Monday, January 19, 2015

''ጥምቀት ከሃይማኖታዊነቱ ባለፈ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነታቸው መገለጫ ነው''

(ጥር 11/2007, (አዲስ አበባ ))-- ''የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ ባሻገር፤ለመላው ኢትዮጵያውያን የአንድነታችን፣የእኩልነታችን፣ የባህላችንና የአብሮነታችን መገለጫ የሆነ የማይበጠስ የአንድነት ገመድ ነው'' ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገለፁ።አቡነ ማቲያስ ዛሬ የጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ ሲከበር እንደተናገሩት የበዓሉ አስተምህሮ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን  አንድነታቸውን ፣ፍቅራቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው ለዘመናት ለመቆየት አስችሏቸዋል።

በዓለ ጥምቀት ዘር፣ ብሄር ፣እድሜ ፆታ ቀለምና ቋንቋ ሳይገድባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያከብሩት ትውፊታዊ በዓል መሆኑንም አስረድተዋል። በመሆኑም በዓሉ ከሃይማኖታዊ ተልዕኮው ባሻገር፤ የፍቅር የሰላም የደሰታ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ይህን ለዘመናት የቆየውን ባህል ጠብቀው አክብረው ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

''እነዚህ እሴቶች ለሰው ልጅ የተስተካከለ አኗኗር እጅግ አስፈላጊ ናቸውና ጠብቀን ተጋግዘን ከተጓዝን የማንወጣው ተራራና የማንሻገረው ወንዝ አይኖርም’’ ሲሉ ቅዱስነታቸው አክለዋል። በዘመናችን ልማቱና እድገቱ፡ መከባበሩና ወንድማማችነቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ እየጎለበተ የመጣው እኩልነትና ሰላም በመረጋገጡ መሆኑንም ፓትርያርኩ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ''ዛሬ፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያም ሰላምና እኩልነት ፍትሃዊና ህዝባዊነት ቦታ ሊነፈጋቸው አይገባም'' ያሉት አቡነ ማቲያስ፣መርሆዎች የሁሉም የሀይማኖቶች ዋና ምሰሶዎች ከመሆናቸውም ባሻገር የልማትና እድገትን ዘላቂ ዋስትና ናቸውና ከማንም በላይ ልንጠነቀቅላቸው ይገባል''ብለዋል።

ብፁዕነታቸው እንደገለፁት የጥምቀት በዓል ለሁሉም ህዝብ ከመንፈሳዊ ተልዕኮው በተጨማሪ እርስ በርስ የሚከባበርበት፣ የሚረዳዳበትና አብሮነቱን የሚያጠናክርበት እንደሆነ ተናግረዋል። በጥምቀት በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት ሁሉም ከተንኮልና ከመጥፎ ድርጊቶች እርቆ  አቅመ ደካሞችን አረጋወያንን በመርዳትና  በማሰብ በዓሉ እንዲከበር ሃይማኖቱ አጥብቆ እንደሚያስተምርም ፓትርያርኩ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሊቀ መምህር ፋንታሁን ሙጬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በዓሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውና በአገሪቱ ገፅታ ግንባታው ሂደት የሚያደርገው አስተዋጽኦ እያደረገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዓሉ እንደመስቀል በዓል ሁሉ በዓለም የማይዳሰሱ የቅርስ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ቤተክርስቲያኒቱና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የተጀመረውጥናት እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

ቅርሱ ከተመዘገበ በኋላም የበዓሉን አከባበር የዓለም ህዝብ የበለጠ እንዲያውቀውና አሁን ካለው በበለጠ ጎብኚዎች ለማምጣት እንደሚ ያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል።እንደ መምሀሩ ገለፃም የጥምቀትን በዓል የሚጎበኙ ቱሪስቶች በየዓመቱ እያደገ መጥቷል።

የበዓሉ አከባበር በዓይነቱ የተለየና አስደናቂ በመሆኑና በኢትዮጵያ እጅግ ከሚያምሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት አንዱ መላው አለም ሊያየውና ለያደንቀው ይገባል ያሉት ደግሞ ዶክተር ቦብ አሌክሳንደር የተባሉ አውስትራሊያዊ ጎብኚ ናቸው። ''በኢትዮጵያ ያየሁትን የጥምቀት በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት መቼም አልረሳውም። ስለሆነም ይህን ልዩ በዓል ሌላውም መጥቶ ንዲጎበኘው የበኩሌን አደርጋለሁ'' ሲሉም አስተያየታቸውም ሰጥተዋል።

በመላው አገሪቱ የጥምቀት በዓል ዛሬ በከፍተኛ ድምቀት ሲከበር ውሏል።ትናንት ከዐብያተ ክርስቲያን የወጡ ታቦታት ዛሬ ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል።ሕዝበ ክርስቲያኑም ታቦታቱን በማጀብ ወደ ማረፊያቸው አስገብቷቸዋል።
ምንጭ:  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment