Tuesday, February 03, 2015

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ይፋዊ የሙከራ ጉዞ (አዲስን በባቡር )

(ጥር 25/2007, (አዲስ አበባ))-- ከመስቀል አደባባይ እስከ ቃሊቲ ዲፖ ድረስ ያለው የተሽከርካሪዎች ብሎም የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ሃዲድ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች «ባቡር እንደገና» እያሉ ይነጋገራሉ። በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለቱን ታሪካዊ ክስተት ለመመልከት ግራና ቀኝ ማዶ ለማዶ እየተያዩ ቆመዋል። በዕለተ ሰንበት ከቤተ እምነት የሚመለሱ ምዕመናንም ቆም ብለው ትዕይንቱን በአግራሞት ይመለከታሉ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሰራተኞች በቃሊቲ ተገኝተዋል። የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ወደተግባር ተሸጋግሮ የባቡር ሀዲዶቹ ሽር የሚልባቸውን ባቡር ይጠባበቃሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች እንግዶች በመጀመሪያው የሙከራ ጉዞ ከቃሊቲ እስከ መስቀል አደባባይ ሽር ብለው በባቡር ተጉዘዋል። ነዋሪዎችም በየተራ እየገቡ ከቃሊቲ ወደ መስቀል አደባባይ እየተሳሳቁ ተንሸራሽረዋል። የባቡር ፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ጉዞም መርቀዋል።
 
የመጀመሪያው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር የሙከራ ጉዞ መጀመርን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደተናገሩት፤ መንግስት ለዜጎች የገባውን ቃል በተግባር እያሳየና ቃሉን እያከበረ ነው።
 

 
 
በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር መንግስት በሚገባ ማጤኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ «የትኩረት አቅጣጫም አድርጎ እየሠራ ነው» ይላሉ። ለዚህም ሲባል በአራቱም አቅጣጫ የሚንቀሳቀስና በሰዓት60ሺ ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዝ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያስገነዝባሉ። መንግስት የዜጎችን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከመቼውም በላይ የተጠናከረ መሆኑንና የዜጎችም ተሳትፎ በዚያው ልክ ማደጉን ያስረዳሉ። የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ስራ መጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
 
ለሶስት ወራት በሙከራ ሂደት የሚቆየው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታው ሲጀመር የበርካታ ሰዎችን ኃላፊነትና ርብርብ የጠየቀ እንደነበር ያስታውሳሉ። በቀጣይም የባቡር ሃዲዱን፣ የኤሌክትሪክ ሲስተሙንና ሌሎች የቀላል ባቡሩ አካል የሆኑትን ሁሉ በአግባቡ በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ ዜጎች ትልቅ ኃላፊነት አንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
 
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጀክት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እየፈሰሰበትና አያሌ የሰው ኃይል ጉልበት፣ እውቀትና ጊዜ እየተጠቀመ ነው። አገሪቷ በየብስ፣ ባህርና መንገድ ትራንስፖርት እንድትዘምን መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠቱንም ያረጋግጣሉ። ለአብነትም የአገሪቷ አየር መንገድ ከአፍሪካ ስመ ጥር መሆኑን ያስረዳሉ። ከኢትዮጵያ ጅቡቲ የሚዘልቀው የባቡር መንገድ ግንባታም 70 ከመቶ መጠናቀቁን ያመለክታሉ። የሁለቱም አገሮች መንግስታትም በቅንጅት ከመስራታቸውም በላይ ትስስሩን አጽንኦት እንደሰጡት ያረጋግጣሉ። አገሪቷን በዘመናዊ ትራንስፖርት ኔትወርክ በማስተሳሰር ኢትዮጵያን እጅግ የዘመነች አገር ለማድረግ እየተሰራ ነው።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አገሪቷ የጀመረችው የልማት ጉዞ በየጊዜው እየተፋጠነ ነው። በተለይም መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ብሎም በመላው አገሪቷ ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጋ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ዜጎችም ልማቱን ለማፋጠን ከመንግስት ጎን መቆማቸውንም ያመለክታሉ። መንግስትም ከዚህ የበለጠ የልማት ሥራ ለማከናወን ቁርጠኛና የኢትዮጵያን ህዳሴ በላቀ ሁኔታ ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተናገሩት።
 
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ስራ እስኪጀመር ድረስ በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበርና፤ ትናንት የተጀመረው የሙከራ ጉዞ ታላቅ ድል መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነሱም በላይ ከተማዋን የዘመናዊ ትራንስፖርት ባለቤት እንደሚያደርጋት ያስረዳሉ። ይህም ዜጎች ጊዜያቸውን ለመቆጠብ ትልቅ ጥቅም አለው። የፕሮጀክቱ ሥራ እስኪጀመር ድረስ በጉጉት እንደጠበቁት ሁሉ፣ አጠቃላይ አገልግሎቱና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በሙሉ የባለቤትነት ስሜት ለመጠበቅ ነው ቃል የገቡት።
 
የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታዎች በመሬት ውስጥ፣ በመሬት ላይና፣ ከመሬት ከፍ ብሎ በድልድይ ላይ የሚተላለፉ የመስመር ዝርጋታዎችን ያካተተ ነው። 39የመንገደኞች መሳፈሪያና መውረጃ ጣቢያዎችም አሉት። ለመኪና እና ለእግረኞች ማቋረጫዎች ሲኖሩ፤ በቀጣይም ለእግረኞች ማቋረጫ ተጨማሪ ድልድዮች ይገነባሉ። የአንዱ ባቡር ርዝመት 28ነጥብ8 ሜትር ሲሆን፤ የጎን ስፋቱ2ነጥብ65 ሜትር ነው።
 
ለፕሮጀክቱም 475 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን፤ 85 ከመቶ የሚሆነው ከቻይናው ኤግዚም ባንክ እንዲሁም15 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው። የባቡር ሃዲዱ34 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። የቀላል ባቡር ትራንስፖርቱን ከወራት በኋላ በሙሉ አቅም ለማስጀመር136 ሰልጣኞች «በትሬይን ማስተር»፤ 40 በባቡር ስምሪትና ቁጥጥር፣ 70በባቡር ጥገና፣ ስምንት ደግሞ በባቡር መሠረተ ልማት ጥገና በአጠቃላይ254 ሰልጣኞች በቻይና አገር ሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ ናቸው። አንዱ ባቡር 317 ተሳፋሪዎችን የመጫን አቅም አለው። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ 85 በመቶ ተጠናቋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment