Sunday, November 30, 2014

«ለሃና ፈጣን እርዳታ አልተደረገም» ሲሉ አባቷ ተናገሩ

(Nov 30, 2014, (አዲስ አበባ))--በደረሰባት ተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሕይወቷ ያለፈው የ16 ዓመቷ ተማሪ ሃና ላላንጎ በሕይወት እያለች ከፖሊስና ከሆስፒታሎች አስቸኳይና ፈጣን ዕርዳታ ባለማግኘቷ ሕይወቷ ሊያልፍ መቻሉን አባቷ ገለጹ። በሴቶች ጥቃት ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ማህበራትም ጥቃቱ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያስገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።የሟች ሃና አባት አቶ ላላንጎ ሀያሱ ትናንት በራስ ሆቴል በተሰጠውና በርካታ ማህበራትና ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ሃና ከጠፋችበት ዕለት ጀምሮና ከተገኘችም በኋላ ዕርዳታቸውን የጠየቋቸው የፍትሕ አካላትና የተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ለአራት ቀናት ዕርዳታ አላደረጉላትም።

ሃና ተጠርጣሪ ወንጀለኞች አስገድደው ከሰወሯት በኋላ ወዲያውኑ ለፖሊስ ማስታወቃቸውን ያስታወሱት አቶ ላላንጎ፤ ከፖሊስ ግን ፈጣን ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ልጃቸው በደረሰባት አስከፊ የመደፈር አደጋ በሕይወትና ሞት መካከል ሆና አግኝተዋት ከ11 ቀናት በኋላ በፍጥነት አቅራቢያ ቸው ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ቢወስዷትም «ፖሊስ ካልመጣ ማከም አንችልም» የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

ከእዚሁ ሆስፒታል ያገኙትን ምላሽ ተከትለውም ፖሊስ እንዲመጣላቸው በማድረግ ዕርዳታ ቢጠይቁም «ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ወደ ሌላ የመንግሥት ሆስፒታል ውሰዷት» እንደተባሉ የተናገሩት አቶ ላላንጎ፣ በተባለው ሆስፒታልም አስፈላጊ ያሉትን መረጃ ከመዘገቡ በኋላ እነርሱም በተመሳሳይ ወደ ሌላ ሦስተኛ የመንግሥት ሆስፒታል እንደላኳቸው ተናግረዋል።

«ወደ ሦስተኛው ሆስፒታልም ሄድኩ። እዚህም ህክምና ስለሌለ ቀደም ብዬ ሄጄበት ወደነበረው ሁለተኛው የመንግሥት ሆስፒታል መለሱኝ። ይሄኛው ሆስፒታል ደግሞ መልሶ ወደ ሌላ አራተኛ የመንግሥት ሆስፒታል ላከኝ። እዚያም አልጋ የለም ተብዬ ልጄን ወንበር ላይ አስተኝቼ መጠባበቅ ጀመርኩ» ብለዋል።

እንደ አቶ ላላንጎ ገለጻም፣ በመጨረሻ የሄዱበት አራተኛው የመንግሥት ሆስፒታል ዶክተሮችና ነርሶች ለተጎጅዋ ሃና እጅግ ከፍተኛ ዕርዳታ ቢያደርጉላትም ታዳጊዋ የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር በ20ኛው ቀን ሕይወቷ አልፏል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሴቶች ጥቃት ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ማህበራት በሴቶች ላይ እየተባባሰ የመጣው ጾታዊ ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሊያስገቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዘመቻ በጾታዊ ጥቃት - ኢትዮጵያ፣ የሎ ሙቭመንትና ፍትሕ ለሀና ፀረ የሴቶች ጥቃት ዘመቻ በጋራ በመሆን ያዘጋጁትና በሃና ላይ እንደተፈጸመው አሰቃቂ እና አጸያፊ ድርጊትም ሆነ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማናቸውም ዓይነት ጥቃት እንዲቆም ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።

ከድጋፍ ፊርማ ጋር ተያይዞ ይቀርባል በተባለው በእዚሁ ደብደቤ ላይ ማህበራቱ «ይደረግልን» ሲሉ አምስት ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡም ታውቋል። ከጥያቄዎቹም መካከል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲወገዱ የሚተጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በበላይነት የሚያስተባብረውና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም ተቆርቋሪ ዜጎችና የኅብረተሰብ መሪዎች የሚሳተፉበት ግብር ኃይል እንዲቋቋም የሚለውና ሠርተው እንዳይተዳደሩ የተደረጉ የጥቃት ሰለባ ሴቶችን የሚያግዝ የሴቶች ጥቃት ፈንድ በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር እንዲቋቋም የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment