Saturday, February 07, 2015

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በዚህ ዓመት 90 ሚሊዮን ይደርሳል

(ጥር 30 /2007, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በዚህ ዓመት 90 ሚሊዮን እንደሚደርስ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የህዝብ ትንበያ ሪፖርት አመለከተ። ኤጀንሲው በቀጣይ እስከ 2029 ዓ.ም ደግሞ የአገሪቷ ጠቅላላ የህዝብ ብዛት 136 ሚሊዮን እንደሚደርስም በሪፖርቱ ተገምቷል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 87 ነጥብ 9 ሚሊዮን መድረሱን በ2006 ዓ.ም የወጣው የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል። የኤጀንሲው የሥነ ህዝብ ቫይታል ስታትስቲክስ ዘርፍ ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትንና የወደፊት የህዝብ ዕድገት ብዛቷን የሚያሳይ የትንበያ መረጃዎችን ማዕከሉ አዘጋጅቷል።

በዚህም የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በ2000 ዓ.ም 75 ሚሊዮን እና በ2006 ዓ.ም 87 ነጥብ 9 ሚሊዮን እንደሚሆን ተገምቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በቀጣይ 30 ዓመታት 136 ነጥብ 7 ሚሊዮን እንደሚደርስና ይህም ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

በመሆኑም በአገሪቱ የሚታየውን የውልደት፣ የሞት፣ የፍልሰት መጠን፣ የቤተሰብ ምጣኔንና ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን መሰረት በማድረግና በግብአትነት በመጠቀም ትንበያው እንደተዘጋጀም አብራርተዋል።

እንደ አቶ አሳልፈው ገለፃ፤ የአገሪቱ ህዝብ ዕድገት ከኢኮኖሚ ዕድገቱ በአነስተኛ መጠን ሁለት ነጥብ አራት በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። «የአገሪቱ ህዝብ ቁጥር ከነበረበት ሁለት ነጥብ ስድስት ዓመታዊ እድገት ወደ ሁለት ነጥብ አራት መቀነሱ ጤናማ የሚባል እና ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር በተመጣጣኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም የሚያሳይ ነው።» ብለዋል።

ይሁንና አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የማይገልፅና ትክክለኛ የህዝብ ቁጥር ያላሟላ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ እያስተላለፉ ይገኛሉ። እነዚህ ተቋማት ከዚህ ተግባራቸው በመቆጠብ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እና ትክክለኛ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በከተሞች የሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥርም በአሁኑ ወቅት 19 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፤ በ2029 ዓ.ም 31 በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ሪፖርቱን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት የፈጀ ሲሆን ከመንግስታቱ ድርጅት የሥነ ህዝብ ፈንድ፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ትንተናው መዘጋጀቱን የማዕከሉ መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ የህዝብ ቆጠራ የህዝቡ ቁጥር 73 ነጥብ 8 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፤ አራተኛው የህዝብና የቤት ቆጠራ ደግሞ በ2010 ዓ.ም ይካሄዳል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

1 comment:

Anonymous said...

በኢትዮጵያ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ የህዝብ ቆጠራ የህዝቡ ቁጥር 73 ነጥብ 8 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፤ አራተኛው የህዝብና የቤት ቆጠራ ደግሞ በ2010 ዓ.ም ይካሄዳል:: WHAT DOES IT MEAN? 2010 HAS EXPIRED

Post a Comment