Thursday, March 13, 2014

የግብፅ መገናኛ ብዙሃንና ባለሥልጣናት የ «በሬ ወለደ» ዲስኩር

(Mar 13, 2014, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግልጽና የማያሻማ ነው፡፡ በመልካም ጉርብትና፣ በመከባበር፤ ለጋራ ጥቅም በጋራ መሥራት መርህ ታምናለች፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ሀገራት ወዳጅ ስትሆን የትኛውንም ሀገር በጠላትነት አታይም፤ አትፈር ጅምም፡፡ በጉርብትናም ያሉ ሀገሮች እድገት፣ ልማትና ሰላም ለራሷም፤ ለአካባቢውም ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘባለች፡፡

በቅርብም ሆነ በሩቅ ካሉ ሀገራት ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች አለመግባባቶች ቢከሰቱ በውይይት፣ በምክክር፤ በመግባባት፤ የጋራ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ መፍትሄ ያገኛል የሚል ጠንካራ እምነት አላት፡፡ ብሔራዊ ሕልውናዋንና ጥቅሟን የሚነካ ማንኛውንም ዓይነት አካሄድ አትቀበልም። አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ሙሉ ለሙሉ ታከብራለች፡፡ ይህም የሚሆነው የራሷን መሠረታዊ ብሔራዊ ጥቅም እስካልነካ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ለመገንባት ስትነሳ ከቀድሞ ተሞክሮዎችዋ ምን እንደሚፈጠር ስለምታውቅ የተማመነችው የራሷንና የሕዝቧን ታላቅ አቅም እንጂ የትኛውንም የውጭ መንግሥት ወይንም ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅት አይደለም፡፡ አሁንም የጠየቀችው ወይንም የምትጠይቀው ነገር የለም፡፡ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በራሷ አቅም እንደ ጀመረችው ሁሉ በሕዝቧ ታላቅ ርብርብ ለፍጻሜ ታበቃዋለች፡፡

የግድቡ ባለቤት ሕዝቡ በመሆኑ ሥራውን ለማሳካት ሌት ከቀን በመረባረብ ላይ ሲሆን፤ የገንዘብ መዋጮውም ዛሬም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ የሥራ እንቅስቃሴውም ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሕዝቡ ይቆጣጠራል፡፡ ለግድቡ መስሪያም ሆነ ማስጨረሻ ከበቂ በላይ የራሳችን አቅም አለን፤ ከውጭ ምንም ዓይነት የፋይናንስ ብድርም ሆነ ዕርዳታ አንፈልግም እያለ ነው፡፡ ይህንንም በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ ለማስቆም ሞክረው የነበሩት የግብፅ የፖለቲካ መሪዎች በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንዳላገኙ ሲያውቁት ካርቱም ላይ የነበረውን ውይይት አቋርጠው በመውጣት አዲስ ዓለም አቀፍ ፀረ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዲፕሎ ማሲያዊና የፖለቲካ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ጉዳዩን ለተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በማቅረብም የግድቡ ግንባታ እንዲቆም፤ የትኛውም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ለኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳያበድር ለማድረግ ሠፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

ይህን በማድረጋቸው ታላቅና ታሪካዊ ስህተት ተሳሳቱ፡፡ በግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማንንም የውጭ ዕርዳታ አይፈልግም፡፡ ሲቸገርና በድርቅ ሲመታ የነበረው እኮ የታላቁ የአባይ ወንዝ ብቸኛ ባለቤት ሆኖ ነው፡፡ ያ ታሪክና ጊዜ ተመልሶ እንዲ ደገም የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍፁም አይፈቅድም፡፡ ለእዚህ ነው የአባይን ግድብ ለመገንባት ቆርጦና ታጥቆ በእልህ የተነሳው፡፡ የግድቡን ግንባታ ለሰከንድ እንኳን ሊያስቆመው የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስቆም ወይንም ለማሰናከል የትኛውንም ዓይነት የሚታይም ሆነ የማይታይ ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆኑ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ግብፆች ሲናገሩ ከርመዋል፡፡

በቅርቡ ባረቀቁት አዲስ ሕገ መንግሥት ውስጥም (በአንቀፅ 44) የአባይ ውሃ ጉዳይ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ተደርጎ እንዲሰፍር አድርገዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ሕዝብ አስገር ሞታል፤ አስቆታልም፡፡ አባይ ወንዝ የሚመነጨው ከሲናይ በረሀ እኮ አይደለም፤ ከኢትዮጵያ መሬት ነው፡፡ እኛ ባለቤቶቹ ለዘመናት ሳንጠቀምበት ስንኖር ሌላው በሰው ሀብት ብቻውን እየከበረ፤ «ህዝቡ ድሀ ነው አባይን የመገንባት አቅም የለውም» እያለ የሚያላግጥበት ስላቅ ከእንግዲህ አይደገምም፤ ተረት ሆኗል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት እኛ ጠግበን እንደር እናንተ ደግሞ በችግር ውስጥ ኑሩ የሚል ዓይን አውጣነትን እያራመዱ ያሉ ይመስላል፡፡ «በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት » ማለት ይኸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ «አባይን በጋራ እንጠቀምበት ለሁላችንም ይበቃል» ነው ያለችው፡፡ ይሁንና አበው «የራሷ ድስት እያረረባት የሰው ታማስላለች» እንዳሉት የግብፅ አንዳንድ ፖለቲከኞችና ኤክስፐርቶችም በሀገራቸው ውስጥ በብጥብጥና በሁከት ተመሰቃቅሎ እንዲሁም አስተማማኝ የሰላም ዋስትናዋ ጠፍቶ እያለ፤ የአባይን ጉዳይ የውስጥ ችግር ማስተንፈሻና ሕዝቡንም ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያሰባስብልን ማዕከላዊ የስበት ነጥብ ነው ብለው በማመን በግድቡ ዙሪያ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይህን ተከትሎም የግብፅ ሚዲያዎች በአሁኑ ጊዜ ከአባይ ውሃና ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በማያያዝ ሠፊ የተዛባና እርስበርሱ የተጋጨ መረጃ በማሰራጨት ላይ ናቸው፡፡

ከወደ ግብፅ ብሔራዊ የአርበኝነት መዝሙሮች፣ ቀረርቶዎችና ሽለላዎች እጅግ በስፋት እየተደመጡ ነው፡፡ የግብፅ መከላከያ ምክር ቤት በሽግግሩ ፕሬዚዳንት አማካይነት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በአገር ውስጥና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብፅ ላይ ይፈጥራል በሚለው ተጽእኖ ዙሪያ ላይ መክሯል፤ ዘክሯል፡፡ በወቅቱም አደጋውን ለመቀነስ መደረግ አለባቸው ያላቸውን አማራጮች እንዳስቀመጠ የተለያዩ ምንጮች አስደምጠዋል፡፡ ምንም ተመከረ ምንም ተዘከረ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

ሲስሙዋት ቀርቶ ሲስቧት!

የአባይ ውሃ85 በመቶ አመንጪና ባለቤቷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ሳትጠቀምበት ግብፅ ደግሞ ስትጠቀምበት ለዘመናት ኖራለች፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እንዳይችሉ፤ ሰላምና መረጋጋት እንዲያጡ፤ ለዘመናት ከኖረው ሴራ ጀርባ ዋናዎቹ ተዋናዮች ግብፆች ነበሩ፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ ከእዚህ ስውር ድርጊታቸው ተቆጥበው አያውቁም። ለእዚህ ዋነኛ ምክንያታቸው ደግሞ የአባይ ወንዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ ከገደበችው የውሃው መጠን ይቀንሳል፤በእዚህም ምክንያት የምናገኘው ፈርጀ ብዙ ጥቅም ይቀርብናል በሚል ባዶ ስጋት፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለጋራ ጥቅም እንጂ ብቻዬን ልጠቀም አላለችም።

የግብፅ አንዳንድ ፖለቲከኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው፤ የዓሣ እርባታውና በምሥራቅ ግብፅ በመስኖ ውሃ የሚካሄዱት ፍራፍሬ ልማት በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ዶላር የሚያስገኘላቸው መሆኑና ሰው ሠራሽ ሐይቁም ከፍተኛ የቱሪስት ገቢ ማስገኘቱ፣ ትላልቅ እርሻዎቻቸውም መሠረት ያደረጉት የአባይን ውሃ በመሆኑ እነዚህ ሁሉ አባይ ከተገደበ ይደርቃሉ፤ ይጠወልጋሉ፤ ይከስማሉ የሚል ከንቱ ስጋት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተሰጣቸውን የውሃው አይቀነስም ማረጋገጫ በፍፁም ሊሰሙትም ሆነ ሊቀበሉም አልፈለጉም፡፡

የግብፅ የፖለቲካ መሪዎችና አንዳንድ ምሁራን እያራመዱት የሚገኘው ሃሳብ በራስ ወዳድነት የተሞላና «እኛ ብቻ እንጠቀም» የሚል ነው። ይህ ሃሳብ ደግሞ ግብፅና ሕዝቧ ደልቷቸውና ጠግበው ይዋሉ ይደሩ እንጂ ስለሌላው ሀገርና ሕዝብ አያገባንም፤ ቢፈልግም ይራብ፤ ይጠማ፤ ይለቅ፤ እኛና እኛ ብቻ እንኑር የሚል ነው፡፡ በእዚህ ዘመን ዋነኛዋ የውሃው ባለቤትና አመንጪ የሆነችው ኢትዮጵያና ሌሎቹም የተፋሰሱ ሀገሮች ይህንን የጋራ ጥቅም ሳይሆን ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ባሕርይ ሊቀበሉትም ሊያስተናግዱትም አይችሉም፣ አይፈልጉምም፡፡

ግብፅ የሦስተኛውን ዙር የሦስትዮሽ ውይይት ረግጣ ከወጣች ወዲህ በተጠናከረ መልኩ በሀገር ውስጥ ሚዲያዎቿ፤ ኤክስፐርቶችና ፖለቲከኞቿ በመጠቀም የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስቆም ሠፊ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ጀምራለች፡፡ ጉዳዩንም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት በመውሰድም በድምፅ ብልጫ ለማስወሰንም ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽነው ከአባይ ውሃ የ85 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ መብቷ ነው፡፡ይህን በአግባቡ መገንዘብ ደግሞ የግብፅ ፋንታ ነው።

ግብፅ በአባይ ውሃ ላይ አንድም የፈላጭ ቆራጭነት መብት የላትም፡፡ ስለሆነም ፈፅሞ ልታዝበት አትችልም፡፡ መብቷም አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በአዲስ መልክ ያካተተችው የአባይ ውሃ መብት የማይገሰስ መብት ነው የሚለውም ከተረት ተረት አይዘልም፡፡ ምክንያቱም የአባይ ውሃ የተፋሰሱ ሀገሮች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙበት ነው እንጂ ግብፅ ብቻ የምትወስንበት አይደለም። ከእዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የራሷን ሀብት ሳትጠቀምበት በዘላለማዊ ድህነት መኖር አለባት በአንፃሩ ደግሞ ግብፅ የራሷ ባልሆነ ሀብት ተጠቅማ በብልጽግና ትኖር ፤ ብሎ የሚደነግግ አንድም ሕግ የለም፤ አይኖርምም፡፡

አባይን በተመለከተ ግብጽ በአዲስ መልክ በሕገ መንግሥቷ ውስጥ ያካተተችበት ዓቢይ ጉዳይ የአባይ ውሃ ባለቤትነት የእኔ ነው ብላ ማስፈሯ ነው፡፡ የግብፅ ፓለቲከኞች የአባይ ውሃ ባለቤት ማን እንደሆነ እያወቁ አፍን ሞልቶ በድፍረት የእኛ ነው ማለታቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡

ሰሞኑን ከጀነራልነት ወደ መጨረሻው ወታደራዊ ማዕረግ ፊልድ ማርሻልነት የተሸጋገሩት አብዱል ፈታህ ሲሲ የአባይ ውሃ ሰላምና መረጋጋት የራቀውን የግብፅ ሕዝብ ወደ አንድ ማዕከላዊ አጀንዳ ያሰባስበዋል፤ ውጥረቱም ይቀንሳል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መቆም አለበት ብለው እጅግ ከፍተኛ ዘመቻ የከፈቱት፡፡

አጥቂውና ተከላካዩ መገናኛ ብዙሃን

ያለንበት ወቅት የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ላይ ዓይን ያወጣ የሐሰት ዘገባ በስፋት እያሰራጩበት ያለበት ነው፡፡ የሚገርመው ግን የእነርሱው የሆነው ናሽናል ዎተር ሪሶርስ ሲንተር (ብሔራዊ የውሃ ሀብት ማዕከል) ኢትየጵያ የጀመረችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንደማይቋረጥ ቢገልጸም እነርሱ እያወሩት ያለው የእዚህ ተቋራኒ ነው፡፡ እንዲሁም በተለይ አልአህራም እና አል ሞኒተር የተሰኙ የግብፅ ጋዜጦች የተለያዩ ግብፃውያን ኤክስፐርቶችን በማነጋገር የግድቡ ግንባታ ለግብፅ ታላቅ አደጋ መሆኑን ለሕዝቡ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ሕዝቡ ከእነርሱ ልቆና ጉዳዩን በሚገባ ተረድቶት የአገራቸው መንግሥት ወደ ሰላምና ድርድር እንዲያመራ ግፊት እያደረገ ባለበት በእዚህ ወቅት የመገናኛ ብዙሃኑ መቀላመድ ቀጥሏል።

የእኛ መገናኛብዙሃን የመንግሥትም ሬድዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ እንዲሁም የግሉ ፕሬስ ሕዝቡ እውነታውን እንዲያውቅ የማድረግ፤ በግብፅ መገናኛ ብዙሃን በኩል ያለውን እኩይ ሴራና ደባ የማጋለጥ ሥራ በተገቢው መንገድ አልሠሩም፡፡ የግሉ ፕሬስ ገበያ ለመሳብ ርዕስና የጦርነት ወሬ ይዞ በስሜታዊነት ከመጋለብ ርቆ የስከነና የበሰለ ሥራ ይዞ ለብሔራዊ ጥቅሙ የሀሳብ ክርክርና መፍትሄ ወደ ማመንጨት ገና አልሄደም፤ ሠርቷል ከተባለም ለእኛ ሳይሆን ለግብፆች ነው መሆን ያለበት፡፡ ምክንያቱም ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድ ተብሎ የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ጥሩ ዜና ይዘው የወጡበትን ዕትም ማስታወስ አይቻልም እና ነው።

በአጠቃላይ የግብፅ ፖለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙሀኑና አንዳንድ ምሁራን የአረቡንም ሆነ የሌላውን ዓለም እያካለሉ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ላይ የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎችን እያካሄዱ ነው። በእዚህ ጉዳይ ተገቢውን ምላሽና እውነታውን በማሳወቅ ረገድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅበትን ያህል አልሠራም፡፡ ግብፆች ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ልሳን የሚታተም ከአባይ ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንድም ጽሑፍ አያመልጣቸውም፡፡

አዲስ አበባ ያለው ፕሬስ አታሼ እያስተረጎመ ወደ ሀገሩ ይልካል፤ ሥራውም ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያና የሕዝቧ መልእክት ሃሳብና ግንዛቤ አቋም ምን እንደሚመስል ጨዋና ምክንያታዊ በሆነ ተጫባጭ መንገድ እንዲያውቁትና እንዲረዱት ማድረግ የሁላችንም የጋራ ግዴታ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስለ ግድቡ ያለውን እውነታ በግልጽ የግብፅ ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የግል ሚዲያዎችም ይህን አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣሉ ብያ አስባለሁ። ቸር እንሰንብት።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment