Wednesday, December 03, 2014

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለሥራ ጉብኝት በርሊን ገቡ

(Dec, 2014, (አዲስ አበባ))--ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ጀርመን በርሊን ገቡ። በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በርሊን ሲደርስ በአገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል ተደርጎ ለታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከአገሪቱ መራሂተ-መንግሥት አንጌላ መርክል እና ከሌሎችም የጀርመን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ።

ከጀርመን የፓርላማ አባላት፣ የንግድ ማህበረሰብና፣ ከልማት ትብብር ኮሚቴ ጋር ቆይታ እንደሚኖራቸውም ታውቋል። የጉብኝቱ ዓላማ እያደገ የመጣውን የሁለቱ አገራት የገንዘብና የቴክኒክ ትብብር እንዲሁም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የህዝብ ለህዝብና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር ነው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1964 ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈረመው የኢትዮ- ጀርመን የትብብር ስምምነት ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጀርመን ለኢትዮጵያ ከ939 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ አድርጋለች።

ስምምነቱ በየሦስት ዓመታት የሚታደስ ሲሆን፣ ባለፉት ጊዜያት 102 ሚሊዮን ዩሮ የነበረውን የትብብር ድጋፍ በቀጣዮቹ ዓመታት 129 ሚሊዮን ዩሮ ለማድረስ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ድጋፉ በዋነኛነት ለገጠር ልማት፣ ለትምህርትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሲውል ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዩሮ ለብዝሃ ህይወትና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሰጥታለች።

ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ጀርመን ከአውሮፓ አገራት ለአረንጓዴ ልማት ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረግ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ አገር ናት። ባለሀብቶችዋም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም ወደ ሥራ በመሰማራት ላይ ይገኛሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ 198 የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የ52 ፕሮጀክ ቶች ፈቃድ ወስደዋል። የሁለቱ አገራት የንግድ ትብብርም የጠነከረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ ወደ ጀርመን ስትልክ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ደግሞ ከጀርመን ታስገባለች።

በተመሳሳይ ዜና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተው የልኡካን ቡድን ወደ አገሪቱ የሄደው የጀርመን መንግሥት ባደረገለት ይፋዊ ግብዣ መሠረት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቡድኑ በአገሪቱ በሚኖረው ቆይታ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በሚጠናከርባቸው መንገዶች ላይ ይመካከራል። በተለይም በቴክኒክና ገንዘብ ድጋፍ ረገድ ያለውን ግንኙነት ለማሳ ደግ ትኩረት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment