Friday, September 05, 2014

«በሶስትዮሹ ውይይት በተደረሰው ስምምነት ግብፅ ደስተኛ ናት»

(Sep 05, 2014, (አዲስ አበባ))--የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በአዲስ መንፈስ መንቀሳቀስ የጀመረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ነው ለአቻቸው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዶክተር ቴድሮስ የተናገሩት፤

«በሱዳን ካርቱም በተካሄደው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ ውይይት ላይ የተደረሰው ስምምነት ግብፅን ያስደሰታትና ሌሎችንም ያስማማ ነው» ሲሉ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፁ። ወደ የጋራ ትብብሩ ለመምጣትና የኢትዮጵያና ግብፅ የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዲስ መልክ እንዲጀመር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው የሁለቱ አገሮች መሪዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ ያደረጉት ውይይት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምና የግብፁ አቻቸው ትናንት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች የሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በመከሩበት ወቅት የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ እንደተናገሩት፤ ከዶክተር ቴድሮስ ጋር ያደረጉት ውይት ሁለቱ አገሮች በአዲስ መንፈስ ግንኙነታ ቸውን መቀጠል በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ሲሆን፤ ውጤታማም ነው።

ግብፅና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፤ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት አሁንም ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል። የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያደረጉት ውይይት ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተና በአዲስ መንፈስ ለመንቀሳቀስ ያስቻለም እንደሆነ አመልክተዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስት ሳሜህ ሹክሪ በሶስትዮሹ ውይይት ላይ የተደረሰው ስምምነት ሁሉንም ያግባባ ሲሆን፤ ከየአገሮቹ ተውጣጥቶ የተዋቀረው ኮሚቴም ሥራውን በአግባቡ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። የናይል ወንዝ የጥቅማችን ምንጭ መሆን አለበት፤ የአገሮቹም ግንኙነት በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መሆን ይጠበቅበታልም ብለዋል። ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ውይይት በአገሮቹ ላይ በራስ መተማዀን እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም አጽንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በበኩላቸው፤ እንደ ግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሉ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ቀደም ሲል ያካሄዱት ውይይት ለአሁኑ እንቅስ ቃሴያቸው ውጤት ያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል። በካርቱም የተካሄደው የሶስትዮሹ ውይይትም ስኬታማ ነበር ሲሉ ገልፀው፤ ለዚህ ስኬት ትልቁን እገዛ ያደረገው የመሪዎቹ አስቀድሞ መወያየት እንደሆነም ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ፣ የአቻቸው አዲስ አበባ መገኘትና የሶስቱ አገሮች የውሃ ሚኒስትሮች ያካሄዱት የሶስትዮሹ ውይይት ስምምነት ላይ መደረሱ አሁንም ምክንያቱ የመሪዎቹ መወያየት እንደሆነ በአፅንኦት ገልፀዋል። እንዲሁም በራስ መተማመንንና እምነትን ያጎለበተ መሆኑንም ተናግረዋል። ዶክተር ቴድሮስ፤ የግብፁ ፕሬዚዳንት «የናይል ጉዳይ በአብሮነት ለመስራት የሚያስችለን ምክንያት እንጂ ልዩነት ሊፈጥርብን የተገባው መሆን የለበትም» ሲሉ መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ኢትዮጵያና ግብፅ ትብብራቸውን በማጠናከር፤ በተለይም በጤናው፤ በግብርናው፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልክ ተዋል። አሁን የተፈጠረው አዲስ መንፈስ አጋርነትን የሚያጎለብት፣ ግንኙነትን የሚያጠናክርና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል በማድረግ አብሮ ለመጓዝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አስረድተዋል። ሳሜህ ሹክሪ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት እኤአ ሰኔ ወር 2014 ሲሆን ከዛ በፊት በአምባሳደርነት አገልግለዋል።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment