Tuesday, January 20, 2015

የስፖርተኞቻችን የዕድሜ ጉዳይ ዕድሜ ይፍታው

(ጥር 12/2007, (አዲስ አበባ))-- ዕድሜ ጉዳይ ሲነሳ በአገራችን በርካታ አጨቃጫቂና ፈገግ የሚያሰኙ ገጠመኞችን በተለያዩ አጋጣሚዎች እናስተውላለን፡፡ ትክክለኛ ዕድሜያችንን ከመናገር ሽሽት «የፓስፓርት ወይንስ ...?»ዓይነት ቀልድ እንደተጀመረም እየሰማን ነው። የዕድሜ ጉዳይ በአገራችን በተለይም በስፖርቱ ዙሪያ የምንጊዜም መነጋገሪያ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

ስፖርተኞቻችን ሁሉም ባይሆኑም አብዛኛዎቹ ትክክለኛውን ዕድሜያችውን መናገር ሃጢያት የሚመስላቸው አሉ፡፡ የተጋነነ የዕድሜ እውነታዎችን ካለአንዳች መሸማቀቅ የሚናገሩም ጥቂት አይደሉም፡፡

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት መድፍ ተኳሽ የነበረ አንድ ስፖርተኛ አሁን ላይ ሃያ አምስት ዓመቴ ነው ብሎ እስከ መሞገትና ከጋዜጠኞች ጋር እስከ መጋጨት የደረሰበት አጋጣሚ አለ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንበል። ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተጠናቀቀ እንኳን ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ አስቆጥራል፡፡ በእዚያ ጦርነት አንድ ሰው መድፍ ለመተኮስ ቢያንስ ሃያ ዓመት ሊሆነው ይገባል፡፡

ይህን ያነሳሁት ያለፈ ታሪክ አንስቶ ለመወቃቀስ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነታን ከመካድ ስፖርተኞቻችን እንዲጠነቀቁ በማሰብ ነው፡፡ ለእዚህ ጽሑፍ መነሻነት ግብአት የሆነኝ ያለፈው ታሪካችን ሳይሆን ሰሞኑን በአሰላ ከተማ የተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው፡፡

ከእዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የስፖርተኞች የዕድሜ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሔ እያገኘ እንደሚሄድ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በእዚህ የወጣቶች ሻምፒዮናም ይህ ጉዳይ በመጠኑም ቢሆን ተቀርፎ አገኘዋለሁ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ተቀርፎ ወይንም ተቃልሎ ሳይሆን ስር ሰዶ ነው ያገኘሁት፡፡

አይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና ከአስራ ስድስት እስከ አስራ ዘጠኝ ዓመታችን ነው ብለው በወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ከሚሳተፉት ስፖርተኛች አባዛኞቹን በማየት ብቻ ዕድሜያቸው ትክክለኛ አለመሆኑን መገመት ይቻላል፡፡

ብዙ ጊዜ አይቶ መፍረድ በዕድሜ ጉዳይ ላይ ከባድ ቢሆንም ከተክለ ሰውነትና አቋም በመነሳት ወጣትና አዋቂን መለየት ያን ያህል አዳጋች ሊሆን አይችልም። ነገር ግን አንድ ስፖርተኛ «አስራ ስምንት ነኝ» ብሎ ድርቅ ካለ ምን ማድረግ ይቻላል? ዘመናዊው የዕድሜ መመርመሪያ ወይንም ኤም አር አይ የተባለው ቴክኖሎጂ ወደ አገራችን ገብቶ እስኪገላግለን ድረስ ዝም ብለን ተቀምጠናል።

ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በአገራችን መግባቱ አይቀርም። እስከዚያ ግን የስፖርተኞቻችንን የዕድሜ ጉዳይ ዕድሜ ይፍታው ብለን ከማለፍ የዘለለ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ስናደርግ አልታየንም። ቴክኖሎጂው የመጣ ጊዜ ግን ሃያን ማለፍ የሚፈሩት ስፖርተኞቻችን ምን እንደሚውጣቸው አናውቅም።

የስፖርተኞቻችንን ትክክለኛ ዕድሜ ለማወቅ ባይቻል እንኳን በተለያዩ ማስረጃዎች የዕድሜ ማጣራት ሙከራዎች ሲደረጉ እንመለከታለን። ነገር ግን ሙከራው ስኬታማ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል። ለእዚህ ደግሞ ተጠያቂው ስፖርተኛው ብቻ አይደለም። ክለቦች፤ አሰልጣኞች፤ የቡድን መሪዎችና ራሳቸው ፌዴሬሽኖች ጭምር ናቸው።

ክልሎችና ክለቦች እርስ በርስ ለመበላለጥ በሚያደርጉት ፉክክር ወይንም በልጦ ለመገኘት በወጣቶች ፈንታ ዕድሜያቸው የማይፈቅድና ልምድ ያዳበሩ ስፖርተኞችን ከማወዳደር ወደ ኋላ አይሉም። በየትኛውም ሻምፒዮና ክለቦችም ይሁኑ ክልሎች በዕድሜ ጉዳይ ላይ ኃላፊነት ተሰምቷቸው ወደ ውድድር ሲመጡ አላየንም። በአንዳንድ አጋጣሚዎች በትክክለኛው ዕድሜ ስፖርተኞችን ይዘው የሚቀርቡ ተሳታፊዎች ዕድሜ ባጭበረበሩት የበላይነት ይወሰድባቸዋል። ታዲያ በሌላ ጊዜ ሲመጡ እነዚህ ተሳታፊዎች እንዴት ትክክለኛውን ስፖርተኛ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች በተለያዩ ውድድሮች በሚያስመዘግቡት ስኬትና በሚወስዱት ዋንጫ መሠረት ከክለባቸው ወይንም ክልላቸው ማዕረግ ወይንም ሹመትና ሌሎች ጥቅሞችን እንደሚያገኙ ግልፅ ነው። ይህ ዓይነቱ ጉዳይ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ከአገሪቱ ስፖርት ይልቅ ስለ ራሳቸው ጥቅም እንዲያስቡ እያደረ ጋቸው ነው።

ከስር ጀምሮ ወጣቶችን በመኮትኮት ትክክለኛ ሥራ የሚሰሩ ብዙ አሰልጣኞች እንዳሉ ማንም ያውቃል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አሰልጣኞችና ስፖርተኞቻቸው ለጥቅም በሚሮጡ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ተውጠው እንጂ እምብዛም ጉልተው ሲወጡ አንመለከትም፡፡

ፌዴሬሽኖች በተለያዩ ውድድሮች የሚያዘጋጁት የዋንጫ ሽልማት መቅረት አለበት ባይባልም አገርን የሚወክሉና በዓለምአቀፍ ደረጃ አገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞች በሚመረጡባቸው ውድድሮች ላይ የዋንጫና ሌሎች ሽልማቶች ቢቀሩ አይጎዳም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሽልማቶች የስህተት ምንጮች ሲሆኑ እያየን ነውና፡፡

በመጪው ወር ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው አስራ ሁለተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ለመወዳደር ዘመናዊ የዕድሜ መመርመሪያ ማሽን ላይኖር ይችላል፡፡ ምናልባትም ውድድሩ በዕድሜ ጉዳይ ላይ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ግን ውድድር ላይ የምናቀርበው ስፖርተኛ ትዝብት ላይ እንዳይጥለን መጠንቀቅ አለብን፡፡ የበርካታ ጀግና አትሌቶች መፍለቂያ የሆነች አንድ አገር በዕድሜ ጉዳይ በአይ ደብል ኤፍ ትዝብት ላይ መውደቅ የለባትም፡፡

ኬንያውያን አትሌቶችን እያመሰ የሚገኘው የአበረታች ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚነት በእኛ አገር አትሌቶች ላይ ዝር አለማለቱ አኩርቶናል፡፡ የዕድሜ ጉዳይም ከአበረታች መድኃኒት ተጠቃሚነት ተለይቶ መታየት የለበትም። ስለእዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመልካም ተምሳሌታችን መገለጫ የሆነውን አትሌቲክስ ጥቁር ጥላ እንዳያጠላበት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment