Monday, December 01, 2014

የአክሱም ጽዮን ማርያም በዓል በድምቀት ተከበረ

(Dec, 01, 2014, (አዲስ አበባ))--አክሱም ህዳር 21/2007 የአክሱም ጽዮን ማርያም የንግስ በአል ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ  በላይ  በተገኘበት ዛሬ ተከበረ ። አቡነ ማቲያስ ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወኢጨጌ ዘ መንበረ ተክለሀይማኖት በዓሉን ለማክበር ለተሰበሰበው ህዝብ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡


በዓሉ ህዝቦች ተሰባስበው ፍቅራቸውንና አንድነታቸው የሚገልፁበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከስደት ይልቅ መንግስት ባስቀመጠለት አድል ተጠቅሞ ኑሮውን ለመለወጥ መስራት እንዳለበትም በዚሁ ጊዜ አሳስበዋል፡፡

የትግራይ  ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር  አቶ አባይ ወልዱ እንደተናገሩት በአሉ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን በማስተዋወቅ ልናከብረው ይገባል ብለዋል ። በተጨማሪም በአክሱምና አከባቢው የሚገኙ ቅርሶችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚገባ ገልፀው በዚህም ባለሀብቶችና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በርትተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአክሱም ጽዮን ማርያምን ለማክበር ከጀርመንና እስራኤል የመጡ ዶክተር አልያን ደቢድና ሚስ ዮላአነዳ ዲሎሰ እንደተናገሩት በርካታ ህዝብ በአንድ ላይ ተሰባስቦ በዓሉን በፍቅር ማክበሩ በጣም ደስ የሚል ትእይንት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የቄሶች አልባሳትና ያሳዩት ያሬዳዊ ዜማና ውዝዋዜ እርካታ ሰጥቶናል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ለጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ያነሱትን  ፎቶና የቀረጹትን ፊልም በማሳየት በሚቀጥለው አመት እንዲመጡ እንመክራቸዋለን ብለዋል ።

በበዓሉ አከባበር ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶችና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ምእምናን ተገንተዋል፡፡
ምንጭ:  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment