Tuesday, September 16, 2014

«ሁለት እግር አለኝ» ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም!

(Sep 16, 2014, ( አዲስ አበባ)--የዛሬው የጋዜጣችን መልዕክት በአንዲት አነስተኛ ተረት ላይ ይመሠረታል። በአንድ መካከለኛ ዕድሜ ደረጃ ያለ ፀጉሩ ወደ ግራጫነት የተለወጠና ሁለት ፍቅረኞች ያሉት አንድ ሰው ነበር። አንደኛዋ ፍቅረኛው ወጣት ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ አሮጊት ነበረች። ስለሆነም ወንድዬው ወደ ወጣቷ ሲሄድ ወጣት እንዲመስልላት ነጫጭ ፀጉሩን (ሽበቱን) ትነቅልለታለች። ወደ አሮጊቷ ሲሄድ ደግሞ ወጣት ፍቅረኛ ያዘ እንዳይባል ሽበቱን እየተወች ጥቁር ጥቁሩን ትነቅልበታለች። በየጊዜው ጥቁርና ሽበት ፀጉሩ ሲነቀልበት በአጭር ጊዜ መላጣ ሆነ ይባላል ሰውዬው።

ኢትዮጵያውያን በኖረው ቱባ ባህላችን ታሪካችንና ህብረብሔራዊ ልማዳችን ሁሉ «ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም!» የምንለው ይህን ዓይነቱን ተግባር ነው። ዛሬ ሀገራችን መገንባት በጀመረችው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችና የግል መገናኛ ብዙኃን ሙያተኞችን ይህንኑ የአበው ብሂል በመጥቀስ ምክር ልንለግሳቸው እንወዳለን።

•የፖለቲካ ኃይሎች ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊው «ዛፍ» ይበቃቸዋል

የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መግቢያ ላይ ከተቀመጡ መሳጭ መሪ ሃሳቦች አንዱ « በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነፃ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት...» ይላል።

በሀገሪቱ ያለውን የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የአመለካከት፣ የፆታና መሰል ብዝሃነትን ታሳቢ ያደረገው ዴሞክራሲያዊው ሕገመንግሥት ሁሉንም ኃይሎችና አመለካከቶች የማስተናገድ አቅም አለው። ለዚህም ነው ዛሬ ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍቃድ ተሰጥቷቸው የራሳቸውን ደጋፊዎች በማደራጀት የሚንቀሳቀሱት። ያም ሆኖ ግን አሁንም «አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት» የተስማሙ ፖለቲከኞች በሀገሪቱ ተፈጥረዋል ወይ? የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ሕጋዊና ሕገ ወጥነትን እንዴት ለይቶ እየተጓዘ ነው? ለብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር ቅድሚያ የመስጠቱ መግባባትስ አለ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት መፈተሽ ይገባል፤ ያስፈልጋልም።

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ነው ሲባል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁሉም ኃይሎች በኃላፊነት ስሜት እንዲሳተፉበት በመመኘት ነው። ትናንት ያልነበሩ አዲስ መቀራረቦችና መሻሻሎችም እንዲመጡ ታሳቢ በማድረግ ነው። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሰሶ የሆኑትን ሕጋዊና ሰላማዊ አማራጮችን ያለማቅማማት መቀበል ግድና አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ «ሁለት እግር አለኝ» ተብሎ አንድ እግርን ወደ ሕገወጥነት አመጽ ሁከትና ሽብር ማምራትና ማዘንበል ማንንም የማይበጅና ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል። ከዴሞክራሲያዊና ሀገራዊ ፋይዳ ውጪ የሆኑ አክራሪነት፣ ጠባብነትና ትምክህትን ማራገብም ማንንም የሚበጅ ተግባር አይደለም።

•የመገናኛ ብዙኃን- ሚዛናዊ የመሆን ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው
በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ከእውነተኝነት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ባልተናነሰ ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት ሊኖራቸው ይገባል። በየትኛውም ዓለም ባሉ ጋዜጦች ፣ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ የሚሠሩ ሙያተኞች የራሳቸው አመለካከት ይኖራቸዋል፡፡ ያንን የግል ስሜታቸውን በሥራቸው ውስጥ በመክተት ግን እውነትን ማዛባት፣ አድሎ መፈጸም፣ የሰዎችን ክብር ማንኳሰስ፣ የዜጎችን ሰላም ማወክ፣ የሙያ ሥነምግባራቸውም አይፈቅድላቸውም። በሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል።

በታዳጊው የዴሞክራሲ ባህላችን ውስጥ ግን «ሁለት ዛፍ ላይ» መውጣት የሚያምራቸው የመገናኛ ብዙኃን አካሄዶች መታየታቸው አልቀረም። በአንድ በኩል ሙያን ከጋዜጠኝነት አውጥቶ የፖለቲካ ተገዳዳሪና ተፎካካሪን ሥራ መውሰድና ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያለውን ሥርዓት የማጠልሸት የማብጠልጠልና የመኮነን ተግባር ደርቶ ይታያል። በሌላ በኩል በሀገሪቱ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች በአሸባሪነት የተፈረጁና የጦርነት አማራጭን የያዙ ኃይሎችን የማንቆለባበስ፣ አጋራቸው የመሆንና በሚሠሩበት የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት የመስጠት አካሄድ ይንፀባረቃል። ከሁሉም በላይ መሬት ላይ ስላለው እውነት ሚዛናዊ ሆኖ ማቅረብን በመፍራት በተስፋ ላይ ባለች ሀገር ውስጥ መርዶ መናገርን ዋነኛ ሥራ አድርጎ መገኘት የአንዳንድ የግል ህትመቶች መገለጫ መስሏል።

እነዚህ ወደ ኋላ የሚመልሱንና የሕዝቡን ገለልተኛና ሐቀኛ መረጃ የማግኘት መብት የሚደፈጥጡ ተግባራት ናቸው። የሕዝብም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙኃን ከሁሉ በፊት ለሕገመንግሥቱ የሚገዙ ለዴሞክራሲያዊ መርሆና ለሙያው ሥነምግባር የታመኑ መሆን አለባቸው። የብሔራዊ ጥቅምና የሕዝብ እኩልነት ጉዳይም ለድርድር የሚያቀርቡት አይደለም። እነዚህ እውነታዎችን ዘንግቶ ጥላቻን ማቀንቀን ደግሞ ባልታሰበ ሁኔታ ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት እንደሞከረው የተረቱ ሰው መመላለጥን ያስከትላል።

ሲጠቃለል የተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማንም ተብሎ ሳይሆን ለሀገሪቱ ካለው ፋይዳ አኳያ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችና ሙያተኞች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራኑ እንዲሁም ሕዝቡ በነቃ ተሳትፎና በሕግ መሠረት ሊያጅቡትና ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ሕጋዊና ሕገወጥነት፤ ዴሞክራሲያዊና ኢ - ዴሞክራሲያዊነትን... በማቀላቀል ምኞት «ሁለት ዛፍ ላይ» ለመውጣት ማሰብ ግን አያዋጣም ብቻ ሳይሆን ውድቀትን ያስከትላል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment