Tuesday, March 11, 2014

በአባይ ጉዳይ የታዩ የየየባንዳነት ምልክቶች

(Mar 11, 2014, (አዲስ አበባ))--ከትልልቅ የእድገትና የጀብደኝነት ታሪካችን ጋር አብረው የበቀሉ ጥቂት የታሪክ ስንክሳሮች በውስጣችን ኖረው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያን ያሉ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል እየወደቁ እየተነሱ አገራቸው በወራሪ እጅ ከምትወድቅ ከምድሯ ወድቀው አፈሯን በደማቸው ለውሰው መቀበርን መርጠው አልፈዋል።

ቀደምት ወገኖች፣ የኢትዮጵያን የጣር ድምፅ ሳይሰሙ ቀድመዋት በጣር ጮኸው መውደቅን በመረጡባት በእዚያ ወሳኝ ወቅት የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ባስመሰከሩበት በእዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ልጆቿ ብቻ ሳይሆን ጋራና ሸንተረሮቿ የተሸፈኑበት ደንና ቁጥቋጦ ሳይቀር በመርዝ ጭስ በሚያወድም አረመኔ ፋሺስት በተቀጣበት በእዚያ የጭንቅ ወቅት ከእነዚያ ጀግና አርበኞች ተቃራኒ የቆሙ ጥቂት ኢትዮጵያዊ ባንዳዎች ነበሩ። ጀግኖቿን እየተከተሉ የሚያስመቱ፡፡ በእነርሱ የደም ዋጋ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳኩ፣ በደም ዋጋ መሬት የሚገዙ፣ የትግሉን ጊዜ ፍዳ ያደረጉ፣ የማይታመን አገራዊ ክህደት የፈጸሙና በወገን ውስጥ የተደበቁ የጭቃ ላይ እሾህ የሆኑ የማይቀረውን የአርበኞችን ድል ለማዘግየት ከፋሺስት ጋር አብረው የተገኙ።

ይህ ሁሉ መሰናክል ግን የሀገሬን አርበኞች ከድል አላስቀራቸውም፡፡ ምክንያቱም ጥሪው የኢትዮጵያ ነበርና፡፡ ወደ ትግል የጠራቸው ያልሞላ ኑሯቸው፣ የግዛት መሬት ማስፋፋት ወይም የግል ሀብት አይደለም፡፡ የጥሪው ድምፅ በጭንቅ ውስጥ ያለው የታፈነው የሚወዷት አገራቸው የኢትዮጵያ የጣር ጩኸት ነበርና ምንም ዓይነት ኃይል ከድል እንደማያስቆማቸው ያምኑ ነበርና ከእኔ ያልሆነ ከእነርሱ ነው ያለችዋን አገራቸውን ከኢትዮጵያ ያልሆነ ከፋሺስት ነው ብለው የተነሱት እነዚያን ጀግና አርበኞች ምንም ኃይል ከድል እንደማያስቀራቸው እሙን ሆነ፡፡

ዛሬስ፡-አባቶች ጠብቀው ያስረከቡን ያልተነካች አገር በዕድገትም ቀዳሚ በማድረግ ልጆቿ እንዳይራቡና እንዳይታረዙ፣ በመጠለያ እጦት እንዳይቸገሩ እና ልባቸው በፈቀደው በድሎት እንዲኖሩ አገራዊ ጥሪ የተቀበሉት የዚህ ዘመን ጀግና አርበኞች ቃሏን በማክበር ከድህነት ጋር የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በእዚህም በኢኮኖሚው ረገድ በስፋት ሊጠቀሱ የሚችሉ ድሎችን ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ ይህን ድል በተሻለ ፍጥነት ማስቀጠል ይችላል ተብሎ ትልቅ አገራዊ እምነት የተጣለበትን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በመላው የአገሪቱ ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ሲታቀድ አንስቶ ለእዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ብቸኛ ኃላፊነት የተጣለበት ሕዝብ ዛሬም እንደትናንት ጀግና የማታጣው ኢትዮጵያ ልጆቿ በድል እንደሚወጡት እርግጠኛ ሆናለች።

ይሁንና የህዳሴው ግድብ ላይ ስንክሳር እየፈጠረች የፕሮጀክቱን ሂደት ለማዘግየት የምትጣጣረውን ግብፅ (እሩጫዋ የማይሳካ እንደሆነ ብትረዳም) ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ ለመመላለጥ በሚያስብል ደረጃ እየኳተነች ነው። አሁን ላይ በአገሯ ስር የሰደደ የፖለቲካ ቀውስ እያተራመሳትና የኋልዮሽ እያስኬዳት ባለበት ሁኔታ እንኳን ከችግሩ መውጫ መንገድ ተስኗት ድራማዊ ክስተቶችን ለዓለም ማሳየት በጀመረችበት የውስጥ ውጥረቷን ማርገቢያ ስልትም አድርጋው እንደሆነ በውል ባይለይም በተለያየ ጊዜ የተዘበራረቀ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነች፡፡

ሲሻት በሠለጠነ አግባብ አለኝ የምትለውን ጉዳይ በድርድርና በውይይት አንስታ ለመፍታት ጤነኛ መስሎ የመታየት ጅምር ማሳየትና ያለበቂ ምክንያት መድረኩን ጥሎ በመውጣት ትጠቀሳለች። ስትፈልግ ደግሞ የማስፈራሪያ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት፣ አንዳንዴም ሌሎች አገሮች በእኛ ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ በማግባባት፣ ሲቀጥልም በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በመክሰስ ብቻ የቱን ይዛ የቱን መጣል እንዳለባት መለየት አቅቷት እንደውሃ ላይ ኩበት ስትዋልል ትታያለች፡፡

በሌላ በኩል በአስገራሚ ሁኔታ ግብፅን ተከትሎ አለንልሽ እያሉ የሕዝብንና የመንግሥትን የማይቀርና የሚጠበቅ ስኬት ለማዘግየት እርሷ በምትሰጣቸው ትራፊ የአገራቸውን የዕድገት ጥሪ ችላ ብለው ለግል ጥቅማቸውና ድሎት የሚተጉ «የእኛው» ሰዎችም ታይተዋል። አገራዊ ክብራቸውን እንደውሻ አዋርደው እና ተራና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን ታሳቢ በማድረግ ግብፅ የምታራምደውን አቋም መንግሥትንና ገዢውን ፓርቲ ማጥቂያ መንገድ ማድረግ እየሻቱ ነው። በእዚህ ረገድ አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ጋዜጠኞችን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። በእዚህም ግድቡን መገንባት የግብፅን ህልውና የሚጎዳና ከእዚህ ጋር በተያያዘ ለአገራችን የደህንነት ስጋት እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ፣ የግድቡ ግንባታ ከሚኖረው አጠቃላይ አገራዊ ፋይዳ ይልቅ የገዢውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ የተደረገ ፕሮጀክት እንደሆነ እና ሌሎች መሠረተ ቢስ ትችቶችን በመሰንዘር ተጠምደዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከግድቡ በፊት ሰብዓዊ መብት ይከበር በሚል ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በማገናኘት ጥቃቅን የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማጉላት አገሪቱ ውስጥ የከፋ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሰት እንዳለ በማስመሰል የሕዝቡን ተኩረት ከግድቡ አንስቶ በተራ አሉባልታ እንዲጠመድ ማድረግ፡፡ ሕዝቡ ግድቡን የራሱ አድርጎ በመውሰድ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ እንዲገነባ በመፍቀድ ድጋፉን ከዳር ዳር ባሳየበት በቦንድ ሰበብ ሕዝቡ ገንዘቡን እንደተነጠቀ አድርጎ ማቅረብ፡፡ በአንድ በኩል ከዓባይ በፊት ልናለማቸው የሚገቡ ሌሎች ወንዞችም መኖራቸውን ሲነግሩን በሌላ በኩል በሌሎች ወንዞች ላይ የምናከናውነውን ልማት እንደተለመደው ጥላሸት መቀባት ዓይነት መሞገቻዎች ተንፀባርቀዋል።

በእዚህ ረገድ ግልገል ጊቤ ሦስት ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ማንሳት ይቻላል፡፡ በእዚህም ግንባታው የአካባቢውን ህብረተሰብ ያፈናቅላል፣ የአካባቢ ብክለት ተፅዕኖ ያደርሳል እና ከጎረቤት ኬንያ ጋር ግጭት ውስጥ ይከተናል የሚሉ ዝባዝንኬዎችን ሲጠቅሱ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም በቂ ጥናት ተደርጎበትና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አልፎ በዓለማችን ታዋቂ ከሚባሉ የግንባታ ተቋራጮች የሚመደበው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ግንባታውን እያከናወነ ባለበት ግድቡ በቂ ጥናት አልተደረገበትም የሚለውን የግብፅን አቋም በማንጸባረቅ ተጠምደዋል፡፡ በባሰ ሁኔታም አቋማቸውን ሲገልጹም ከእዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከግብፅ ጋር ወደ ጦርነት ከገባን ተሸናፊዎች እንሆናለን፡፡ ምክንያቱም እኛ የተራብን ሕዝቦች ነን ብለው ከቀደምት ጀግኖች የወረስነውን ታሪክ ትተን ወኔ ቢስ ትውልድ እንዲፈጠር ይቀሰቅሳሉ፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው ነጥቦች ኢትዮጵያዊነታቸውን በመካድ ባንዳነታቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

እነዚህ ወገኖች ፋይዳ ቢስ አቋሞቻቸውን ለማስረጽ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ በተለይ በሶሻል ሚዲያ በስፋት ይገለገላሉ፡፡ በእዚህ ረገድ ፌስቡክ በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ መሠረተ ቢስ መረጃዎቻቸው የሚደርሰው የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ወጣቱ እንዲደናገርና እውነታውን እስኪረዳ ድረስ ጊዜውን በማባከን እንዲጠመድ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በፌስቡክ፣ በትዊተርና በተለያዩ ድረ-ገፆች የግብፅ አጋርነታቸውን ለሚያሳዩት የዘመኑ ባንዳዎች «ከእኔ ያልሆነ፤ ከእነርሱ ነው» ያለችውን የአገራችንን ጥሪ ተቀብለን ከኢትዮጵያ ያልሆነ ከጠላት ነው ብለናልና ከድርጊታችሁ ካልታቀባችሁ መዋረድ መብታችሁ መሆኑን ብናምንም በጭቃ ውስጥ የተደበቀ እሾህነታችሁ ግን ከድላችን እንዲያዘገየን አንፈቅድም፡፡

የኢትዮጵያ ልጆችና የእኛም ወገኖች ናችሁ ለማለት መቸገራችንም አልቀረም። ምክንያቱም ይህ ጥሪ የፖለቲካ ወይም የሥልጣን ወይም የግል ጀብደኝነት አይደለም፤ ጥሪው የአገር (የኢትዮጵያ) ነው፡፡ ይህ የአገራችን የዘመኑ ጥሪ ነው፡፡ ይህ ልጆቼን አጥግቡ የሚል ጥሪ የደረሰው የእዚህ ዘመን ጀግና ደግሞ በታሪክ የማያውቀውን ውርስ ከየትም አምጥቶ በአገር አይደራደርም፡፡ ሽንፈትንና መንበርከክንም አልወረስንምና ድሉም አይዘገይም፡፡ ለዚያ ዘመን ባንዳዎች ያልደረሱት ባዕድ አገሮችም ዛሬም አይደርሱላችሁም። ምክንያቱም ቁርጥ ቀን ሲመጣ ይህ የጥቁር አፈር ልጅ በአፈሯ እንደሚቀብራቸው ያውቃሉና፡፡

የዘንድሮውንም የአድዋ ድል በዓል ስናከብር በዋናነት ደግመን ደጋግመን ልናስታውስ የሚገባን እነዚያ ለዛሬዋ የድል ቀን ያበቁን ጀግኖች አርበኞች አባቶቻችን ለአገር ሉዓላዊነት የከፈሉትን መስዋትነት በመሆኑ እኛም እንደእነርሱ አገራችንን ከነ ሙሉ ክብሯ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ የተጣለብን መሆኑን ነው፡፡ ባንዳነት ይጥፋ!
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

2 comments:

Anonymous said...

Exactly Bandits shouldn't live in Ethiopian land. They should think critically .We Ethiopians shouldn't give any chance to our motherland enemies.We have to solve any an internal issues around the table.There is no joking with our Motherland Ethiopia. Our attitude should be the same concerned to Ethiopia. Because we get or lost we live in our country Ethiopia freely as we want performed not in other countries. So we have to keep the Agenda of development.

MULUNEH TSEGAYE(MEXICO ADDIS ABABA)

Anonymous said...

Those few Ethiopians working with our enemies are not our citizens because the do not need our country development.They need Ethiopian citizens to live with famine and thirst so know we real Ethiopians should have to unite to give them the price of their hands..GOD BLESS ETHIOPIA

Post a Comment