Sunday, October 12, 2014

ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክብር ነው!

(ጥቅምት 02/2007, (አዲስ አበባ))--ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሉዓላዊ ሀገር ሕዝብ የማንነት መለያ ምልክት ነው። ሰንደቅ ዓላማ የሉአላዊ ሀገር ሕዝቦች፣ አንድነታቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ክብራቸውን፣ ታሪካቸውን የሚገልፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወከሉበት ምልክት ነው። የሉዓላዊ ሀገር ሕዝቦች፤ በድል አድራጊነትና በስኬት፣ በሃዘን፣ በቅሬታና ተቃውሞ ስሜታቸውን የሚገልፁበት ምልክታቸው ነው።

የሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ መውለብለብ፤ የሰላም፣ የድል አድራጊነት፣ የስኬት መግለጫ ነው። የሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ መውለብለብ ደግሞ የህዝብ ሃዘን መግለጫ ነው። የሰንደቅ ዓላማ ወርዶ መጣል ደግሞ የሉዓላዊ ሀገርና የህዝቦቿን ድል መነሳት፣ መዋረድ ያመለክታል። የዚሀ አይነት ድርጊት መፈፀም የሀገርና የህዝብን ክብር መንካት ነው።

ሰንደቅ ዓላማ አንድ ሉዓላዊ ሀገር በሚወከልበት ቦታ ሁሉ ይውለበለባል። የሉዓላዊ ሀገር መንግሥት በሌሎች ሀገራትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚወከልበት የኤምባሲ ጽህፈት ቤቶች ቅፅር ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ ይውለበለባል። የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካን ህብረትን በመሰሉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ህብረት እንዲሁም አካባቢያዊ ማህበራት የአባል ሀገራት ሰንደቅ ዓላማዎች በእኩል ቁመት ይውለበለባሉ።

የዓለም ሀገራት በሀብትና በስልጣኔ መጠን ቢለያዩም በሉዓላዊነት ግን እኩል በመሆናቸው ሰንደቅ ዓላማዎቻቸው በእኩል ቁመት ነው የሚውለበለቡት። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው መገለጫ እና ከዓለም ህዝብ ጋር እኩል መሆናቸው ማሳያ ነው።

የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው የህግ ዕውቅና ተነፍጎት በማንነታቸው እንዲያፍሩና ማንነታቸውን እንዲያጡ በተደረገበት የዘውዳዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የነበሩት ቢሆንም በላዩ ላይ አርማ ነበረው። አርማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችን አብዘሃነት፣ እኩልነትና አብሮነት የሚያንፀባርቅ አልነበረም።

ከዚህ ይልቅ የዘወዳዊው ሥርዓት ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሰፈረው አርማ ነገሥታቱ የዘር ግንዳችን ይመዘዝበታል የሚሉትን ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነውን ይሁዳ የሚወክል አንበሳና የነገሥታቱን ክርስትና የሚያመለክት ነበር። ይህ ዓርማ የዘር ሃረጋቸው ከይሁዳ የሚመዘዝ፣ ሃይማኖታቸው ክርስትና የሆነ ነገስታት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባሻቸው መንገድ ረግጠው እንዲገዙ በአምላክ የተሾሙ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው።

አሁንም ይህን «የይሁድ አንበሳ» ዓርማ ያለበትን የቀድሞ ሰንደቅ ዓላማ የሚናፍቁ ተስፋ ለዘውዶች አሉ። እነዚህ ሰዎች «የዘር ሃረጌ ከይሁዳ የሚመዘዝ ክርስቲያን ነኝ»የሚለው ንጉሳዊ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ተመልሶ መጥቶ በአርሶ አደሩ ትከሻ ላይ ተቀምጠው ጠጅ እየጠጡ፣ ጮማ እየቆረጡ በበላይነት ስሜት የሚፎልሉበትን ጊዜ እየናፈቁ ነው።

አዝማሪ አቁመው «አንበሳው የሌለው ሰንደቅ ዓላማ ምኑን ሰንደቅ ዓላማ ሆነ» እያሉ እያዘፈኑ የተስፋ ረሃባቸውን ለማስታገስ እንደሚሞክሩም እንሰማለን። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እነዚህን ተስፋ ለዘውዶች ከጥላ ለይተው አያዩዋቸውም። ምንም ማድረግ የማይችሉ የዘውዳዊው ሥርዓት ጥላዎች።

ዘውዳዊው ሥርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከተወገደ በኋላ ትግሉ ያልተደራጀ ስለነበረ የመንግሥት ሥልጣን ያንኑ ሥርዓት ሲያገለግሉ የነበሩ ጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች እጅ ይወድቃል። ሥርዓቱን ጥቂት ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ወታደራዊ መኮንኖች ነበር የሚመሩት። ይህ ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት፣ ዘውዳዊው ሥርዓት ጭኖት የነበረውን ብሔራዊ ጭቆና አስቀጠለ። በአንድ ብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ የወሰን አንድነት ያለው አሃዳዊ ሥርዓት ነበር የመሰረተው። በወቅቱ ጎልቶ ወጥቶ ለነበረው የመሬት ለአራሹ የኢኮኖሚ ጥያቄ ምላሸ የሰጠ ቢሆንም፣ አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት የባለቤትነት መብት ስላልተረጋገጠ የኢኮኖሚ ጭቆናው በሌላ በኩል ፈጥጦ ወጥቶ ነበር።

ታዲያ ይህ ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሥርዓት በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግሥትነት በቆየባቸው አስራ ሦስት አመታት ውስጥ ምንም አርማ በላዩ ላይ የሌለ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክት አድርጎ ቆየ። ከአስራ ሦስት ዓመታት የጊዚያዊ መንግሥት ቆይታ በኋላ በ1980 ዓ.ም መንግሥት ሲመሰርት ባወጣው ሕገ መንግሥቱ ላይ ሰንደቅ ዓላማው አርማ እንደሚኖረው ደነገገ።

ይህ አርማ ሦስት ሺህ ዘመን ኖሯል የሚባልለትን በአንድ ብሔር የበላይነት የሚገለፀውን፣ የህዝብ ሳይሆን የወሰን አንድነት ያለውን አሃዳዊ ሥርዓት ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነበር። ወታደሮቹ ያንኑ ዘውዳዊ ሥርዓት በተለየ መልክ ማስቀጠላቸውን የገለፁበት አርማ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ አርማ ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ቦታ አልተሰጠውም።

ወታደራዊ መንግሥቱ የመሰረተው አሃዳዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየአቅጣጫው ባካሄዱት የትጥቅ ትግል ግንቦት 1983 ዓ.ም ላይ ተገረሰሰ። ይህን ተከትሎ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዘቦች እንዲሁም ሌሎች አመለካከቶች የተወከሉበት የሽግግር መንግሥት ተመሰረተ።

ይህ የሽግግር መንግሥት የቀደሙት መንግሥታት በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቸ ላይ ጭነውት የነበረውን ብሔራዊ ጭቆና የሚያስቀርና ብሔራዊ ጭቆናው ያስከተለውን የተዛባ የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያስተካክል ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅ ማድረግ ዋና ተግባሩ ነበር። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቀጥታ በተሳተፉበት ሥርዓት ህገ መንግሥት እንዲዘጋጅ ተደረገ። ሂደቱ የሚከተለውን ይመስላል።

ሁሉም የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሌሎች አመለካከቶችን የሚወክሉ የሽግግር መንግሥቱ አባላት የሚወከሉበት የህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ተመሰረተ። ይህ ኮሚሽን የመጀመሪያውን የህገ መንግሥት ረቂቅ አዘጋጀ። ረቂቁን ኮሚሽኑ ራሱ ወይም ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት እንዲያፀድቀው አልተደረገም። ከዚህ ይልቅ የህገ መንግሥቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያፀድቀው ነበር የተደረገው።

በኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚወከሉ ሁሉም ለአካለ መጠን የበቁ ኢትዮጵያውያን በረቂቅ ህገ መንግሥቱ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ እንዲወያዩ ተደረገ። በዚህ ውይይት መቀነስ አለበት ያሉትን ቀንሰው፣ መጨመር አለበት ያሉትን አክለው ረቂቁን በማዳበር መልሰው ላኩት። ኮሚሽኑ በህዝብ ዳብሮ የተላከለትን ረቂቅ አሻሽሎ ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲወያይበት ወደ ሕዝብ መራው።

ረቂቁ ለሁለተኛ ጊዜ የተመራለት የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደመጀመሪያው አንቀፅ በአንቀፅ አድቅቆ ተወያይቶ ማሻሻያ ሃሳቦችን አካቶ ላከው። ከዚህ በኋላ ይህን ሁለት ጊዜ በህዝብ ውይይት የዳበረ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ወደ ማፅደቅ ሂደት ተሸጋገረ። ህገ መንግሥቱ የፀደቀው በአርቃቂ ኮሚሽኑ ወይም በሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት አልነበረም። በሕዝብ ነበር ። ህዝብ በመረጣቸው ተወካዮች።

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተወያዩ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አባላት የሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ኢትዮጵያውያን በምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት የህገ መንግሥት አፅዳቂ ጉባኤ አባላትን መረጡ። ምርጫው የተለያየ አመለካከት ያላቸው ወገኖች የተሳተፉበት፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ነበር። በዚህ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ የተመረጡ አባላትን የያዘው የህገ መንግሥት አፅዳቂ ጉባኤ ሁለት ጊዜ በሕዝብ ውይይት የዳበረውን ረቂቅ ሕገ መንግሥት እያንዳንዷን አንቀፅ በድምፅ ብልጫ እያሳለፉ በመጨረሻ ሙሉውን ህገ መንግሥት አፀደቁ።

ሕገመንግሥቱን ማዘጋጀት ተቀዳሚ ኃላፊነቱ በነበረው የሽግግር መንግሥት ወቅት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ምንም አይነት አርማ የሌለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ነበር። የአፌዴሪ ህገ መንግሥት ላይ ግን ይህን የሚቀይር ድንጋጌ ሰፍሯል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የሆኑበት፣ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ መኖር የሚችሉበትን መብትና ነፃነት ያጎናፀፈው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (የኢፌዴሪ) ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አዲሱን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግንኙነት የሚያንፀባርቅ አርማ እንዲኖረው ነው የደነገገው። ሕገ መንግሥቱ የአርማውን አይነት ግን አልወሰነም ነበር።

ሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 3 «የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ» በሚል ርዕስ ስር፤

• የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ አርማ ይኖረዋል።

• ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል ይላል።

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በሚመለከት ህገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን የእኩልነትና የአንድነት ተስፋ የሚያንፀባርቁበት ዓርማ ማዘጋጀት ችሎታ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ተሰጠ። ችሎታ ያላቸው ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን መንፈስ የሚወክል ዓርማ አቅርበው እንዲወዳደሩ ይፋ ማስታወቂያም ወጣ። ከተወዳዳሪዎቹ ያሸነፈው ሃሳብ አሁን ሰንደቅ ዓላማው ላይ የሰፈረው ዓርማ ሆኖ ታትሟል።

የኢፌዴሪ ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ህብረ ቀለማት የሰፈረው (ሦስቱም ቀለማት ላይ ያረፈ) ክብ ሰማያዊ መደብ ባለአምስት ማዕዘን ኮከብና ጮራ ያለው አርማ ነው። ይኸው በህገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን «ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል።» የሚለውን ሃሳብ ያንፀባርቃል፤ የትኛውንም የፖለቲካ ቡድንም የማይወክል ነው።

ይህን ሰንደቅ ዓላማ መድፈር የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የሆኑና ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ያላቸውን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መድፈር ነው።

በቅርቡ ኢትዮጵያን ማፈራረስና ገፅታዋን ማበላሸት ዋናው ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የኤርትራው ሻዕቢያ ተላላኪ በሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽህፈት ቤት ቅፅር ውስጥ በመውለብለብ ላይ የነበረውን የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ለማውረድ ያደረጉት ሙከራ ኢትዮጵያውያንን እጅግ አስቆጥቷል። የአሜሪካ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰንደቅ ዓላማውን ለመድፈር የሞከሩት አሜሪካውያን ላይ ዓለም አቀፍ የኤምባሲዎች ግንኙነት ስምምነትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች በሚያዙት መሰረት ተገቢውን የህግ እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠይቃል።

የአንድ ሉዓላዊ ሀገር ኤምባሲን ፅህፈት ቤት ቅፅር መድፈር፣ የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ለማዋረድ መሞከር በጄኔቫ ዓለም አቀፍ የኤምባሲዎች ግንኙነት ስምምነት መሰረት በጥብቅ የተከለከለና በህግ የሚያስጠይቀ ድርጊት ነው። በሌላ ሀገር የሚገኝ የኤምባሲ ፅህፈት ቤት ቅፅርን መድፈር የባለ ኤምባሲውን ሀገር ሉአላዊ ወሰን ከመደፈር ተለይቶ አይታይም። የኤምባሲ ፅህፈት ቤቱ የሚገኝበት መንግሥትም ቢሆን እንኳን በማንኛውም ሁኔታ የኤምባሲውን ቅፅርና በቅፅር ውስጥ የሚገኙትን የሉዓላዊነት መገለጫዎች መድፈር አይችልም። በወንጀል የሚፈልጋቸው ሰዎች እንኳን ወደ ኤምባሲው ቅፅር ሸሽተው ቢገቡ፣ በፖሊስም ይሁን በወታደር ቅፅሩን ደፍሮ ሰዎቹን መውሰድ አይችልም። ስፍራው የሀገራቱ ሉዓላዊነት መገለጫ ነውና።

የአሜሪካ መንግሥት የኢፌዴሪን ሰንደቅ ዓላማ በደፈሩ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ሕጋዊና ፍትሃዊ እርምጃ፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነትና ጥቅም ያገናዘበ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ደግሞ የግንኙነቱን ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ከግንዛቤ ሊያስገባው ይገባል። የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መድፈር የኢትዮጵያ ብሔሮችንና ብሔረሰቦችን መድፈር መሆኑ መታወቅም ይኖርበታል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment