Wednesday, February 04, 2015

አበበ ቢቂላ ውስጡ አረንጓዴ ላዩ ግን...?

(ጥር 26/2007, (አዲስ አበባ))--የምንጊዜም ምርጡ የማራቶን ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ እ.ኤ.አ በ1960 በጣሊያን ሮም፣ እ.ኤ.አ በ1964 በጃፓን ቶኪዮ እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ከሆነም በኋላ ተወዳድሮ ኢትዮጵያውያ ንና አፍሪካውያንን አንገታቸውን ቀና እንዲሉ ላደረገበት ውለታው ከተለያዩ መንግስታትና አገሮች ዕውቅና ተሰጥቶታል። የስፖርት ጋዜጠኞችና ተንታኞች፣ የአገር መሪዎችና ሌሎችም ብዙም ብለውለታል።

በአንድ ወቅት በጣሊያን ተነባቢውና ዝነኛው ጋዜጣ «ጋዜጣ ዴሎ ስፖርት» ዘጋቢ «ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር በርካታ ወታደሮችን አዝምታ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን በአንድ ወታደር (በአበበ ቢቂላ) ድፍን ሮምን ወረረች» ሲል አበበ በባዶ እግሩ በሮም የሰበረውን የማራቶን ክብረ ወሰን ገለጸው።

በዛን ወቅት የአገሪቷ መሪ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ለጀግናው የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት አስር አለቅነትን ሰጥተውት እንደነበርና በዛም ህዝቡ በጣም እንደተከፋ በወቅቱ የነበሩ እማኞች ይናገራሉ። ታዲያ እናቱ ኢትዮጵያም ይብዛም ይነስም መታሰቢያ ማዘጋጀት ነበረባት። ምንም እንኳን በህይወት ባይኖርም ህያው ስራውን በማስታወስ በ2006 ዓ.ም በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽንና በጋዜጠኛ ሳምሶን ከተማ በተጀመረው የመጀመሪያው የምርጥ ስፖርተኞች ሽልማት ላይ የምንጊዜም ምርጥ ስፖርተኛ (የህይወት ዘመን) ተብሎ ተሰይሟል። ሽልማቱንም የአበበ ቢቂላ ልጅ የትናየት አበበ ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ተቀብሏል። ከዚህ የዕውቅና ስራ በጣም ቀደም ብሎ ደግሞ በአዲስ አበባና በአዳማ በስሙ ስታዲየሞች ተገንብተዋል።

የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ብዙ ጥቅም እየሰጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለአዳማ ከነማ እግር ኳስ ቡድን የመጫወቻና የመለማመጃ ሜዳው ሆኖ ያገለግላል፤ ከዚያ ባለፈም ለሌሎች ስፖርታዊና ለበዓላት ዝግጅቶች የሚያገለግል ስታዲየም ነው። ለአብነትም ክልሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስፖርት ፌስቲቫሎችን ሲያዘጋጅ የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ዋናው የዝግጅቱ ቦታ በመሆን እያገለገለ ነው።

ወደ አዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተመለስኩ

ሻምበል አበበ ቢቂላ በአዲስ አበባ በስሙ የተሰራለት «ስታዲየም» ስታዲየም ነው ብሎ ለማውራት በጣም ያስቸግራል። ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም።ኢትዮጵያ «አበበ ቢቂላን በምን እያስታወሽው ነው?» ተብላ ብትጠየቅ ምላሿ በአገሪቷ ሁለት ስታዲየሞችን በስሙ ሰይሜለታለሁ ማለቷ አይቀርም። ነው ለምን? በስሙ ስታዲየሞች ስለተሰሩ። ይህ መቼም ግዴታዋ ይመስለኛል ግን ስቴዲየሞቹ ከስም ባለፈ ፋይዳ እንዲሰጡ ማድረግም ያስፈልጋል።

ምክንያቱም

አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ የማራቶንን ክብረ ወሰንን የሰበረባት (2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ማይክሮ ሴኮንድ ) የጣሊያኗ ሮም በአበበ ስም ድልድይ ሰይማለች። እ.ኤ.አ በ1964 የራሱን ክብረ ወሰን ያሻሻለባት የጃፓኗ ቶኪዮም «በብዙ መልኩ ሻምበል አበበን አዘክራለሁኝ» ማለቷን እ.ኤ.አ 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዙ አቤ የአበበ በቂላን ልጅ (የትናየት አበበ) በሸራተን አዲስ ባገኙበት ወቅት ተናግረዋል። በተግባርም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዳለ ይታወቃል።

ታዲያ አዲስ አበባ ያለው አበበ ቢቂላ ስታዲየም «ስታዲየም» ለመባል ያስቸግራል ያልኩት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። ስታዲየሙ ኳስ ያጫውታል። ኳስ የሚያጫውት ሜዳ ሁሉ ግን ስታዲየም እንደማይባል የስፖርት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሲጀመር በክቡር ትሪቡን ያሉት ወንበሮች በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ ግማሽ ጎናቸው አልቆ፤ ግማሹም ተሰነጣጥቆ ሰው የሚቀመጠው ደረጃዎቹ ላይ ነው። ሌላው የገረመኝና ያሳዘነኝ የእንግዶች መቀመጫ የለም። እንግዶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ስታዲየም ይመጣሉ። ስለሆነም ለነዚህ እንግዶች የተስተካከሉ ወንበሮች ሊኖሩ ይገባል። ለእንግዶች የሚሆን ወንበር ስለሌለ ዝም ብሎ የላስቲክ ወንበር አንዳንድ ጊዜ ከውጭ እንዲመጣ ይደረጋል። ይህ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ መዲና ለምትባል ከተማ የማይመጥን፣ አበበንም በወጉ የማያስጠራ ነው።

ሌላው ስታዲየሙ ሰው ሰራሽ ሳር የተገጠመለት ስለሆነ ኳስን አንሸራሽሮ ለመጫወት አመቺ ነው በመሆኑ ም ውስጡ አረንጓዴ ሆኗል። ከዚህ በላይ ግን አዲስ አበባ አስተዳደር ለስቴዲየሙ ከፍተኛ ሀብት «አወጣሁ!» እንደማለቱ ፍሬው የት አለ ያስብላል?

ዳሩስ...?

ዳሩንማ አለማየት ነው የስታዲየሙ ዳር ጭራሽ እልም ያለ በረሃ ውስጥ ያለ ባዶ መሬት ነው የሚመስለው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። አያድርገው እንጂ ተጫዋቾች ወይም ዳኞች ለኳስ ከተባለችውና ሳር ከለበሰችው ሜዳ ውጭ ቢወድቁ እኮ የሚደርሰው አደጋ ከባድ ነው።ታዲያ ሳር ብቻ ለብሶ ዳሩ እንደተደበደበችው ባግዳድ ጭር ያለው ለምንድነው? እያልኩ ራሴን እየጠየቅሁ ተክዤ ነበር። ከዚያም ብዕሬን ላነሳ ሲቃጣኝ በመገናኛ ብዙሃን «አበበ ቢቂላ እድሳት ሊደረግለት ነው» የሚል አስደሳች ዜና ብሰማም እስካሁን ግን ምንም የተለየ ነገር አላየሁም። የተውኳትን ብዕሬን በድጋሚ አነሳኋት!

የዚህ ስታዲየም ባለቤት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንም ሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስታዲየሙ ብቻ አይደሉም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ነው። ማለት ይቀላል። ስለዚህ ስለምን የስፖርት ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ዝምታን መረጡ። እንደሚታወቀው በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ስታዲየሞች እየተሰሩ ናቸው እንጅ ብዙ ስታዲየሞች ለመጫወቻነት አልተዘጋጁም። ስለዚህ ያለንን ሀብት ለምን አንጠግነውም? ለምንስ ትኩረት አንሰጠውም?

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ የልማት ስራዎች ላይ ገንዘብ እያወጣች ናት። የሚወጣውን ገንዘብ በየዘርፎች በየባለሙያዎች ክትትል ይደረግባቸዋል። የዚህን ስታዲየም ጉዳይ የሚከታተል፣ባለቤት ነኝ የሚል መጥፋቱ ግን ግራ አጋብቶኛል። «ባለቤት ነኝ» የሚል ካለ ግን ወቀሳዬን ጠበብ አድርጌ ባለቤት የተባለውን ብቻ እናገራለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ጥቅም ያለውና የአገሪቷ ሊጎች (ብሔራዊና ፕሪሚየር ሊግ) የሚከናወኑበት ስታዲየም ተዘንግቶ ማየት የሚያሳዝን ነው። ስለዚህ ስታዲየሙ ወንበሮቹ ግማሾቹ ቀበሮ ጀምሮ የተወው ጉድጓድ የሚመስሉት ግማሾቹ ደግሞ መቀመጫቸው ተልጦ ባዶው ደረጃ የሚታይበት ምክንያት በአጭር ጊዜ እንዲቀየር ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል እላለሁ።

ሁሉም ሰው የሚቀመጥበት ወንበር ለመስራት የገንዘብ አቅም የለም ቢባል እንኳን ከኳስ መጫወቻዋ ውጭ ያሉት የሜዳው ክፍሎች ለምን ሳር አይለብሱም? ትንሽም ቢሆኑ ወንበሮቹስ ለምን አመቺና ብቁ አይሆኑም? የአካባቢው ጽዳትና ሳቢነትስ ስለምን ሊታሰብበት አልቻለም ያስብላል። የተረሳ ቦታ!

እግር ኳስ እኮ ሩጫ፣ትግልና ትንቅንቅ ያለበት ስፖርት ነው።ሲሆን ሲሆን በአበበ በቂላ ስም ስለተሰየመ የመሮጫ ትራክ ሊሰራለት ይገባ ነበር። ውብና ማራኪም መሆን ነበረበት። ካልሆነ ደግሞ ያሉት ትንሽ ነገሮች ጥራትና ደረጃ ሊታሰብበት ይገባል።

አዲስ አበባ ስታዲየም የመሮጫ ትራክ ተሰርቶለታል። አበበ ቢቂላ ስታዲየምም የዚህ ማዕረግ ባለቤት ቢሆንና የመሮጫ ትራክ ቢኖረው ለዚህም ባለሀብቶችና የሚመለከታቸው ፌዴሬሽኖች ቢያስቡበት። እጅግ በዘመናዊ መንገድም ባይሆን ቀለል ያለ ነገር ቢሰራለት የሚል እይታ አለኝ።

ወይም ደግሞ የመሮጫ ትራክ እንኳን ባይሰራለት ዙሪያውን እንዲታረስና እንዲስተካከል ቢደረግና ተጫዋቾች የስፖርት ቤተሰቦችና ሌሎችም እንዳይጎዱ ቢደረግ ጥሩ ነው እላለሁ። በዋናነት ግን የሚመለከታቸው የፌዴራልና የአዲስ አበባ የስፖርት ኮሚሽኖች ዝምታው ምንድነው?

በጀት የብዙ ነገሮች ምክንያት ሆኖ ይቀርባል። በእርግጥ የበጀት ችግር ሊያጋጥም ይችላል፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ታዳጊ አገር። ግን እስኪ ከአሁን በኋላ አበበ ቢቂላ ስታዲየምን ታድሶ እንየው።

እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ የስፖርት ቤተሰቦች አበበ ቢቂላ ስታዲም የተስተካከሉ ወንበሮች፤ ሳር የለበሱ የሜዳው ክፍሎች አምረውና ተውበው ማየት ይፈልጋሉ። ለዚህ ግን የሚቆጭ፣ የሚቆረቆርና ለውጥን በእጅጉ የሚፈልጉ የስፖርት አመራሮች ሊኖሩ ግድ ነውና ይታሰብበት። ሚናው ሊዘነጋ አይገባውም። ለአበበ ቢቂላና መሰሎቹ ተጨማሪ መጠሪያና መከበሪያ እንዲሁም ትውልድ የሚያስታውስበት ነገር መቆም ሲገባ የነበረው ሲጠፋና ሲንኮታኮት ማየት ሁሉንም ሊያስቆጭ ይገባዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment