Tuesday, October 17, 2017

«አገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?»

(Oct 17, 2017)
አንድ የድሮ ዘፈን አለ፡፡
«አገር መውደድ ማለት፣ ምንድን ነው ትርጉሙ
ማንቀላፋት ነው ወይ፣ ዓይንን ማስለምለሙ፡፡»
የጌታ መሣይ አበበ ዘፈን መሰለኝ፡፡ ዘፈን በዜማ እንጂ በፊደል አይሆንም፡፡ ሆኖም ለእኔ ጉዳይ ፊደሉ ይበቃል፡፡ የእኔ ጉዳይ ከዜማው ሳይሆን ከመልዕክቱ ነው፡፡ በእውነት አገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?

በነገራችን ላይ፣ ይህን ጉዳይ እንዳስብ ምክንያት የሆነኝ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የተከበረው የአገር ፍቅር ቀን ነው፡፡ ስለዚህ ቀኑን ያከበርኩት፤ ‹‹በእውነት አገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?›› የሚል ነገር እያሰላሰልኩ ነው፡፡

በነገሩ ብዙ አሰብኩበት፡፡ አስቤ ... አስቤ ቁርጥ ካለ አንድ ሃሳብ መድረሱ ተሳነኝ፡፡ እናም ሃሳቤ ተበታትኖ ሲያስቸገረኝ፤ ‹‹የአገር መውደድ ነገር አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም የለውም›› ለማለት ሞከርኩ፡፡ እንደኔ አስተያየት፣ የአገር መውደድ ስሜት መገለጫ ወይም መከሰቻ ማህደር ካላገኘ አደናጋሪ እና ረቂቅ ሃሳብ ሆኖ ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ወይም የማይጨበጥ ጉም ሆኖ የሚቀር ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ የአገር ፍቅር ጉዳይ መከሰቻ ወይም መገለጫ እሴት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም መከሰቻ እና መገለጫ ማህደር፤ እንደ አገሪቱ ተጨባጭ ወይም ወቅታዊ ይዞታ የሚለዋወጥ ገጽታ ሊይዝ የሚችል መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ከሰው ልጆች ሁሉ መሠረታዊ ጥቅም ጋር የተጣጣመ ወይም ለዚህ እሴት ተጻራሪ ባልሆነ አመለካከት የሚገዛ ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ለአገር መውደድ ስሜት ከድንጋይ የተቀረጸ አንድ ወጥ ትርጉም እንስጠው ከተባለ፤ አገር መውደድ ማለት ‹‹ሁሌም ለአገር ወይም ለህዝብ ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው›› የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ለአገር ታማኝ መሆን በአንድ ድንበር ወይም የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ታማኝ በመሆን የሚገለጥ እሴት ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለተካተቱት እና በተለያየ አመለካከት (ግለሰባዊ እና ቡድናዊ) ሊገለጡ ወይም ለወከሉ ለሚችሉ ሰዎች ሁሉ ታማኝ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲህ ማድረግ የሚቻለውም ለሰው ልጆች ሁሉ ታማኝ የሚያደርግ እሴት በመያዝ ነው፡፡ ስለዚህ አገር መውደድ ማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ጠበቃ በሚያደርጉ እሴቶች እየተመሩ፤ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለታቀፉ ሰዎች ታማኝ ሆኖ መገኘት ማለት ነው፡፡

የአገር መውደድ ስሜት፤ የግድ የሰው ልጆችን ከመውደድ መነሳት ይኖርበታል፡፡ በአንተ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች እንዲሆን ካለመፈለግ እሴት መነሳት አለበት፡፡ እሴቶቹ ሁሉንም ሰዎች ወይም ህዝቦች የሚመለከቱ ቢሆኑም፤ በአሁኑ ዓለማዊ ሁኔታ የአገር ፍቅር ጉዳይ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በተመሠረተበት ክልል የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብም በተለያዩ ዘመናት የሚኖሩት ዋነኛ ትኩረቶች የሚለያዩ በመሆናቸው፤ የአገር ፍቅር መገለጫው እንደ ጊዜው የተለያየ መሆኑ አይቀርም፡፡ ሆኖም ከዚህ ተለዋዋጭ ከሆነ ጉዳይ አንድ ዘላለማዊ ወይም ቋሚ ነገር ማውጣት ይቻላል፡፡

የአገር መውደድ ጉዳይ ማሰብን እና ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡ አገርን መውደድ በመሠረታዊነት በእሴቶች እና በመርሆዎች ዙሪያ የሚመሰረት አመለካከት ነው፡፡የማይለዋወጥ ቋሚ የአገር ፍቅር ስሜት ባህርይ ነው፡፡ አገርን የመውደድ ስሜት በየዋህነት እና ባለማወቅ ከተመራ አደገኛ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ባለማወቅ አንቀልባ ላይ የታዘለ የአገር መውደድ ስሜት አጥፊ ነው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት unpatriotic ነው፡፡

ለምሣሌ፤ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አገር ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ እሴት ይዞ አገር ወዳድ ሰው መሆን አይቻልም፤ እንዲሁም አገርን የመውደድ ስሜት ከግለሰብ ወይም ከቡድን ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ በእርግጥ አገርን የመውደድ ስሜት ከግለሰብ ወይም ከቡድን ጋር ተያይዞ የሚከሰትበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ታዲያ በዚህ መሰል አጋጣሚዎች ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አንድ መሪ፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚወክል እንዲሁም በሰው ልጆች ሁሉ ተቀባይነት ያለውን እሴት ያነገበ መሪ ወይም ቡድን ሆኖ ሲገኝ ሊወደድ ይገባዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ያ ግለሰብ ወይም ቡድን ከእሴቶቹ ተቃራኒ የሆነ ሥራ ውስጥ ሲገባ መወደዱ ይቀራል፡፡

ስለዚህ፤ ለአገር ዘወትር ታማኝ መሆን ይገባል፡፡ ለግለሰብ ወይም ለቡድን ታማኝ የምንሆነው በቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ግለሰቡ ወይም ቡድኑ ክብር የሚገባቸው ሆነው ከተገኙ ሊከበሩ ወይም ሊወደዱ ይገባል፡፡ ከእነዚያ እሴቶች ተጻራሪ ሆነው ሲገኙ መወደዳቸው ይቀራል፡፡

ስለዚህ ለግለሰብ ወይም ለቡድን የሚኖረን ታማኝነት በሁኔታ የሚወሰን ሲሆን፤ ለአገር የሚኖረን ታማኝነት ግን ቋሚ እና ዘላለማዊ ነው፡፡ ማርክ ትወይን፣ «Loyalty to country ALWAYS. Loyalty to government, when it deserves it» ይላል፡፡ በሌላ አገላለጽ «Patriotism is supporting your country all the time and your government when it deserves it» ያለው ለዚህ ነው፡፡

ኤድዋርድ አቤይ (Edward Abbey) በበኩሉ «A patriot must always be ready to defend his country against his government» የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ይህ ሃሳብ የማርክ ትወይን ሃሳብ በሌላ ዐ.ነገር እንደ ማለት ነው፡፡ አገር መውደድ ማለት «አገርህ በተሳሳተች ጊዜ በድፍረት መሳሳቷን መናገር ነው» የሚል አቋምን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ «The greatest patriotism is to tell your country when it is behaving dishonorably, foolishly, viciously» የሚሉት ትክክል ነው፡፡

ሰው በመሆናችን ያገኘናቸውን እና አጥብቀን የምንሻቸውን ውድ ኀብረተሰባዊ እሴቶች የሚወክል ግለሰብ እና ቡድን ሊወደድ ይገባል፡፡ የሚወደደው ግን በስሙ ወይም በመልኩ ሳይሆን፣በተላበሳቸው እሴቶቹ ነው፡፡ ያ ግለሰብ ወይም ቡድን አጥብቀን የምንሻቸውን እሴቶች የሚጠብቅ እና የሚያረጋግጥ በመሆኑ ይወደዳል፡፡ የእነዚያ ውድ እሴቶች መገለጫ ወይም መከሰቻ የሆነ መሪ ወይም ቡድን ሊወደድ እና ሊከበር ይገባል፡፡በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የወደድነው ግለሰቡን ወይም ቡድኑን አይደለም፡፡ ይልቅስ በእርሱ የሚገለጸውን እሴት ነው፡፡

አገር ሁሌም መወደድ ይገባታል፡፡ ሆኖም መንግሥት እና የመንግሥት ወኪል የሆኑ መሪዎችን የምንወዳቸው የሚወደዱ (እጅግ የሚከበሩ እሴቶቻችንን የሚጠብቁ) ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ሊወደዱ የሚገባቸው፤ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ እሴቶቻችን መገለጫ እና ጠበቃ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ ለመሪዎች የሚሰጥ ከበሬታ እና ታማኝነት ሊወሰድ የሚችል ችሮታ ነው፡፡ ለአገር የሚኖረን ታማኝነት ግን ዘወትር ጸንቶ የሚኖር ነው፡፡

ለአገር የሚደረግ ታማኝነት ለተራራው ለወንዙ አይደለም፡፡ ተራራው እና ወንዙ ትርጉም የሚኖራቸው ለሰዎች እንዲሁም ለህዝብ ሲያገለግሉ ነው፡፡ ስለዚህ አገርን መውደድ ሰውን ወይም ህዝብን መውደድ ነው፡፡ አርስጣጣሊስ «Man is the measure of all things» ይላል፡፡ አዎን፤ ሰው የነገሮች ሁሉ መመዘኛ ነው፡፡ ተራራው እና ወንዙ ለሰው ወይም ለህዝብ ነው፡፡ የሁሉም ነገሮች ወይም ሥራዎች ፋይዳ መመዘኛው ለሰው የሚሰጠው ጥቅም ነው፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሰው በጣም የሚወዳቸው እና የሚኖርላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሥራ ትልቅ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርገው፤ ሰው ባጣ፣ የሚወዳቸውን እና የሚኖርላቸውን እሴቶች የሚያከብር ሥራ በመሆኑ ነው፡፡ ሰው የሚወዳቸውን ነገሮች እያጠፉ ለሰው መኖር አይቻልም፡፡ ለህዝብ ጥቅም እያሉ ህዝብን የመጨፍጨፍ ተግባር ውስጥ መዘፈቅ፤ በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት የለውም።

መሪዎች የሚወደዱት ወይም ሊወደዱ የሚገባቸው፤ ሰዎች በብዛት የሚሿቸውን ነገሮች የሚያስፈጽሙ ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ፍቅር ስሜት በእሴት ላይ ሊመሠረት የሚገባው ለዚህ ነው፡፡ እሴቶችን እየረገጥን ስንሄድ የአገር መውደድ ስሜት ከንቱ ይሆናል፡፡ በአገር ፍቅር ስም የሚፈጸሙ ነውሮችን የተመለከቱ አንዳንዶች «Patriotism is the virtue of the vicious» _ይላሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡

አገር በየዘመኑ የሚኖራት ትኩረት የተለያየ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም የአገር ፍቅር ስሜት መገለጫው በዚሁ አኳያ የተለያየ ይሆናል፡፡ የሚለያየው ይዘቱ ሳይሆን ቅርጹ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በምሳሌ እንፈትሸው፡፡ የጃፓን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ገጠመኝ የአገር ፍቅር ስሜት ምን እንደሚመስል ያሳየናል፡፡ የጃፓኖች ታሪክ በዚህ ረገድ ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል፡፡ አገራችን የዘመነ መሣፍንት አስተዳደር ውስጥ በነበረች ጊዜ፤ ጃፓንም ከእኛው ጋር ተመሳሳይ በሆነ አቋም እና ሥርዓት ውስጥ ትገኝ ነበር፡፡

እንደኛ ሺህ ዘመናት ባይቆዩም፤ ጃፓኖችም ለሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት ለሚሆን ጊዜ ከዓለም ተነጥለው ኖረዋል፡፡ ዓለም በጃፓን ውስጥ ምን ይሰራ እንደነበር አያውቅም፡፡ እርሷም በዓለም ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ሳትችል ብዙ ዘመን ኖረች፡፡ የረሳትን ዓለም ረስታ ተኝታ ዘለቀች፡፡

ከ250 ዓመታት በኋላ ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ መጀመሪያ አሜሪካ፣ ቀጥሎ ፈረንሳይ፣ ከዚያም እንግሊዞች በጦር ኃይል በሯን ሰብረው ገቡ፡፡ በዚያን ጊዜ ኃያላን የሆኑትን የአውሮፓ አገራት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል የሌላት ደካማ አገር መሆኗን ተረዱት፡፡ የጃፓኑ ንጉሥ ሙትሱሂቶ ገሩ የኃያላን አገራትን ጉልበት ተቋቁማ ለመኖር እንደማትችል አወቀ፡፡

ጃፓን እንደ ፈለገችው ኃያላኑን መንግሥታት ተከላክላ ድንበሯን ተሻግረው እንዳይገቡ ለማድረግ የማትችል ደካማ አገር መሆኗን አውቀው፤ ጃፓን የአውሮፓን ሥልጣኔ ተምራ ራሷን በጥበብ አጠናክራ ለመሄድ ካልቻለች፤ የቀድሞ አባቶቹ የፈሩት በሌሎች ኃያላን መዳፍ የመደፍጠጥ ዕጣ እንደሚገጥማት ተረዳ፡፡ ስለዚህ ሙትሱሂቶ ገሩ የአውሮፓን ሥልጣኔ እንድትቀበልና ትምህርት ቤቶች በሰፊው እንዲከፈቱ አዘዘ፡፡ በዚህ ወቅት የአገር ፍቅር የሚገለጸው የምዕራቡን ጥበብ ተግቶ በማጥናት እና በመማር ነበር፡፡

ስለዚህ ጃፓኖች «የሜይዢ ዘመን» የሚሉት ዘመን ተጀመረ፡፡ «ሜይዢ» ማለት ብርሃን ማለት ነው፡፡ ጃፓኖች ከዓለም ተነጥለው ሲኖሩ በዕውቀት እና በሥልጣኔ ወደ ኋላ ቀርተው እንደተጎዱ ስለተረዱ እጅግ ተቆጩ፡፡ ፊውዳላዊ በሆነ እና እንደኛው የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ በመሰለ የአስተዳደር ዘይቤ ሥር የቆየችው ጃፓን፤ ማዕከላዊ ኃይል በሌለው የተበታተነ እና የተዳከመ መንግሥት እጅ ቆይታለች፡፡ ህዝቡ ወደ ውጭ እንዳይወጣ እና የውጭ ሰዎችም ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጎ በኖሩበት ዘመን፤ ዓለም ጥሏቸው እንደሄደ አስተዋሉ፡፡ ይህን በጃፓን ህዝብ ዘንድ የነበረውን የቁጭት ስሜት የሚያንጸባርቅ አንድ አስተያየት በ1921 ዓ.ም (እኤአ) በታተመ አንድ የቶክዮ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር፡፡

…እኛ በቤታችን ቁጭ ብለን ቅኔ በመጻፍ እና የሻይ ግብዣ በማድረግ ጉልበታችንን ሁሉ ማባከን ግዴታ ሆኖብን ኖርን፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ ያገኘነው ትርፍ የሕዝባችን ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ መቸገር እና በዘር ምክንያት የተናቅን ሕዝብ ሆነን መታየት ብቻ ነው፡፡ ባለፈው የመሣፍንት አገዛዝ ዘመን ለተሰራው ስህተት ዛሬ እኛ ዕዳ ከፋዮች ሆነናል። የሚለው አስተያየት፤ የጃፓንን ህዝብ የቁጭት ስሜት ብቻ ሳይሆን አስተዋይ መንፈሱንም የሚገልጥ ነው፡፡

አገርን መውደድ፤ አገር በወቅቱ ወይም በዘመነ - ትውልዱ ምን እንደምትፈልግ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ አገርን የመውደድ ስሜት መነሻ ሊደረግ የሚገባው፤ በዘመኑ አገር ከምን ችግር ውስጥ እንደሆነች በመረዳት ያ የተጋረጠባት ችግር አፍኖ እንዳያስቀራት አስተውሎ ለመራመድ የሚያስችላትን እሴት አንጥሮ በማውጣት፤ ይህንንም እሴት አክብሮ በመያዝ አደጋዎችን እያስተዋሉ ለመጓዝ መጣጣር ነው፡፡ ለመሆኑ በእኛስ ዘንድ የአገር መውደድ ስሜት ምን መልክና ይዘት አለው? ምን ምን መገለጫዎችስ አሉት? በሚቀጥለው ክፍል ይዤ እመለሳለሁ። እስከዚያው ሰላም!

አሜን ተፈሪ  (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment