Wednesday, September 17, 2014

ኢትዮጵያዊ ከሆንክ - ቦንድ ግዛ! በ8100 ተወዳደር!

(Sep 17, 2014, ( አዲስ አበባ)--ለዘመናት እግር ተወርች አስሮን የኖረውን የአይቻልም መንፈስ የሰበረው የሀገራችን ኢኮኖሚ እድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ጉዳይ አንድ ህዝብ መሆናችንን በተጨባጭ ያረጋገጥንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብቻ አይደለም፤ በየዘርፉ የልማት ርብርብ የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ እንዲሳካ ኹነኛ አስተዋፅኦ እያደረግን በመሆናችንም ነው። የዚሁ ውጤት ባለቤትም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።

አርሶ እና አርብቶ አደሩ፣ ወጣቱ፣ ባለሃብቱ፣ ሰራተኛው፣ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልማት ለእኛም ይተርፋል ያሉ ጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች ወዘተ... ሳይቀሩ ባላቸው አቅም ድጋፍ እያደረጉ ነው። ትኩረታችን ልማት መሆኑንም እየመሰከሩ ነው።

ከሰሞኑም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገቢ በማሰባሰብ፣ ህዝቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሄራዊ አስተባባሪ ፅህፈት ቤት ባዘጋጀው የ8100 የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት ልዩ የሽልማት ፕሮግራም እየተሳተፈ ራሱንና ሀገሩን ለመለወጥ ፅኑ መሆኑን ዳግም በተግባር እያረጋገጠ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያኖች ሁለንተናዊ ተሳትፎ 35ነጥብ 8 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን በስፋት እየገለፁት ከመሆኑ ባሻገር በፕሮጀክቱ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው ግብጽን የመሰሉ ሀገራትም እውነታውን እየተረዱ የመጡ መስለዋል።

እንደ አልአህራምና አልመስሪ አልዩም ያሉ የግብፅ የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች ሳይቀሩ ይህንኑ በተጨባጭ ከማረጋገጥ ባለፈ «የወቅቱ ወግ» አቅጣጫውን ቀይሮ ግድቡ በስንት ወር እንዲሞላ ይደረግ ወደሚለው ማመዘናቸውን ልብ ይሏል። ኢትዮጵያውያን የአምስት ዓመቱ እቅዳቸውን ለማሳካት በልማት መጠመዳቸውንም አብራርተዋል።

በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ካሉ ፕሮጀክቶች የህዳሴው ግድብ ዋነኛ የመሆኑ ምስጢር አቅምን በእጅጉ የሚፈትን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ድህነትና ተረጂነትን አሜን ብሎ የተቀበለው ትውልድ የዘመናት ውርደቱን አሽቀንጥሮ በመጣል የህዳሴ ብርሃን እንዲያውጅ ታላቅ የመቻል አቅም ስለሚሆነውም ጭምር ነው።

የህዳሴው ግድብ፣ ትውልዱ ከአባቶቹ በተቀበለው ታሪክ ብቻ በመኖር ለመጪው ትውልድ የእሱ ያልሆነ ታሪክ ከማስተላለፍ እንዲድን፣ አሻራውንም እንዲያኖር ልዩ አጋጣሚ የፈጠረ ነው። ከዚህም አኳያ ለግድቡ መጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ የትውልድ መነቃቃት የሚያተርፍ፣ ታላቅ የልማት ርብርብ የሚጠይቅና በጠነከረ ተሳትፎ ሊመራ የሚገባው ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሄራዊ አስተባባሪ ፅህፈት ቤትም ህዝቡን በ8100 የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት ለሽልማት በማወዳደር፣ አንድም ለግድቡ ግንባታ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማነሳሳት፣ አንድም የሽልማቱ ተቋዳሽ እንዲሆን በማስቻል የዘየደው መላ በዚሁ ፍጥነት መቀጠል ይኖርበታል። በዚህ የተሳትፎ ሂደት ለሽልማቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች በተለይም ኩባንያዎች፣ አትሌቶችና ባለሃብቶች ግን በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው።

ይሁንና የ8100 ውድድሩ በውጭ ያለውን ዳያስፖራ የማያሳትፍ በመሆኑ ይኸው የህብረተሰብ ክፍል ከዚህ ቀደም በቦንድ ግዢው እንዳደረገው ተሳትፎ ሁሉ የሚኖርበትን ሀገር ህግና ስርዓት ባከበረ፣ የመፍትሄ አማራጭንም ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በሀገሩ ሁሉንተናዊ ልማት አሻራውን የሚያኖርበት ሌላ እድል የመፍጠር ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባው ነው።

በሌላ በኩል አንዳንድ ህገወጦች ለህዳሴው ግድብ የሚውል ገንዘብ እናሰባስባለን በሚል ከብሄራዊ አሰተባባሪ ፅህፈት ቤቱ እውቅና ውጪ ገንዘብ የማሰባሰብና ከታለመለት ዓላማ በተቃራኒ የማጭበርበር ተግባር ውስጥ እየገቡ እንዳሉ ይሰማል። እዚህ ላይ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቱ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ ስናሳስብ ሕዝቡም ቢሆን ትክክለኛውን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችልበትን አካሄድ ብቻ እንዲከተል መጠቆም እንወዳለን።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ  

No comments:

Post a Comment