Monday, February 16, 2015

«አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ የሚሉ ሁሉ ህወሓትን ይጠሉታል» -አቶ ስብሃት ነጋ ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

(የካቲት 09/2007 , (አዲስ አበባ))--የመምህርነት ሙያቸውን ትተው ነበር በ1967 .ም ወደ ትግል የተቀላቀሉት። ከህወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው፤ አቦይ ስብሃት ነጋ። ህወሓት የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዝግጅት ክፍላችን በህወሓት አመሠራረት፣ ዓላማና የትግል አግባብ ዙሪያ ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር ያደረግነውን ቃለ- ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፡- የንጉሡ ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊ ሥርዓት ሲመጣ የነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ ምን ይመስላል? 

አቦይ ስብሃት፡-
የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት የጣለው ሕዝቡ ነው። የጣለው ደግሞ መውደቅ ስለነበረበት ነው። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታው የከፋ ነበር። በሌላው ሀገር ኢንዱስትሪው ማቆጥቆጥ ጀምሯል። የአፄው ሥርዓት በጣም ያከረረ ፊውዳል ስለነበር በሀገሪቷ ልማት የሚባል ነገር አልነበረም። ትምህርትም ቢሆን እንደ ጠበል የሚንጠባጠብ በጣም የተወሰነ እንጂ የሰፋ አልነበረም። ሕክምናም እንደዚሁ።

ሀገሪቷ ለማንኛውም አደጋ የተጋለጠች ነበረች። ሕዝቡ በረሃብ እየሞተ «ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ናት» ይባል ነበር። ሕዝቡ ኑሮው አስከፊ ሆኖ ሳለ በወቅቱ የሚነገረው ግን ኢትዮጵያ ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደገች ናት የሚል ነው። ይህ ደግሞ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ተቃራኒ ነበር። ማንኛውም ነገር ሲመረቅ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሁለተኛ ነው ይባል የነበረው።

በአፄው ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረው የከፋ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንስኤውን ይወቀው አይወቀው አገፍግፎት ነው ከተማሪዎች ጀምሮ እስከ ገበሬው ድረስ ሥርዓቱን ለመጣል ትግል የጀመረው። ፖለቲካውም አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሕዝብና አንድ ሃይማኖት የሚል ነው። ይህ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚገልጽ አይደለም። የመናገር የመፃፍ መብት የለም። እነዚህ ሁኔታዎች የአጼው ሥርዓት እንዲወድቅ ምክንያት ሆነዋል። ሥርዓቱ ከተገረሰሰ በኋላ ደርግ ሥልጣኑን ተቆጣጠረው። ምክንያቱም በወቅቱ የተደራጀ ኃይል የለም፤ ሊደራጅ የሚችል ብቃት ያለው ልምድም አልነበረውም።

በወቅቱ የተለያዩ ተደራጅተው የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ። አሰላለፋቸውንም በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው የነበረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ለመመለስ የሚታገል ነው። በሰሜን ሸዋ፣ በትግራይና በላስታ የባላባት ወገኖች ንጉሣዊ ሥርዓቱን ለመመለስ እዚህም እዚያም ትግል ሲያደርጉ ነበር።

ሁለተኛው ቡድን የብሔር ግንባሮች ናቸው። የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር፣ የሲዳማ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርና የምዕራብ ሱማሌ ነፃ አውጪ ግንባር የሚባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ከዚህ የከፋ የለም ብለው ነው ጥለው የወጡ። እነዚህ ግንባሮች «ከዚህ የከፋ የለም» ማለታቸው ትክክል ነው ግን ምንድንነው መንስኤው፣ መፍትሔውና ተለዋጩ ሥርዓት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ማስቀመጥ አልቻሉም።

ሌላው ሦስተኛው ቡድን ግራ አዝማሚያ የሚከተለው ነው። በዚህ አሰላለፍ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ አለ። እነዚህ ፖለቲካቸውና ምድባቸው አንድ ነው። በኢትዮጵያ ያለ ቅራኔ በሠራተኛውና በባለሀብቱ መካከል ያለ ቅራኔ ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የነበረውን መሠረታዊ ሥርዓት ሳይነኩ እንዳለ ሥልጣን ላይ መውጣት ነበር ግባቸው። 

ኢህአፓም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም አለበት ቢልም ደርግን ለመመከት የተከተለው ስልትና ስትራቴጂ የተዛባ ነው። ፕሮግራሙም ብቻ ሳይሆን አካሄዱም ኢትዮጵያን ያንፀባረቀ አልነበረም። እናም አፄ ኃይለሥላሴ ከሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላና ደርግ ሥልጣን ከወጣ ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ የተዘበራረቀ ነበር። ህወሓትን በአራተኛ አሰላለፍ ልናስቀምጠው እንችላለን። ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ያቋቋሙት በተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡-
የህወሓት አመሠራረት ዓላማና የትግል አግባብ እንዴት ነበር? 

አቦይ ስብሃት፡
ህወሓትን የመሠረተው ማህበረ ገስገስ ብሔረ ትግራይ (ማገምት) የሚባለው ቡድን ነው። ማገምት ይህን የፖለቲካ ሁኔታ ካየ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሀገር ናት። ስለዚህ ዋነኛው ቅራኔ የብሔር ቅራኔ ነው። ይህ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈታት አለበት። እናም በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ነው አማራጩ አለ። ቅራኔው ሀገር እየበታተነ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት መመስረት ካልተቻለ ደግሞ መገንጠል ይከተላል። በእኩልነት ላይ አንድነትን ማምጣት ይቻላል ብሎ ተነሳ።

ሁለተኛው ቅራኔ በገበሬውና በከተማ ነዋሪ ያለው ቅራኔ ነው። ሀብታችን መሬት ሆኖ ሳለ በገበሬውና በከተማው ነዋሪ ያለውን ቅሬታ ካልተፈታ ልማት አይመጣም። ሀገሪቷን የማወቅ ሙከራ እንደ መደርደሪያ ይዞ በሂደት እየጠራ የሚሄድ አቅጣጫ ተከተለ። ስልትና ስትራቴጂውም ከገጠር የሚጀምር የተራዘመ የትጥቅ ትግል ማድረግ ነው ።

እና ይህን ፕሮግራም ለማስፈጸም ደግሞ ከማንኛውም በሀገራችን የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠራ አደረጃጀት ፈጥሮ ነው የተንቀሳቀሰው። ለትግሉ የሚያስፈልገው አደረጃጀትም በኅዳር ወር 1967.ም ነድፎ ደደቢት የሚገባው ደደቢት ገባ። ኤርትራ የሚሄደው ኤርትራ ለሥልጠና ሄደ። ከተማ የሚሰማራው ከተማ ገባ። ትግሉ የካቲት 11ቀን 1967 በደደቢ በረሃ ተጀመረ ።

አዲስ ዘመን፡-
ህወሓት በትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ የትግራይን ህዝብ በኋላ ደግሞ ቀሪውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማንቀሳቀስ ረገድ ስኬታማ ያደረገው ምስጢር ምንድንነው? 

አቦይ ስብሃት፡
ምስጢሩ ፕሮግራሙ ነው። ሕዝባዊነቱ ነው። ለፕሮግራሙ ሲል ህወሓት ረጅምና መራራ ትግል ማድረጉን ማንም ሊክደው አይችልም። ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስለሚያንፀባርቅ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። ያም ሆኖ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሃይማኖትና ሌሎች አንዶችን በውስጡ አስርጾ ለኖረ ሕዝብ ስለ ትግሉ ፕሮግራም በቀላሉ ማስረዳት ይቸግራል። እናም ህወሓት ስኬታማ የመሆኑ ዋናው ምክንያት ፕሮግራሙ ነው። ፕሮግራሙን ለመፈጸም የነበረው አደረጃጀትና አሠራር የጠራ መሆኑ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ነበረው። 

ፕሮግራሙን ለሕዝብ እያሳወቀ መሄዱ፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ይህንን የሚቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እኛም እያገኘናቸው እነርሱም እያገኙን መምጣት ፕሮግራሙን ወደ ሕዝቡ ለማስፋፋት ተችሏል። በመጀመሪያ ፕሮግራሙን የትግራይ ሕዝብ ተቀበለው፤ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በጥልቀት አመነው። ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጀ። ከትግራይ ውጪ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ይህን እያመነ ሄደ።

በተለይ ደግሞ ህወሓት በትጥቅ ትግሉ የማረካቸውን የደርግ ወታደሮች ስለፕሮግራሙ አስረድቶ ስለሚለቃቸው በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ህወሓትን የመሰለ ድርጅት የለም እያሉ ይመሰክሩ ነበር። ይህም ለድርጅቱ ኃይል እየፈጠረ እየሰፋ እንዲመጣ አድርጓል። ህወሓት ትግራይ ውስጥ 17 ዓመት ትግል አካሂዷል። ወደ አማራ ሕዝብ ስንገባ ደግሞ ትግሉ እያጠረ ሄዷል። ሕዝቡም ህወሓ /ኢህዴግ ከነበረው ሥርዓት የተሻለ መሆኑን እያመነ ሄደ። ቁርጠኛ አመራርና ታጋይ እየተበራከተ መጣ። ታጋይ ስንል ገበሬውና ሐኪሙንም ይጨምራል። ለፕሮግራሙ ቁርጠኛ የሆነ አባልና አደረጃጀት ስለነበረን ውጤታማ መሆን ችለናል። 

አዲስ ዘመን፡ 
ህወሓት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመታገል የአቋም ለውጥ አድርጎ ይሆን? 

አቦይ ስብሃት፡ 
የህወሓት ፕሮግራሙ በትክክል የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያፀባርቅ ነው። ይሁን እንጂ ኢዲዩ አይቀበለንም። ኢህአፓም አይቀበለውም። እንዲያውም የብሔር ድርጅቶች አያስፈልጉም የተፈጠሩ ካሉ በኢህአፓ አመራር ውስጥ መግባት አለባቸው ይል ነበር። የኢህዴን/ብአዴን አባሎች ከኢህአፓ የወጡ ናቸው። ኢህአፓ ኢትዮጵያን ለማወቅ ፍቃደኛ አልነበረም። ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ ያገኘነው ኢህዴን/ ብአዴንን ነው። ከእነርሱ ጋርም የፖለቲካ ውይይት አድርገን ምንም ፖለቲካዊ ልዩነት አላገኘንም። ስለዚህ ትግሉን አብረን ቀጠልን። ነገር ግን ህወሓት የለወጠው ምንም ነገር የለም። የህወሓት ፕሮግራም አይለወጥም። ምክንያቱም ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚፀባርቅ ነውና።

አዲስ ዘመን፡ 
በህወሓት የትግል የመጀመሪያ ዓመታት ደርግን ለመፋለም የወጡ የፖለቲካ ኃይሎች በህወሓት ላይ ጥቃት ይፈጸሙ እንደነበር ይነገራል። ምክንያቱ ምንድንነው? እነዚህ ድርጅቶች ሲከስሙ ህወሓት እስካሁን መዝለቅ የቻለበት ምክንያትስ ምንድንነው? 

አቦይ ስብሃት፡-  
ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተጋጨንበት መንስኤ ፕሮግራሙ ነው። ኢዲዩ በምዕራብ ሀገራት እየተደገፈ የመጣ ነው። ምዕራባውያን ህወሓትን ሀገር የሚበትን ሥርዓት አድርገው ነው የተረዱት። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ የሚሉ ሁሉ ህወሓትን ይጠሉታል። ኢህአፓም እንዲሁ ነው። ከደርግም ቅራኔ ውስጥ የከተተን ፕሮግራማችን ነው። ገንጣይ አስገንጣይ ዘረኛ የሚል ስያሜ ነው የሰጡን። 

አርነት ትግራይ የሚባል የትግራይ ድርጅት ነበር። በጣም ጠባብ ነው። ከእርሱ ጋርም በፕሮግራም ተጋጨን። ጀብሃም እርሱን ይደግፍ ስለነበር ከጀብሃ ጋርም ተጣላን። የብሔሮቹ ድርጅቶች ደግሞ በእኩልነት የተመሠረተ አንድነት አይቻልም የሚል እምነት ነበራቸው። እና ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያጋጨን ፕሮግራማችን ነው። ስኬታማ ያደረገንም ፕሮግራማችን ነው።

እነዚህ ድጅቶች የከሰሙት በፖለቲካ ባህሪያቸው ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች አያንፀባርቁም። የነበራቸውን ፕሮግራም ይዘው ኃይል መፍጠር አልቻሉም። የእኛ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያንፀባረቀ ነው። መንስኤውን አስቀምጦ መፍሔውንም ያሳያል። ለስኬት እንዲበቃ ያደረገው ፕሮግራሙ ነው።

ሁለተኛ ይህንን ፕሮግራም ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጃትና አቅም ፈጥሯል። ምቹ ሁኔታ የማያመልጠው አደጋን መከላከል የሚችል ታጋይ ተፈጥሯል። አመራሩም ሲሄድም ሆነ ሲተኛም ለፕሮግራሙ የሚታገል ነው። በጥቅሉ አደጋ ካለ የሚከላከል ምቹ ሁኔታ ካለ የሚጠቀም ኃይል ስላለው ነው።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment