Monday, January 26, 2015

ይድረስ «በሬ ሆይ ሳሩን አየህና...» ሆናችሁ ለቀራችሁ ጋዜጠኞች

(ጥር 16/2007, (አዲስ አበባ))--ድሮ ነው አሉ። በጣም ድሮ ድሮ፡፡ እጅግም ሲበዛ የሚዋደዱ ሁለት ጎረቤታሞች ነበሩ። በሙያቸውም ብቻ ሳይሆን በኑሯቸውም ጭምር ተመሳሳይና ከእጅ ወደ አፍ የሚሉቱን ዓይነት ኑሮ የሚገፉ አራሽ ገበሬዎች። እነዚህ ጎረቤታሞች ከገቡበት የኑሮ አዙሪት ለመውጣት ያልማሱት መሬት፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ግና የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ሆኖ ነው መሰል የሰዎቹ ኑሮ ከእለት ጉርስ ተርፎ ጠብ የሚል ነገር አልገኝበት አላቸው።

በዚህ መሐል ግን የአንደኛው ጎረቤት ኑሮ ድንገት መለወጥ ጀመረ። ድንገትም ቤቱ፣ ድንገትም ልጆቹ፣ ድንገትም መብላቸው ሁሉ የድሮውን አልመስል አለ። ደሳሳዋ ጎጆ በቆርቆሮ፤ የአጋም አጥሩም በድንጋይ ክምር ተተካ። ሰውም ጉድ አለ። «ምን አግኝቶ ይሆን?» ሲልም የመሰለውን ሁሉ አወራ። ያ ምስኪን ጎረቤትም በወዳጁ ድንገት ሀብት ማፍራት ተገርሞ ሲያበቃ ከዕለታት በአንዱ ቀን «እስኪ መላውን ለእኔም ቢነግረኝ» ብሎ ወደ ቤቱ ለመሄድ ወሰነ። ተነስቶም ወደዚያው አቀና፡፡ ከወዳጁ ደጃፍም ደረሰ፡፡ ድሮ ገፋ አድርጓት ይገባ የነበረች ደሳሳ በር ዛሬ የለችም። በምትኳ አርበ ሠፊና አብረቅራቂ በር ተተክቶበታል።

ምስኪኑ ጎረቤትም እየተገረመ በሩን አንኳኩቶ ሳይጨርስ ሰማይ ምድሩን የሚያደባልቅ የውሻ ጩኸት አካባቢውን ሞላው። እንደ መደንገጥም እያለ በሩን ደግሞ ሊያንኳኳ ገና እጁን ከማንሳቱ «ማነው?» የሚል አስገምጋሚ ድምፅ ከውስጥ ሰማ። ራሱን አስተዋውቆ ሲያበቃ በሩ ተከፈተለት። ወደ ውስጥም ዘለቀ።

ምስኪኑ ሰው በውሻ ጩኸት ታጅቦ በዘበኛው እየተመራ ወደ ቤቱ ውስጥ እንደዘለቀም ያ የቀድሞ ወዳጁን ገበታ ላይ አገኘው። ኖር ተብሎም እነርሱን ይመስል ዘንድ ተጋበዘ። ለእጁ ውሃ ቀርቦለት ታጠበና አብሮ ተሰየመ። ምስኪኑ ጎረቤት የምግቡን ዓይነትና ብዛት ቆጥሮ ሳይጨርስ ጠቁሞ ያዘጋጀውን ጉርሻ ወደ አፉ ጨመረውና በግርምቱ ላይ ሌላ ግርምት አከለበት። እንዲህም ያለ የምግብ ጣዕም፣ እንዲህም ያለ እጅ የሚያስቆረጥም ምግብ እንኳንስ በልቶ ዓይቶም ስላለማወቁ ራሱ ለራሱ ነገረው።

የገበታው መስተንግዶ እንዳበቃም ምስኪኒ ጎረቤት የመጣበትን ሊያወጋው ዳር ዳር ማለት ጀመረ። ሲፈራ ሲቸርም « ወዳጅ ሆነን ሳለ እንደው ድንገት እንዲህ ያለ ሀብት ባለቤት ስትሆን መላውን ምነው ሳትነግረኝ?» ሲልም ጠየቀው። ጎረቤትየውም መልሶ «ምን ላርግ ብለህ ነው ሥራ በዝቶብኝ ከአገር አገር ስዞር እኮ ነው» ሲል ምክንያቱን ነገረው።

«ይሁን። ግን እንደው ምን ብትሠራ፤ ምንስ ብታገኝ ነው እንዲህ ያለ ሀብት በአንድ ጊዜ ማፍራት የቻልከው?» ሲል ጠየቀው። ያም ጎረቤት መልሶ ምን ችግር አለው ወዳጄ ላንተ ያልሆነ ለማን ሊሆን ነው ብሎ ሁሉንም ነገር ይነግረው ጀመር። «እነዚያን የምታውቃቸውን ከብቶቼን በሙሉ ሸጥኩና ወደ ከተማ ሄጄ እዚህ እኛ አገር የሌሉ ከብረት የተሠሩ የተለያዩ በርካታ ቁሳቁስን ገዝቼ አመጣሁ። ወደ ገበያም ወስጄ በውድ ዋጋ ለገበሬዎች ሸጥኩላቸው። በዚህ መንገድ አንድ ሦስት አራት ጊዜ ከተመላለስኩ በኋላ የምታየውን ሀብት ሁሉ አፈራሁ» አለው። ምስኪኑ ጎረቤትም የቀድሞ ወዳጁን አመስግኖ እርሱም እንደተመከረው ሊያደርግ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ቤቱ እንደደረሰም ማንንም ሳያማክር በበረት ያሉ ከብቶቹን ሁሉ አውጥቶ ወደ ገበያ ነዳቸው። ገበያው በሰጠው ዋጋም ሁሉንም ሸጦ ጨረሰና ወደ ተባለው አገር አቀና። እዚያም እንደደረሰ ከብረት የተሠራ አንድም ዓይነት ዕቃ ሳይቀረው ሁሉንም ሸምቶ ወደ አገሩ መመለስ ጀመረ። ነገር ግን የአገሩ መንገድ አቀበት የበዛበት ነበርና በቀላሉ የሚገፋ አልሆነም። የተሸከመውን የብረት መአት እያነሳ እየጣለ እርሱም እየወደቀ እየተነሳ ጥቂት ቢጓዝም አልሆንልህ አለው። ሌሎች መንገደኞችም ያግዙኛል ብሎ ዓይን ዓይናቸውን ቢያይ «አይዞህ ድረስብን» ከማለት ውጪ የፈየዱለት ነገር አልነበረም።

ጀንበር አዘቀዘቀች። ገበያተኛው ሁሉ ወደ አገሩ ሳይጨልምበት ለመድረስ ይፈተለክ ያዘ። በዚህ መሀል ታዲያ አንድ የሚያውቀው ሰው ምስኪኑ ገበሬ ከተቀመጠበት ስፍራ ደርሶ «ምነው ወዳጄ ምን ሆነሃል? እየመሸም አይደል ተነስ እንጂ እንሂድ» ሲል ጠየቀው። ያ መከረኛ ገበሬም የሆነውን ሁሉ አጫወተውና «ወዳጄ ያልኩት ጎረቤቴ ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ ቀርቶ ይኸው ጉድ ሠርቶኝ አረፈው» ሲል ብሶቱን ተነፈሰ። መንገደኛውም ከከተማ የሸመተው በርካታ ዕቃ ነበረውና ሊያግዘው ባለመቻሉ ሲበዛ አዘነ። በመጨረሻም «በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ» ሲል ተርቶበት ጉዞውን ወደፊት ቀጠለ። ምስኪኑ ገበሬም ትርፍ ፍለጋ ወጥቶ የጅብ እራት ሆኖ ቀረ አሉ።

ነገሬ ወዲህ ነው።
እንዲህ እንደተረቱ አጉል ምክር ሰምታችሁ የምትወዷትን አገራችሁን ትታችሁ በሰው አገር ሆናችሁ ወደሌላ የሰው አገር ለመሻገር ደጅ እየጠናችሁ ያላችሁ ውድ የሙያ መሰሎቼ ሰላሜ ካላችሁበት ይደርሳችሁ ዘንደ ምኞቴ ነው። ሀገራችሁና እኛ ወገኖቻችሁ ሰላም መሆናችንን ስንገልጽ የጀመርነው ብሩህ ጉዞ ተጠናክሮ እንደቀጠለ መሆኑንም በማስታወስ ነው። ባለችሁበት ኬንያ ተቸግራችሁም ብቻ ሳይሆን ተሳቃችሁም እንደምትኖሩ ሰሞኑን ከወዳጃችሁ የሲ ፒ ጄ ድረ ገጽ አንድ ዘገባ ላይ አንብቤ አዘንኩ፡፡ በእውነት ችግራችሁ በእኔ ላይ የደረሰ ያህል ጠልቆ ተሰምቶኛል፡፡ ግን ወዳችሁ የገባችሁበት ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም ስል መልሼ ተጽናናሁ፡፡

ባልኳችሁ ዘገባ ላይ ማነው ስሙ ኒኮል ሺሊት የተባለው ሰው (ጋዜጠኛ ያላልኩት የጋዜጠኝነት አንዱና ዋነኛ መርህ የሆነውን ሚዛናዊ የማድረግ ነገር በድርሰቱ ላይ ስላላየሁበት ነው) እናንተን ባላችሁበት ስፍራ ድረስ መጥቶ አነጋግሯችሁ የሠራላችሁን ዘገባ ሳነበው ሲበዛ ተገረምኩ፤ ከብዙው በጥቂቱ ቆንጥሬ ላስታውሳችሁማ፤  «አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ወደ እዚህ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነው የተሰደዱት፤ ወደ ዩጋንዳ መዲና ካንፓላም የተሰደዱ ሌሎች ጋዜጠኞችም አሉ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል በርካታ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ እስከዛሬ አላየንም። በዚህ ዓመት ከኢትዮጵያ የተሰደዱት ጋዜጠኞች ቁጥር ወደ 30 ደርሷል። ሁሉም ጋዜጠኞች ሀገራቸውን ጥለው የወጡት ደግሞ ክሱን በመፍራት ነው።»

ይሄ የሲ ፒ ጄው ሰው ያላችሁትን እንጂ የነበራችሁበትን ባለማወቁ የሠራው ድረሰት ቢያንስ ለእርሱ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ እኔና እናንተ ግን በደንብ ስለምንተዋወቅ የተባለችዋ ሁሉ እንደ ምስኪኑ ገበሬ ለትርፍ ፍለጋ የተደረገች መሆኗን አንወሻሽም። ምክንያቱም አውሮፓና አሜሪካ ገብተው የስደት ኑሮ የሚኖሩ መሰሎቻችሁ የነገሯችሁን ሰምታችሁ አገራችሁን ጥላችሁ የወጣችሁ የዚህ ዘመን ምስኪን ገበሬዎች ስለመሆናችሁ እንተዋወቃለንና፡፡

ያ ባይሆንማ ኖሮ ገና ለገና ጋዜጣ ላይ ተጻፈብኝ ተብሎ አገር ተጥሎ የሚወጣው እንዴት ተደርጎ ነው? መንግሥት እናንተን ማሰር ከፈለገ ለምን አገር ጥላችሁ እስክትሄዱ ይጠብቃል? አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተጻፈብን የምትሉት ዘገባም ቢሆን በባለሙያዎች የተጠናና ትክክለኛ ማንነታችሁን ያሳየ ትነግሩኝ የነበርውንም ይፋ ያወጣ ሀቅ ነው። እናንተ በትክክል ጋዜጠኞች ብትሆኑ ኖሮ ግን የአዲስ ዘመንን ዘገባ በራሱ በአዲስ ዘመን ላይ እንኳን ቢቀር በራሳችሁ ጋዜጣና መፅሄት መቃወምና በተመሳሳይ ጥናት ፉርሽ ማድረግ ትችሉ ነበር። በእርግጥ ውሸት ከሆነ ማለት ነው። ያንን ግን አላደረጋችሁም። ምክንያቱም መጀመሪያም ቢሆን የእናንተ ዓላማ ከመንግሥት ጋር በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ መጋጨትና ተፈላጊ መምሰል ከዚያም አገር ጥሎ መሄድ ነበር። ያንንም በተራዘመ ጉዟችሁ አደረጋችሁት።

ምናልባት ይሄንን ጽሑፍ በብዕር ስሜ ስለጻፈኩት ማንነቴን በውል ባታውቁትም አብረን ብዙ ቦታዎችን የተጓዝን፣ አብረንም ብዙ ሥራዎችን ሳይቀር የሠራንና ብዙ ብዙ ነገሮችን ያወራን የሙያ ቢጤያችሁ ስለሆንኩ ምን ትጽፉ እንደነበርም ብቻ ሳይሆን ለምን ትጽፉ እንደነበርና የማንን አጀንዳ ታስፈጽሙ እንደነበር እንደማውቅ እናንተም ታውቃላችሁ። በግልጽ እናወራ ነበርና። እዚህ በነበራችሁበት ወቅት ትሠሩት የነበረውን በተመለከተ አስተያየት ስሰጣችሁ፤ እኔም በምጽፈው ዙሪያ ስታወሩኝ ምን እንባባል እንደነበር ታስታውሳላችሁ? «አንተ የምትሠራው የካድሬ ሥራ ነው» ስትሉኝ ለምን ስላችሁ «ልማት ምናምን እያልክ የምትጽፈው ጽሑፍ ለዚህች አገርና ሕዝብ ምን ፈየደላት? ይልቁንም ጥቅሙ ለገዥው ፓርቲና ለመንግሥት ነው።» ትሉኝ እንደነበር የምትረሱት አይሆንም። እናንተ የምትጽፉትም ቢሆን ሕዝብንና መንግሥትን የሚያቃቅር እንጂ ለዚህች አገር የሚጠቅማት ነገር የለውም ስላችሁ አዘውትራችሁ ትሉት የነበረው «ይሄ መንግሥት ለዚህች አገር ስለማይበጃት መቀየር አለበት» ነው። መቀየሩ ተፈጥሯዊ ቢሆን እንኳን በሰላምና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሆን የምትፈልጉ አይመስለኝም።

እንዴት ተብሎስ ነው ጋዜጠኛ የመንግሥት ቅያሬን አጀንዳ ይዞ የሚሠራው? በየት አገር ያለ ጋዜጠኝነት ይሆን? እናንተ ያላችሁባቸው ከተሞች ጋዜጦችን እስኪ አንሱና ተመልከቷቸው። በእርግጥ እንደናንተ መርዶ ነጋሪ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አፈቀላጤ ናቸውን? በጭራሽ። ያን ቢያደርጉ አንድ ቀን ውለው እንደማያድሩ የአገሪቱ ሕግ እማኝ ነው። እዚህ እኛ አገር ግን አሥራ ምናምን ዓመት ከጋዜጠኝነት መርህ ውጪ የሆነ ሥራ እየሠሩ ዛሬም ድረስ በሆደ ሠፊነት የታለፉ እንደ እናንተ ዓይነት ሰዎች እንዳሉ የሚታወቅ ነው።

እኔ እስከማውቀው ድረስ የዓለም ፕሬስ በሁለት ሰፋፊ ፈርጆች ሊከፈል ይችላል። በመንግሥት እና በግል የሚታተሙ ወይም ብሮድካስት የሚሆኑ ተብሎ። የእኛ አገር ግን የተለየ ነው። የመንግሥት ፕሬስ አለ፤ የግልም አለ፤ ሦስተኛውና ለጊዜው ስያሜ ያጣሁለት የእናንተ ዓይነቱ ፕሬስም አለ። እስኪ ዛሬ ላይ እንኳን ሆናችሁ ትጽፉ የነበረውን ነገር ታገለግሉ የነበረውን አካልም መለስ ብላችሁ አስታውሱና ቢያንስ ትክክል አለመሆናችሁን እመኑ። ካለፈ ስህተት መማርንም ልመዱ።

የእናንተ የጋዜጠኝነት ብዕር ሳይኖር የሞተ በመሆኑ በጣም አዝናለሁ። ከእናንተ ቀድመው አውሮፓና ኬንያ የገቡት ጓደኞቻችሁ ያገኙትን ቱሩፋት (ቱሩፋት ከተባለ ማለት ነው) ማግኘት ፈልጋችሁ የማታምኑበትን ስታደርጉ ኖራችሁ፤ በመጨረሻም ያው እብስ አላችሁ። ለማነኛውም ግን ዛሬም አዲስ ዘመን ጋዜጣን ይዛችሁ ሳይ ከገባችሁበት አዙሪት አለመውጣታችሁን ተረዳሁ።  በነገራችን ላይ እናንተ አውሮፓና አሜሪካን ዓላማ አድርጋችሁ ትሠሩ እንደነበር ያረጋገጠ ሌላ ሀቅም ሰሞኑን ደርሶኛል።

«ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከመንግሥት ጋር ተደራድሬ ወደ አገራችሁ ልመልሳችሁ፤ ለደህንነታችሁም ዋስትናውን እኔ እወስዳለሁ» የሚል አማራጭ አቅርቦላችሁ እንቢ ማለታችሁን ወፏ ሹክ አለችኝ። ድርጅቱ ሁለተኛም አማራጭ አቅርቦላችሁ በእንቢተኝነታችሁ ጸንታችኋል አሉ። «ባላችሁበት አገር ከመንግሥት ጋር ተደራድሬ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ላውጣላችሁ» ብሏችሁም እንብየው ማለታችሁ በትክክልም ምን እንደምትፈልጉ ለምንም ትሠሩ እንደነበር ታውቆባችኋል።

ለማንኛውም ግን ወደ ቀልባችሁና ወደ ትክክለኛው መስመር እስክትመለሱ ድረስ መልካም መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋላሁ። ያሰባችሁት ቢሳካም ባይሳካም አገራችሁ ግን በሆደ ሠፊነት እጆቿን ዘርግታ እንደምተቀበላችሁም እምነቴ ነው። አለበለዚያ ግን እንደ ምስኪኑ ገበሬ ሆናችሁ ከመቅረታችሁ በፊት አስቡበት።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment