው በረሽድ ሆስፒታል እንደተኛች ትገኛለች፡፡ ሌሎችም በቀዝቃዛ እስር ቤት ታስረው የሳንባ ነቀርሳ ህመማቸው ያገረሸባቸው፤ እንዳይሞቱ እንዳይሽሩ ሆነው የተደበደቡ፣ በሁለት በሦስት ወጠምሻ ጎረምሶች ተገደው የተደፈሩ ወዘተ አሉበት፡፡ የሚያሳዝነው እህቶቻችን ወይ ፍቅረኞቻችን ብቻ ሳይሆኑ እናቶቻችን እና አያቶቻችን የሚሆኑ ወገኖቻችን ሁሉ በዚያ አሉ፡፡ በአሠሪዎቻቸው ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ከፖሊስ ጋር ድብብቆሽ የሚጫወቱ ወገኖች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በፍፁም ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው የሴተኛ አዳሪነትን ሕይወት ጀምረዋል፡፡ በተለይ በዱባይ ባለ አንድ ቦታ ያየሁት እውነት ይሄንኑ የሚያረጋግጥልኝ ነበር፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን አገራችን ገመናችንን ደብቃ፣ እቅፍ ድግፍ አድርጋ ከምታኖረን እናት ጉያ ስንወጣ ማንም ሰው የሚገምተው የተሻለ ሕይወት እኖራለሁ እንጂ ከባሰበትም የባሰበት ሕይወትን እቀላቀላለሁ ብለን አይደለም፡፡ በዱባይ ግን እህቶቻችን የአደንዛዥ ዕጽ ሰለባ ሆነው በዓይኔ አይቻለሁ፤ በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው ገላቸውን አራቁተው ተመልክቻለሁ፤ ወደ ቦታው ጎራ ያልኩት ቀን በመሆኑ አብዛኞቹ አብረዋቸው ያሉት ወንዶች ሱዳናውያን ሲሆኑ ዐረቦቹ ማታ ማታ ብቻ ብቅ እንደሚሉም ሰምቻለሁ፡፡ ሱዳኖቹ ግን የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ግድ የሆነባቸውን እህቶቻችንን በመድኃኒት እያፈዘዙ እንዳሻቸው ይሆኑባቸዋል፤ በነፃ፡፡

በዚህ ሕይወት ውስጥ ተሰማርተው ባሉት እህቶቻችን ላይ አብረውኝ ከነበሩት ብዙዎቹ ሲያፍሩባቸው አይቻለሁ፡፡ እኔ ግን ሀፍረት ሳይሆን ልብ ሰርስሮ የሚገባ ኀዘን ነበር የተሰማኝ፡፡ ያልፍልኛል ብለው ከአገር የወጡና ያለፈባቸው ብዙ ናቸው፡፡ በተስፋ መቁረጥ ደዌ የሚሰቃዩም በርካታ ናቸው፡፡ በበታችነት እና በጭንቀት ስቃይ ውስጥ ያሉ በዚያ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል ናቸው፡፡ ይህም ማለት ከዐርባ ሺ በላይ ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ በእሳት እየተፈተኑ የሚኖሩ ወገኖቻችን መከራቸውን አይተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብ ይልካሉ፡፡ እነርሱ የሚለብሱት አጥተው ጎረምሳ ባላቸውን (ፍቅረኛ?) ይቀልባሉ፡፡

እነርሱ ይለብሱት ቸግሯቸው ስታይል እየቀያየሩ ለመዘነጥ ቅጥ ያጡ እህቶቻቸውን (ጓደኞቻቸውን) ያለብሳሉ፡፡ ይህም ይመስለኛል እዚህ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በዐረብ አገራት በስደት የሚኖሩ እህቶቻችን ተመችቷቸው እንደሚኖሩ እንድናምን የሚያደርገን፡፡ እነርሱ ነጭ ላብ፣ ጥቁር ደም ገብረው የሚልኩት ገንዘብ በቀላሉ የሚገኝ መስሎ የሚታየን፡፡ ያላባቸውን እና ያደማቸውን መከራ ብናውቀውማ ኖሮ ዛሬም እግራችንን ወደ በረሃማው መንገድ ባላቀናን ነበር፡፡ ዛሬም ልባችን ለመሰደድ ባልተነሳሳ ነበር፡፡

ስደትን እና እኛን ምን ያገናኘናል? እኛ እኮ በየትኛውም ዓለም የምንታወቀው በስደተኝነት አይደለም፡፡ ይልቁንም ስደተኞችን በክብር በመቀበልና በሚገባቸው ቦታ በማኖር እንጂ፡፡ የተገፉትን ሰብሳቢዎች ነበር መለያችን፡፡ እንግዳ ተቀባይ ነበር ስማችን፡፡ ዛሬ ግን የክብር ቦታ የሚሰጠን ብናጣ እንኳን ከእነክብራችን እንድንኖር መብት ሊነፈገን አይገባም ነበር፡፡ ይሁን፣ ክፉ የሚባለው ነገር ይደረግብን፤ እኛ ለምን ወደመታረጃው ቦታ ሰተት ብለን እንገባለን? ስደት ከእኛ ጋር ምን ወዳጅነት አለው?

በአንገታችን ላይ ካራ ይሳላል፤ በእግራችን ላይ እግረ ሙቅ ይጠለቃል፤ በእጃችን ላይ የብረት ካቴና ይታሰራል፤ በፊታችን ላይ የፈላ ውሃ ይደፋል፤ መኖርን ጠልተን መሞትን እንድንናፍቅ እንገደዳለን፤ እኛስ ለምን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ብለን የተሻለ መከራ እንቀበላለን? ለምንድንነው ሞታችን ወደተደገሰበት ተራራ የምንወጣው? ልንሰደድ ያሰብን፣ እየተሰደድን ያለን ሁሉ ቆም ብለን እናስብ፡፡ በአገራችን ኩርማን እንጀራ የምንቋደስበት ሥራና ጤና ይዘን መኖር እንችላለን፡፡ በሰው አገር ግን ሥራውን ሳናገኘው፤ ጤናችንን ገብረን፤ ሙሉ አካላችንንም አጥተን የስብዕና መዛነፍ ውስጥ እንገባለን፡፡ ስለዚህ ስደት እና እኛ ፍቺ ልንፈጽም ይገባል እላለሁ፡፡

ባጠቃላይ፣ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን በለውጥ እርምጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ በርካታ የዓለም ሀገራት ፊታቸውን ወደሀገራችን ማዞራቸውና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት ለዜጎች ሠፊ የሥራ ዕድልን ከመፍጠራቸው ባሻገር መንግሥት በቀየሰው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ትርጉም ባለው መልኩ ተቋቁመው ከመንግሥት በሚደረግላቸው ድጋፍ የሀብት ባለቤት እስከ መሆንና ለሌሎች ወገኖቻቸው የሥራ ዕድል እስከመፍጠር የደረሱ ስላሉ የእነርሱን ፈለግ ተከትለን ፊታችንን ወደሀገራችን ልማት በማዞር በስደት ምክንያት ሊደርስብን ከሚችለው ሰብዓዊ ቀውስ እራሳችንን በማዳንና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረን በማገልገል፤ እንዲሁም ያገኘነውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመን የራሳችንን ተቋም በማቋቋም ራሳችንን ለውጤት እናብቃ፤ በዚህም የስደት ዘመን ይብቃ፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment