Tuesday, January 13, 2015

የዳኝነት ነፃነት፣ግልፅነትና ተጠያቂነት በኢትዮጵያ

(ጥር 4/2007, (አዲስ አበባ))--ግልፅ የሥልጣን ክፍፍል ባላቸው ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ነፃነቱ የተጠበቀ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር የተላበሰ የዳኝነት አካል መኖር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደ ቁልፍ መሳሪያ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ በውድድር ሕግ የሚመራ የገበያ ሥርዓት ለመገንባት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋትም ሆነ የተረጋጋ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ዕውን የማድረግ ራዕይ ማሳካት የሚቻለው ከማንኛውም ተፅዕኖና ጫና ነፃ የሆነ ሕግንና ፍሬ ነገርን ብቻ ተመስርቶ አለመግባባቶችን መመርመር፣ መወሰንና ውሣኔውን ማስፈፀም የሚችል ጠንካራ ፍርድ ቤት መገንባት ሲቻል መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ የፍትህ ታሪክ ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠረ ቢነገርም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችልና የዜጐች ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የሚያስከብር ነፃ የዳኝነት አካል እንዳልነበረ ከትናንት የታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1923ዓ.ም የተጻፈ ህገ-መንግሥት በፊት እንደ ህገ-መንግሥትና ህግ ሲያገለግሉ የነበሩ የተለያዩ የህግ ሰነዶች እንደነበሯት ይታወቃል፡፡

እነዚህ ፍትሐ-ነገሥት፣ ክብረ-ነገሥትና ሥርዓተ መንግሥት በመባል የሚታወቁ ሰነዶች በአብዛኛው ኃይማኖታዊ ይዘት የነበራቸውና ከቤተ-መንግሥቱ ደጃፍ ውጪ ብዙም ፈቀቅ ያላሉ ስለነበር እንደ ህግ በሀገሪቱ በሙሉ በተግባር ላይ ውለዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡  ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በፈቃዳቸው ለህዝቡ በስጦታ መልክ ያበረከቱት የ1923ዓ.ም ህገ-መንግሥትም ቢሆን የህግ የበላይነትን የማይቀበል እና ዜጐች በህግ ፊት እኩል ናቸው የሚለው መርህ ተጥሶ ንጉሡ የማይከሰሱ በእግዚአብሔር የተመረጡ ልዩ ፍጡር መሆናቸውን በግልፅ የደነገገ ስለነበር የዳኝነት አካሉ ያን ያህል ቦታ ነበረው ማለት አይቻልም፡፡

በ1923ዓ.ም ሆነ በተሻሻለው የ1948ዓ.ም ሕገ-መንግሥት የዳኝነት ሥራን በተመለከተ የተነካኩ ጉዳዮች ቢኖሩም ዳኞች ፍርድ ይሰጡ የነበሩት በንጉሠ ነገሥቱ ስም በመሆኑ ተጠያቂነታቸውም ለሕግና ለህሊናቸው ሳይሆን ለንጉሱና ለባለሟሎቻቸው ነበር፡፡ ዳኞች የሚሾሙት በአካባቢ ገዥዎችና በንጉሠ ነገሥቱ አፅዳቂነት ስለሆነ ንጉሡ ባሻቸው ጊዜ ከዳኝነት ሥራቸው ለማንሳትም ሆነ ለመሻር ሙሉ ሥልጣን ስለነበራቸው የሕግ ማዕቀፉ ዳኞች ያለሥጋትና ጫና ነፃ ሆነው ውሣኔ የሚሰጡበት ሁኔታ አልፈጠረም፡፡

ከዚህም ባሻገር ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በቀጥታ ፍርድ የሚሰጡበት የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ የዙፋን ችሎት በሚል የሚታወቅ ከፍተኛ የዳኝነት አካል ይመሩ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ንጉሠ ነገሥቱ ሀገርን ከማስተዳደር የአስፈፃሚ ሥራቸው በተጓዳኝ የመጨረሻው የዳኝነት ሥልጣን ባለቤት በመሆን የዳኝነት ተግባርም ያከናውኑ ነበር፡፡ ስለሆነም በንጉሡ ዘመን በሦስቱም የመንግሥት አካላት መካከል ግልፅ የሥልጣን ክፍፍል ያልነበረና ንጉሠ ነገሥቱ ሁሉንም አካላት ጠቅልለው የያዙበት ወቅት ስለነበር ስለ ነፃ የዳኝነት አካል መናገር የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ኢትዮጵያ ያለ ሕገ-መንግሥት ለ13 ዓመታት የተመራችበት ዜጐች ወደ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ በየመንገዱ የሚገደሉበት እና የሚታሰሩበት ወቅት ስለነበር ፍርድ ቤቶች ከማንኛውም ዘመን በላይ የዳኝነት ሥልጣናቸው የተዳከመበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የ1980ዓ.ም የደርግ ሕገ-መንግሥትም ቢሆን ዳኞች እንደ ተመራጮች የሥራ ዘመናቸው በአምስት ዓመት የተገደበበት፣ የዳኞች የሥራ ዋስትና የጠፋበት እና የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ሁሉንም የመንግሥት አካላት የመቆጣጠር ሥልጣን የሰጠ ሕገ-መንግሥት ስለነበር ስለ ነፃ የዳኝነት አካል መቋቋም የሚታሰብ አልነበረም፡፡

ፍርድ ቤቶች ከሦስቱም የመንግሥት አካላት መካከል አንዱ መሆናቸው ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና አግኝተው መስራት የጀመሩት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡ በተለይ የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ መሆኑንና ነፃ የዳኝነት አካል መቋቋሙን መደንገጉ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ታሪክ ልዩ ሥፍራ እንዲይዝ አድርጐታል፡፡ ፍርድ ቤቶች እንደ ተቋም ከሕግ አውጪው እና ከህግ አስፈፃሚው ውጪ ሆነው ሶስተኛ የመንግሥት አካል መሆናቸውን በህገ- መንግሥቱ አንቀፅ 79/1/ ሰፍሯል፡፡ ይህንን ተከትለው በወጡት አዋጅ ቁጥር 25/1988 እና ማሻሻያዎቹ ደግሞ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሚባሉ ሦስት እርከኖች እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡

የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 79/2/ በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል ከማንኛውም ባለሥልጣን ይሁን ከማንኛውም ሌላ ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ በተያያዘም በአንቀፅ 79/3/ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት እንደሚያከናውኑ እና ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ እንደማይመሩ ይገልፃል፡፡

የዳኝነት ነፃነት ሲባል ፍርድ ቤቶች እንደተቋም ያላቸው ነፃነትና የዳኞች የመወሰን ነፃነትን የሚያካትት ነው፡፡ ተቋማዊ ነፃነት ሲባል የዳኝነት አካል በሥልጣን ክፍፍል ረገድ ራሱን ችሎ በህገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 መቋቋሙን ብቻ ሳይሆን የዳኝነት አካሉ ዋና ተግባር የሆነው በተከራካሪ ወገኖች የሚነሱ ክርክሮችን መርምሮ በሕጉ መሠረት ውሣኔ የመስጠት ተግባሩን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስፈልገው በጀት በቀጥታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ማስፀደቅ እንደሚችል እና ውስጣዊ አስተዳደር ጉዳዩን እራሱ እንደሚወስን ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘቱ ጭምር ነው፡፡ ሙያዊ ነፃነት ሲባል ደግሞ አንድ ዳኛ የቀረበለትን ጉዳይ ሕግንና ሕግን ብቻ መሠረት አድርጐ እንዲወስን ከውስጥና ከውጭ ከሚደርስበት ማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲሰራ ሕገ መንግሥቱ ዋስትና ሰጥቶታል፡፡ ፍርድ ቤቶች የዳኞች የችሎቶችና የመዝገቦች አመዳደብ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የሚያከናውኑ መሆናቸው የዳኝነት ነፃነታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሌላው የዳኝነት አካል ነፃነት መገለጫ የዳኞች የዲስፒሊን፣ የዕድገት፣ የሹመት፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም የዕጩ ዳኞች ምልመላ ጉዳዮች ነፃና ገለልተኛ አካል በሆነው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት እነዚህን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች በመከተል የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እና አደረጃጀቶች ተዘርግተው ሥራ ላይ እንዲውሉ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ አንዱና ዋንኛው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 684/2002 ይገኝበታል፡፡ ጉባዔው በሕግ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሲሆን አወቃቀሩም ከሦስቱ የመንግሥት አካላት በተለየ መልኩ የተደራጀ እና አባላቱንም ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ ነው፡፡ ጉባዔው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነት የሚመራ ሆኖ ስብጥሩም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የዳኞች ተወካይ፣ የሕግ ትምህርት ቤት ተወካይ፣ የጠበቆች ማህበር ተወካይ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካይ፣ የታዋቂ ሰዎች ተወካይ፣ የፓርላማ አባላትና የአስፈፃሚው ተወካይን ያካተተ መሆኑ በራሱ ገለልተኝነቱን ያረጋግጣል፡፡

በዚህ መሠረት ጉባዔው የዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥልጠና መመሪያ በማውጣትና የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሥርዓቱ ይበልጥ ግልፅ ተአማኒና ብቃት ያለው ለማድረግ አመርቂ ሥራ ሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዳኝነት አካሉን የተጠያቂነት አሰራር ለማጐልበት የዳኞች የሥራ አፈፃፀም ምዘና ሥርዓት ደንብ በማውጣት ዳኞች ከምልመላቸው ጀምሮ በዳኝነት በሚሰሩበት እና ከዳኝነት ሥራቸው በሚሰናበቱበት ጊዜ ስለሚኖረው የዳኞች ብቃትና ሥነ-ምግባር ሁኔታና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ካለማንም ጣልቃ ገብነት በጉባዔው እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ይህም የዳኝነት አካሉ እንደ አንድ የመንግሥት አካል ያለበት የሕዝብና የመንግሥት ተጠያቂነት በአግባቡ እንዲፈፅም ያስችለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከዚህ በተጨማሪ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ተግባራዊ ካደረጉ ዋቸው አሰራሮች መካከል ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ የተጠያቂነት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ከግልፅነት አሰራር አንፃርም ከመዝገብ መክፈት እስከ ፍርድ አፈፃፀም ያለው የፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰጣጥ አሰራር በአደባባይና በግልፅ ችሎት የሚከናወን ስለሆነ ከማንም ተቋም በላይ በባህሪው ለግልፅነት የተጋለጠ ተቋም ያደርገዋል፡፡ የዳኝነት አካሉ የግልፅነት መገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱ መካከል በግልፅ ችሎት ማስቻልና በምክንያት የተደገፉ ውሣኔዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 26 እንደሚለው በሕግ ከተለዩ አንዳንድ ጉዳዮች ውጪ ሁሉንም ጉዳዮች በግልፅ ችሎት እንደሚያስችሉ ይገልፃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሕግ አስገዳጅነት ያላቸው የሰበር ውሣኔዎች አሳትመው የማሰራጨት ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት እስከ አሁን ድረስ የሕግ አስገዳጅነት ያላቸው የሰበር ውሣኔዎች በአስራ አራት መፅሐፍ በማሳተም እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡ ቁጥር 15 እና ቁጥር 16 መፅሐፍት ህትመትም በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታተሙት እና ያልታተሙተ የሰበር ውሣኔዎች ለሕግ ትምህርት ቤቶች ለተመራማሪዎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሰበር ውሣኔዎቹን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረ-ገፅ እንዲጫኑ ተደርጓል (እርስዎም WWW.gov.fsc.et ብለው ቢገቡ የሰበር ውሣኔዎችን በቀላሉ ያገኛሉ)፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት አሰራርና በሥራ ላይ ስለሚገኙ ሕጐች የያዙ በርካታ መረጃዎች በድረ-ገፁ አማካኝነት ለሕዝብ በነፃ ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ለዳኝነት አካሉ ግልፅነት መዳበር የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕዝብ ግንኙነት
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment