Friday, September 12, 2014

ኢቦላ በአገራችን አልተከሰተም፤ ጥንቃቄው ከወዲሁ እየተደረገ ነው

(Sep 12, 2014, ( አዲስ አበባ)--ኢቦላ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና በአጭር ጊዜ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። በሽታው በተለይም በምዕራብ አፍሪካ አገሮች በቅርቡ ተከስቶ በርካታ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን፤ በአገራችንም በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰሞኑን ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተሰጠው መግለጫ።

በኢቦላ በሽታ ከተያዘ ሰው ቁስል፣ደም፣ ምራቅ ትውከት፣አይነምድርና ሽንት ጋር በቀጥታ በመነካካት ወይም እነዚህ ፈሳሾች ወደ ጤነኛ ሰው አይን ከተረጩና ከገቡ፤ መርፌን ሳይቀቅሉ በመጠቀም፣ በኢቮላ በሽታ የተያዘ ሰው የተጠቀመባቸውን ስለታማ ነገሮች በመጠቀም፣ በበሽታው የሞተን ሰው አስከሬን በመንካትና በኢቮላ በሽታ የሞተን እንስሳ ስጋ በመብላት የኢቮላ በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል።

በኢቦላ በሽታ ከተያዘ ሰው ጋር ንከኪ የፈጠረ ሰው ከሁለት እስከ 21 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት የሚጀምር ሲሆን፤ ምልክቶቹም ድንገተኛና ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ፣ እራስ ምታት፣የቆዳ ሽፍታና የአይን መቅላት ከዚህ በተጨማሪም በአይን ፣ በአፍንጫ፣ በድድ፣ በጆሮ፣ ፊንጢጣና በብልት በኩል የመድማት ምልክት ሊያጋጥም ይችላል። ይህ ሁኔታ አንዳንዴ ላይታይ እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢቮላ በሽታ የተጠረጠረን ወይም የተያዘን ሰው በምንረዳበት ጊዜ ሰውነታችንን ከበሽታው መከላከል የሚያስችለንን የእጅ ጓንት የአይን መከላከያ መሳሪያ የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛ በመጠቀም በአፋጣኝ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም መውሰድ ያስፈልጋል።

በሽታው ከታመመ ሰው የሚመጣውን ደምና ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች በቀጥታ በመነካካት የሚተላለፍ በመሆኑ ከታመመ ሰው ጋር የሚኖርና በበሽታው የሞተን ሰው አስከሬን ያለ እጅ ጓንትና ሌሎች የመከላከያ መሳሪያዎች የሚነካ ማንኛውም ሰው በበሽታው ሊያዝ ይችላል።

በኢቦላ በሽታ የተያዘ ወይም የተጠረጠረን ሰው በተቻለ መጠን ለብቻው እንዲሆን ቦታ መለየት፣ታማሚውን ወይም ተጠርጣሪውን ወደ ህክምና ቦታ በምንወስድበት ጊዜ አላስፈላጊ ንክኪ አለማድረግ፣ በበሽታው ከተያዘ ወይም ከተጠረጠረ ሰው የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወዲያው በውሃና በሳሙና መታጠብ፣ በበሽታው የተያዘ ወይም የተጠረጠረ ሰው የሰውነት ፈሳሽ መሬት ከበከለ በረኪና በመጨመር ከ15 ደቂቃ በኋላ ማፅዳት እንዲሁም በበሽታው ታሞ የሞተ ሰው የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም ከአስከሬን ጋር ንክኪ አለማድረግና የጋራ የሆነ የእጅ መታጠቢያ አለመጠቀም የኢቦላ በሽታን ለመከላከል ያስችላል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ኢቦላን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ድረስ በአገሪቷ የበሽታው ምልክት ባይከሰትም አስቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። እስካሁን 275 ለሚሆኑ የመንግሥትና የግል ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ስለ ቫይረሱ ስልጠና ተሰጥቷ ቸዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከምዕራብ አፍሪካ የሚገቡ መንገደኞች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።

«በሽታው እስካሁን አገራችን ባይገባም ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች ጋር ባለን ግንኙነት በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ስለሚችል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገ ባል»ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም በኤርፖ ርቶችና በድንበር አካባቢ ባሉ መውጫና መግቢያ በሮች በኩል ባለሙያ በመመደብ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

95 በመቶ ግንባታው በተጠናቀቀው ኮተቤ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ10 ጊዜያዊ አልጋዎችንና የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ የኢቦላ ምልክት ሊያሳዩ የሚችሉ ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃ ቸውንም ዶክተር ከሰተብርሃን አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ከሰተብርሃን ገለፃ በሽታው በአገሪቷ ከተከሰተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአየር መንገዱ የሚጓዙ መንገደኞችን ሁኔታ በመለየትና የታመመ ሰው ከተገኘም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው ጊዜያዊ የማቆያ ቦታ ህክምና እንዲያገኝ ይደረጋል። ከክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ስምምነት የመከላከል ስራ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል። ለዚሁ ስራ የሚውሉ ሶስት አምቡላንሶች የተዘጋጁ ሲሆን ለህክምና ግብዓቶችና ለባለሙያዎች የሚሆን የመከላከያ መሳሪያዎች በመሟላት ላይ ናቸው።

«ኢቦላ በአሁን ወቅት በኬንያ ይከሰታል ተብሎ የሚፈራ ቢሆንም በሽታው እንዳልገባ ተረጋግጧል» ያሉት ዶክተር ከሰተብርሃን፤ ኬንያ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ በረራዎችን የምታስተናግድ በመሆኑ ስጋቱ ሊፈጠር መቻሉን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ከኬንያ ጋር ድንበር የምትጋራ በመሆኑ በሽታውን በጋራ ለመከላከል ከኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ማድረጓን አስታውቀዋል።

ሰሞኑን ከናይጄሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን በበሽታው ተይዘዋል ተብሎ የተናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑንና ለሰዎቹ በኮሪያ ሆስፒታል በተደረገላቸው ምርመራ በወባ በሽታ የተያዙ መሆኑ ተረጋግጧል። በመሆኑ አስፈላጊው ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ዶክተር ከሰተብርሃን ተናግረዋል።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment