Friday, February 06, 2015

የ224 የውጭ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰረዘ

(ጥር 29 /2007, (አዲስ አበባ))-- በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ፈቃድ ወስደው ወደ ተግባር ያልተሸጋገሩ 224 የውጭ ድርጅቶች ፈቃድ መሰረዙን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ነጋሽ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ድርጅቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂ (አይ ሲ ቲ) እና በሌሎች ዘርፍ ተሠማርተው የነበሩ ድርጅቶች ናቸው። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሃምሳ ስምንት፣

በግብርና አርባ ዘጠኝ እንዲሁም በኮንስትራክሽን ሰላሳ አምስት ድርጅቶች ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡ መንግሥት በዋናነት በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን እና አይ ሲ ቲ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለሚሰማሩ የውጭ አገር ድርጅቶች ለሥራቸው የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን፣ የመገልገያና የግንባታ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡና የግብር እፎይታ ጊዜ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አቶ ጌታሁን አመልክተዋል።
መንግሥት እነዚህን ድጋፎች የሚያደርገው ድርጅቶቹ ወደ ተግባር በመግባት ለዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ፣ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ፣ በተጨማሪም ለመንግሥት ከምርቶቻቸው ከሚያገኙት ገቢ ግብር ይከፍላሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ እንደሆነም አቶ ጌታሁን ጠቁመዋል።

« ይሄን ማድረግ ያልቻለ ባለሀብት የመንግሥት ድጋፍ አያገኝም» ያሉት አቶ ጌታሁን፤ በመጀመርያም መሬት ሲያገኙ፣ ግንባታ ሲጀምሩ እና ወደ ተግባር መግባታቸው ሲረጋገጥ ብቻ ማበረታቻውን እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ድርጅቶችም ከዚህ ቀደም መንግሥት ባደረገው ድጋፍ ተጠቅመው ያስገቡት ዕቃ ካለም እንደሚመልሱ፣ አለበለዚያም ወደ ተመሳሳይ ድርጅት እንዲያስገቡ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ አኳያ አምስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መቶ ስምንት ፕሮጀክቶች ወደ ማምረቱ መሸጋገራቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታነህ፤ ፕሮጀክቶቹ ለ4ሺ484 ዜጎች ቋሚ እና ለ2ሺ 177 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት ፈቃድ ወስደው ረዘም ላለ ጊዜ ወደ ተግባር ያልገቡ ሦስት ሺ ድርጅቶች ፈቃድ መሰረዙን አቶ ጌታሁን አስታውሰዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment