Monday, February 16, 2015

ወዳጅነትስ እንደ ቱርክ

(የካቲት 09/2007 , (አዲስ አበባ))--የውጭ ንግድ ገቢዋ 158 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ቱርክ በዓለማችን ኢኮኖሚ በትልቅነቷ 17ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የቡድን 20 አገሮች የፕሬዚዳንትነት ወረፋ የደረሳት ሲሆን፣ ቀጣይ ትኩረቷን በአፍሪካ ላይ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡ ቱርክ በአፍሪካ ያላት ኢንቨስትመንት መጠን ከ23 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

እንደጨርቃጨርቅ፣ ኮንስትራክሽንና ግብርና ባሉ ዘርፎች ላይ ሰፊ ልምድና ውጤታማነት ያሳየችው ቱርክ ሰፊ የሠራተኛ ኃይል ባለበት የአፍሪካ አህጉር ማነጣጠሯ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ፖሊሲዋን ስኬታማነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በቅርቡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ያደረጉት የአፍሪካ ጉብኝትም የኢኮኖሚ ግንኙነቱን የማጠናከርና በፀረ ሽብር ትግሉ አጋርነትን የማጠናከር ተልዕኮ የያዘ ነው፡፡

የ60 ዓመቱ የቱርክ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አፍሪካን ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ይህም ምናልባት በንግግራቸው እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያን የቱርክ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻና ቁልፍ አጋር ለማድረግ ያላቸውን ዝንባሌ የሚረጋግጥ ነው፡፡

በርግጥ ቱርክ በአፍሪካ ላይ ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ጥረቷን ከጀመረች ቆይታች፡፡ 1988 (እ.ኤ.አ) የወጣውን የአፍሪካ መርሃ ግብር ተከትሎ በ2003 (እ.ኤ.አ) የአፍሪካ ቀዳሚ እቅዷን (African Initiative) ነደፈች:: በ2005 ደግሞ የአፍሪካ ዓመት በሚል ሙሉ ትኩረቷን በአህጉሩ ላይ የማሣረፍ ፍላጎት አሳየች፡፡ በ2003 (እ.ኤ.አ) ቱርክ በአፍሪካ ላይ የነበራት የኢንቨስትመንት መጠን 4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ8 እጥፍ በላይ በማሳደግ ነበር 25 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰችው፡፡

የኢትዮ-ቱርክ ግንኙነት
የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ 16ኛው ክፍለ ዘመን የሚመዘዝ ታሪክ አለው፡፡ በዘመኑ ሠፊ የግዛት ወሰን የነበረው ኦቶማን ቱርክ በንግድና ወታደራዊ ግንኙነት ወደ ሐረር ዘልቆ መቆየቱን ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ባለፉት አምስት ምዕተ ዓመታት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተዳክሞ ከቆየ በኋላ በቅርቡ መጠናከር የጀመረው የንግድ ኢንቨስትመንት ትስስሩ ቱርክ ከታላቆቹ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አጋሮች አንዷ እንድትሆን አስችሏል፡፡ ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መዳረሻዎች መካከል ቱርክ በ9ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ከሚላክባቸው አገሮች መካከል ቻይና ቀዳሚዋ ስትሆን፣ ሶማሊያ፣ ጀርመን፣ ሳዑዲአረቢያ፣ ሱዳን፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድና አሜሪካ በቅደም ተከተል ይቀጥላሉ፡፡

የቱርክ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ በ2003 (እ.ኤ.አ) ከነበረበት 23 ሚሊዮን ዶላር በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ በ7 እጥፍ አድጎ 421 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በዚሁ ወቅት አንድ ብቻ የነበረው በኢትዮጵያ የተሠማራ የቱርክ ኩባያ ቁጥር ወደ 150 አድጓል፡፡ እነዚህ 150 ኩባንያዎች በድምሩ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ለ50 ሺ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ኃይል በመቅጠር የግሉን ዘርፍ እንዲመሩ አስችሏቸዋል፡፡

ለምሳሌ በአገራችን ግዙፍ የሆነው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የቱርኩ አይካ አዲስ ሲሆን፣ በ140 ሚሊዮን ዶላር በ2010 ነበር የተቋቋመው፡፡ ከፍተኛ የሰው ኃይልን በሚጠቀመው የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ መሠማራቱ ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግሩም ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፡፡

የሁለቱ አገሮች የንግድ ሚዛን
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በምትልካቸው ምርቶች ከፍተኛ ገበያ ከምታገኝባቸው አሥር አገሮች መካከል ቱርክ አንዷ ብትሆንም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ወደ ቱርክ ያዘነበለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ ቱርክ የተላከው የኢትዮጵያ የወጪ ምርት ያስገኘው ገቢ 84 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ ይህ መጠን ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ የ2 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ከወጪ ንግድ መዳረሻዎቻችን መካከል ቱርክን በዘጠነኛ ደረጃነት ያስቀምጣታል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ የምትልካቸው ምርቶች ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ ጫት፣ የቁም እንስሳት፣ ሥጋ፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጨርቃጨርቅና ቆዳና ሌጦ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ቱርክን የተሻለ ተጠቃሚ በሚያደርግ ሁኔታ የ100 ሚሊዮን ዶላር ክፍተት አለው፡፡

የንግድ ግንኙነቱ ቀጣይነት
የኢትዮ ቱርክ የንግድ መድረክ በ2009 ነበር የተመሰረተው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፣ የቱርክ ኩባንያዎችም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተሠማሩት በዚሁ የጊዜ ወሰን ነው፡፡ በንግድ መድረኩ ላይ ከኢትዮጵያ ወገን በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የተመራ የንግዱ ማህበረሰብ ቡድን ወደ ቱርክ የተጓዘበት የመጀመሪያው የኢትዮ ቱርክ የንግድ መድረክ ባለፈው ዓመት ተካሂዷል፡፡

ዘንድሮ ደግሞ ከፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ጉብኝት ሦስት ሳምንት ቀደም ብሎ 200 የቱርክ ባለሀብቶችና የዘርፉ ባለሥልጣናትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ውይይት አድርጓል፡፡ በሰሞኑ ጉብኝትም ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶጋን ባለቤታቸውን ቀዳማዊ እመቤት ኤሚን ኤርዶጋንንና ልጃቸውን ሱመያ ኤርዶጋንን ጨምሮ 80 የንግድ ልኡካንን ይዘው መጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የአገራቸውን የኢንቨስት መንት መጠን ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት ሲገልፁ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በማስረዳት የአገራቸው ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሠማሩ ለማድረግ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ቃላቸውን የሚጠብቁ መሪ›› ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ የሚገልጿቸው ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ከወዲሁ ቃላቸውን የሚያረጋግጡ ምልክቶች እያሳዩ ነው፡፡

የአገሪቱ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ፈርማኖግሉ በአዲስ አበባ 300 ሺ ቤቶችን ለመገንባት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ይህ የቤቶች ግንባታ መጠን ከ12 ዓመት በፊት የነበረችውን አዲስ አበባን የመገንባት ያህል የሚመጣጠን ነው፡፡ ሌላው የቱርክ ኩባንያ የአዋሽ ወልዲያን የባቡር ፕሮጀክት ለመሥራት ፈቃድ መውሰዱን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ ፕሮጀክት 389 ኪሎ ሜትሮችን በመሸፈን የአገሪቱን ሰሜናዊና ምሥራቃዊ ክፍሎች የሚያገናኝ ሲሆን 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል፡፡

ሌሎች አሥራ አራት ፕሮጀክቶችም ተግባራዊ እንደሚደረጉ ስለሚጠበቅ በአጠቃላይ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ተሳትፎ ግንባር ቀደም ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እንዲህ ይላሉ፤ ‹‹ለኢትዮጵያ ካለን ፍቅር አኳያ ያደረግነው ኢምንት ነው፡፡››

ከእኛስ ምን ይጠበቃል?
የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት መሠማራት የጀመሩት ባለፉት አራት ዓመታት መሆኑን የሚያረገግጥልን እውነታ በአገራችን የሚታየውን ለውጥና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ዕድል በሚገባ መገንዘባቸውን ነው፡፡ ይህን መነሻ ይዘው ወደ አገራችን ሲመጡ የጠበቃቸው አቀባበልም መልካም መሆኑን በሰሞኑ የንግድ ፎረም ላይ ገልፀውታል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መሰረቱ የአገሪቱ የልማት ፖሊሲ ሲሆን፣ ለኢንቨስተሮች እንዲስማማ ተደርጎ በተደጋጋሚ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲም የባለሀብቶችን ተጠቃሚነት የሚያበረታታ ነው፡፡ ሠፊ የሠራተኛ ኃይል ያላት አገራችን፣ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች መሆኗም ተመራጭ ሊያደርጋት ይችላል፡፡

ሆኖም ትልቁ ነገር ቢሮክራሲውን ማቅለል ነው፡፡ የቱርክ ባለሀብቶች ጥሩ አቀባበል እንደተደ ረገላቸው የገለፁት በአንፃራዊነት ያልተወሳሰበ የቢሮክራሲ ሂደት ስላጋጠማቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በተለምዶ የውጭ ባለሀብቶች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል የተንዛዛ ቢሮክራሲና በፌዴራልና ክልል ተቋማት መካከል የሚታየው አለመናበብ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ባለሀብቶች ሠፊና ርካሽ የሠራተኛ ኃይል ለማግኘት ወይም አበረታች የሊዝ ዋጋን በመፈለግ ብቻ ወደ አገራችን ሊመጡ እንደማይችሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ይዞ የመጣን ባለሀብት እንደጌታ ተቀብሎ በአክብሮትና በቅልጥፍና ማስተናገድ የግድ ነው፡፡ ገንዘብ የያዘ ሰው በአሁኗ ዓለማችን አገሩ የትም ነው፡፡ የትም ቦታ ስቆ የሚቀበለው አያጣም፡፡

ስለዚህም ከሌሎች አገሮች ጋር ጠንካራ ፉክክር ውስጥ ሊያስገባን የሚችውን የቢሮክራሲ አሰራር ቅልጥፍና ማሻሻል ይኖርብናል፡፡ መልካሙ ነገር በመሠረተ ልማት ግንባታ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ ዕድገት ለኢንቨስትመንቱ መጠናከር የጎላ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡ በመንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ እየታየ ያለው ለውጥ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ማዕከልነት በእጅጉ የሚጨምር ነው፡፡

በኢትዮ-ቱርክ የሰሞኑ የንግድ መድረክ ላይ የኢንቨስትመንት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፍፁም አረጋ መስሪያ ቤታቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት እንደሚሰጥ በመግለፅ የውጭ ባለሀብቶች ያለውጣ ውረድ እንደሚስተናገዱ አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ባለሀብቶች እንደፍላጎታቸው ትርፋቸውን ይዘው መሄድ የሚችሉበትና የኢንቨስትመንት ዋስትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡ ከታክስ ሥርዓቱና ከምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ውጣ ውረድ እንዳያጋጥማቸውም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እነዚህ ርምጃዎች ቀላል የማይባል እፎይታ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ባለሀብቱ ምቾት ተሰምቶት ውጤታማ መሆኑ ከአገሪቱ ቀጣይ የልማት ፍላጎት አኳያ ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment