Saturday, February 01, 2014

«በሬ ሆይ ሳሩን…»

(Feb 01, (አዲስ አበባ))--በአገራችን ያለውን በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና በሕዝቦች እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ማህበራዊ መስተጋብር ልብ ብሎ ላጤነው ትልቅ ሀብት መሆኑን ማየት ይቻላል። አገራችን ያላትን የተፈጥሮና ታሪካዊ እስቶቿን ለዓለም በማስተዋወቅ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻልን ሁሉ እንዲህ ያሉ ለዓለም ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶቻችንን በማስተዋወቅ ረገድ ያደረግነው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለእዚህ አንድ አብነት ማንሳት ይቻላል።

ጎረቤታችን ኬንያ በተፈጥሮም ሆነ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦቿ ከአገራችን ጋር ልትወዳደር የማትችል ብትሆንም ከቱሪዝም ዘርፍ ግን ዳጎስ ያለ ገቢ ማግኘት እንደምትችል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን መረጃዎች መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ለእዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን ማቅረብ ቢቻልም ዋንኛው ነገር ኬንያውያን ከእኛ በተሻለ ሁኔታ አገራቸውን በአግባቡ ማስተዋወቅ በመቻላቸው ነው። ይህ ርዕሰ ጉዳይ የዛሬ መነሻዬ ባለመሆኑ በይደር ላቆየው።

መንግሥታት ቢለዋወጡም በአገራችን ሕዝቦች መካከል ያሉት መልካም ግንኙነቶች ሳይሸራረፉ ለዘመናት ዘልቀዋል። በአርሲ ዞን ባለች አንድ ቀበሌ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ቤተ አምልኮ የሌላቸው በመሆኑ ለቀብር ወይም ሌላ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም ሲሉ ከሁለት ሰዓት በላይ መጓዝ የግድ ይላቸው ነበር። የዚህች ቀበሌ ክርስቲያን ነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ለመስራት አቅም እንደሌላቸው የተረዱት ሙስሊም የቀበሌዋ ነዋሪዎች ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር በመመካከር ያላቸውን በማዋጣት ቤተ ክርስቲያን በቀበሌዋ እንዲቋቋም በማድረጋቸው፣ የቀበሌዋ ነዋሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን በቅርብ እንዲፈፅሙ አድርገዋቸዋል።

በኢትዮጵያ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በሃይማኖታዊ በዓሎች ሳይቀር በጋራ በመሰባሰብ ቤት ያፈራውን አብረው በመብላትና በመጠጣት በዓልን ያሳልፋሉ። በኢትዮጵያ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በመቻቻልና በፍቅር በጉርብትና የሚኖርበት አገር ብቻ ሳትሆን ቤተ እምነቶች ጭምር በአጥር ብቻ ተለያይተው ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን በሰላማዊ ሁኔታ የሚፈፅሙባት ብቸኛ አገር ናት፡፡

በአገራችን በተለያዩ እምነት ተከታይ ሕዝቦች መካከል የቆየና የጠነከረ መልካም ግንኙነት ይኑር እንጂ የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ስንመለከተው የቀድሞ መንግሥታት አንድን ሃይማኖት በማቅረብ ሌላውን በመግፋት የግል ፍላጎታቸውን ያራምዱ እንደነበር ህያው የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች የሚሰጡትን ምስክርነት ማድመጥ ይቻላል። የአጼዎቹ መንግሥታት ሃይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ ማድረጋቸው ንግሥናቸው ስዩመ እግዚአብሔር እንደሆነ ለማስመሰልና ሥልጣናቸውን ዘለዓለማዊ ለማድረግ እንዲያመቻቸው እንጂ እውነትም ለሃይማኖታቸው መርህ ተገዥ ሆነው ወይም የእነርሱን እምነት ተከታዮችን ለመጥቀም እንዳልሆነ ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል።

አፄ ኃይለሥላሴን ተከትሎ ሥልጣን የያዘው ሶሻሊስት ሥርዓት አራምዳለሁ የሚለው የደርግ አገዛዝም ሃይማኖትን በጅምላ በማጥፋት ሰዎች ሃይማኖት እንዳይኖራቸው የማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ብዙ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮች ወዘተ በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ ለሞት፣ ለወህኒ እንዲሁም ለስደትና ለእንግልት ተዳርገዋል። እንዲህ ዓይነቱና ሌሎች መረን የለቀቁ የደርግ በደሎችን በቃኝ ያለው ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ባቀጣጠለው ሕዝባዊ ትግል ግዙፍ ሠራዊትና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የደርግ ሥርዓት አሸቀንጥሮ ከሥልጣኑ አውርዶታል።

ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ መረን አልፎ የነበረውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ የመብት ጥሰቶች እልባት ለመስጠት በሕዝቦች ተሳትፎ የዳበረ ሕገ-መንግሥት እንዲጸድቅ አድርጓል። ኅዳር 29/ 1987 ዓ.ም የጸደቀው የአገራችን ሕገ-መንግሥት የሃይ ማኖትንና የብሔር ጥያቄዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ እንዲያገኙ አድርጓል። ሕገ-መንግሥታችን ዜጎች የመረጡትን ሃይማኖት በነፃነት እንዲከተሉ ከማስቻሉም በላይ መንግሥት በሃይማኖት፣ በተመሳሳይ ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ግልጽ ወሰን አስምሯል።

ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ በሚካሄድ የሃይማኖት ኮንፈረንስ ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ የሰማሁት ንግግር እጅግ በጣም ስለሳበኝ እስኪ ለእናንተም ላካፍላችሁ «በቀድሞው ወቅት ማለትም በአፄዎቹ መንግሥታት በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ የሃይማኖት መቻቻል ሳይሆን መቻል ነበር። አሁን ግን ነገሮች ተቀይረው በአገራችን በሃይማኖቶች መካከል መቻል ሳይሆን መቻቻል ሰፍኗል»ሲሉ ተናግረው ነበር። እውነት ነው ዛሬ በኢትዮጵያ በሃይማኖቶች መካከል መቻቻል ሰፍኗል።

አንዳንድ ሰዎች መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ በተለየ መልኩ በመረዳት መንግሥት የሚያደርጋቸውን የሕገ-መንግሥት ማስከበር አካሄዶችን እንደ ጣልቃገብንት ሲመለከቱት ይታያል። በሕገ-መንግሥ-ታችን መንግሥት በሃይማኖት፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ፤ በተመሳሳይ የሃይማኖት ተከታዮች ወይም በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ግጭት ወይ ያለመግባባት ሲከሰት መንግሥት ይህ ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ በመሆኑ አያገባኝም በሚል ስሜት እጁን አጣጥፎ ይመለከታል ማለት አይደለም፡፡

በየትኛውም ዓለም መንግሥት ሕገ-መንግሥት የማስከበር ግዴታ አለበት። ይህን ማድረግ የማይችል መንግሥት በሕዝቦች ተቀባይነት ስለማይኖረው እንደመንግሥት ሊቀጥል አይችልም። በሃይማኖቶች መካከል ያለመግባባት ሲከሰት ሁኔታዎችን የማብረድና ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነት የሚወድቀውም በመንግሥት ላይ ነው። እንዲሁም መንግሥት በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልን የሚሸረሽሩ ነገሮች ሲከሰቱ አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት ቀድሞ የመከላከልና በድርጊቱ ተካፋይ የሆኑትን ቡድኖችና ግለሰቦች ከተሳሳተ አካሄዳቸው እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነትም አለበት። የሕግ የበላይነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ማናቸውም ድርጊቶች ከተከሰቱ በኋላ ለማጥፋት ከመንደፋደፍ ይልቅ የጥፋት መንገዶችን ቀድሞ መዝጋት ብልህነት ይመስለኛል፡፡ አገራችን በተለያየ ጊዜ የአሸባሪዎችን ገፈት ቀምሳለች። ስለዚህ ችግር ከመድረሱ በፊት መንግሥትና ሕዝብ በጋራ በመሆን የአክራሪዎችን አካሄድ በአትኩሮት መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። አበው ሲተርቱ «ሳይቃጠል በቅጠል» ይሉ የለ።

የአክራሪዎች መሰሪ አካሄድ የሚጀምረው የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች በመከፋፈልና በመለያየት እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ ነው፡፡ አክራሪዎች ራሳቸው በሚከተሉት ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ምዕመናንን መከፋፈል እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች በሃይማኖት መሪዎች ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ሰፊና የተለያዩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን መንዛት ቅድሚያ ሥራቸው ነው፡፡ አክራሪዎች በእዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ምዕመኑ በመንግሥት ተቋማት በተለይ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ የመንግሥት ተቋማት መካከል በዋናነት በአክራሪዎች ዘመቻ የሚከፈትባቸው የፍትህና የፖሊስ ተቋማት ናቸው።

አክራሪው ኃይል ያልተደረጉና ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን በመፍጠር ወይም ትንንሽ ነገሮችን ከመጠን በላይ በማጎን በመንግሥትና በኅብረተሰቡ መካከል መቃቃርና ያለመተማመን ለመፍጠር ሲሯሯጥ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ የፌዴራል ፖሊሶች ጭንብል በመልበስ ሙስሊሞች ቤት በምሽት በመግባት ንብረት ዘረፉ፣ ሴቶችን ደፈሩ ... ወዘተ የሚሉ የፈጠራ ክሶችን በመደርደር ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመንግሥት መዋቅር ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ የፈጠራ ክሶችን ያለመታከት ሲሰሩ ነበር። ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ተራ ውንጀላዎችን አክራሪው ኃይልና አጋር የሆኑት አንዳንድ ወገኖች የተቻላቸውን ያህል የፈጠራ ወሬያቸውን ሲያነፍሱ ቢከርሙም ተቀባይ ሊያገኙ አልቻሉም።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት አክራሪዎች፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ስለ መቻቻልና መከባበር የሚሰብኩ ለዘብተኛ የሃይማኖቱ ተከታዮችን የማንቋሸሽና የማጥላላት ዘመቻ መክፈት እንዲሁም በሃይማኖት መሪዎቻቸውና በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የስም የማጥፋት ዘመቻን በመክፈት በኅብረተሰቡ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ሰፊ ዘመቻ ይከፍታሉ። ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻቸው የሰመረ ካልመሰላቸው የኃይል እርምጃ እስከመውሰድ ይደርሳሉ። ለእዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት በደሴው የሃይማኖት አባት በሼህ ይማም ኑር ላይ የተደረገው ግድያ ነው። አክራሪዎች ሁሌም በራሳቸው የማይቆሙ በመሆናቸው በሃሳብ ትግል የሚሞግታቸውን አይወዱም።

ባለፈው ዓመት ራሳቸውን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ እያሉ የሚጠሩት ቡድኖችን መንግሥት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናቸው በሚል በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ፍርድ ቤት በአቀረበበት ወቅት አክራሪው ኃይል የፍትህ ሥርዓቱን ክፉኛ ሲተች እንደነበር ይታወሳል። «የፍትህ ሥርዓቱ ነፃ አይደለም፣ መንግሥት ይጠቀምበታል፣ ካንጋሮ ኮርት ነው ወዘተ» እያሉ የማጣጣል ዘመቻ ሲከፍቱበት የነበረው ፍርድ-ቤት፤ ዛሬ አቃቤ-ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ በተገቢው ሁኔታ መርምሮ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች ነፃነታቸውን አረጋግጦላቸዋል። ፍትህ ማለት ይህ ነው። ዛሬስ የሽብርተኞች አቀንቃኝ የሆነው «ድምፃችን ይሰማዎች» ምን ትሉ ይሆን?

ሌላው አክራሪዎች እቅዳቸውን ለማስፈፀም እንዲያመቻቸው በአገራችን አክራሪነትና አሸባሪነት የለም «መንግሥት የፈጠረው ነገር እንጂ በኢትዮጵያ አክራሪነትና አሸበሪነት የለም፣ ወይም ሊኖርም አይችልም» በማለት ሰፊ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ኅብረተሰቡን ለማደናገር ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ አክራሪነት የሚወልደው አሸባሪነት በህቡ የሚፈፀም እጅግ በረቀቀ መንገድ ወንጀል የሚገመድበት ብዙውን ጊዜ የሩቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ያለው አካሄድ እንጂ እንደተራ ወንጀል በቀላሉ የሚፈጸም እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በአገራችን በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በምርጫ የሕዝብን ቀልብ መሳብ ሲሳናቸው ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በማይገባ መንገድ ወደ ቋመጡለት የሥልጣን ማማ የሚያደርሳቸው እየመሰላቸው የሃይማኖት ጉዳይን ከፖለቲካ ጋር ሲደበላልቁት ይታያሉ። የእነዚህ ፓርቲ አመራሮች «የአክራሪዎችን ድርጊት አይዟችሁ ትግላችሁ አግባብ ነው፣ እንረዳዳ በርቱ ተጠናከሩ» በማለት በየሚዲያው በሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለምልልሶች የአክራሪዎችን አካሄድ ሲያወድሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

የእነዚህ ፓርቲ አመራሮች በእንዲህ ያለ ያልተገባ መንገድ የቋመጡለትን ስልጣን ቢያገኙት እንኳን ስልጣናቸውን ሳያጣጥሙት በአሸባሪዎች ጎርፍ ተጠራርገው እንደሚጠፉ የተገነዘቡት አይመስሉም። «የጠላቴ ጠላት...» በሚለው የተሳሳተ ብሂል አገርንና ሕዝብን ሊጎዳ የሚችል ድርጊት ውስጥ መዘፈቅ ተገቢ አካሄድ አይመስለኝም። «በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን … » እንደሚባለው መሆንም ይመጣልና መጠንቀቅ ተገቢ ይመስለኛል። ለሁሉም የአሸባሪነት አደጋ የመላው የሀገራችን ሕዝቦች አደጋ ነውና የፖለቲካ ኃይሎች የግል የመንግሥት ሳይባል የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና መላው ዜጋ ሊወጉት ግድ ይላል። ሰላም!
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ 

2 comments:

Anonymous said...

Terrorists are terrorist.They make joke by human being blood & they worn the jacket of Devil. They have not care about their country,because they have not any pure mind.Their aim is so complex. They do not know which one is their enemy or friend. They got happiness by killing honorable human being.So We Ethiopians must have condemn seriously their activities.Peace is more than every thing.

Muluneh Tsegaye
(A/Inspector)
Addis Ababa(Mexico)

Anonymous said...

Extremism is an individual disease which transmitted by who have the owner of an ugly & the most worst mind.The extremists attitude so narrow.They have not any work with out doing to satisfy their interest.They are the family of rent seekers. They lost their time by performing not useful activities for their mother land. They are the messenger of who think by their money. They have not permanent stand, So We Ethiopians must have resisted the extremists strongly,because We loved & we have obligation to safe guard our mother land from this kind of bad disease.

Muluneh Tsegaye (Ass/Inspector)
Addis Ababa (Mexico)

Post a Comment