Saturday, February 01, 2014

የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ማተኮር ቀጣይ የቤት ሥራቸው ነው

(Feb 01, (አዲስ አበባ))--የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች በእናቶችና ህፃናት ጤና እና በኤች.አይ. ቪ/ ኤድስ መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ። በኤች .አይ.ቪ ላይ የሚሰራው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ማህበር ለድህረ 2015 ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የጋራ መግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ።

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፤ (Credit Ethiopian press)


ማህበሩ 13 ኛውን መደበኛ ጉባኤ « አንድም ህፃን ከኤች.አይ.ቪ /ኤድስ ጋር እንዳይወለድ» በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በቀድሞው የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደበት ወቅት ፤የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ እንደገለፁት፤ የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ማህበር በእናቶችና ህፃናት ጤና እንዲሁም በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ላይ በትኩረት በመሥራት የሚፈለገውን ልማት ለማምጣት የሚያስችል ሥራ ማከናወን ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል።

ማህበሩ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና በእናቶችና ህፃናት ሞት ላይ ጠንክሮ መሥራቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያመለከቱት ወይዘሮ ሮማን፤ ለዚህም የሚመለከተው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሊያበረክት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ በሚከሰቱ ማናቸውም ግጭቶች ቀዳሚ ተጋላጮች ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን አስታውሰው፤ ችግር እንዳይከሰትም ሆነ በሚከሰትበት ወቅት የሴቶችና ህፃናት ተጎጂነት ለመቀነስ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ነው። ለአብነትም የኤች.አይ.ቪ / ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ እንዲሁም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራት አከናውናለች። በቀጣይ አልፎ አልፎ ችግሩ በሚታይባቸው አካባቢዎችም በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

የማህበሩ ሊቀመንበርና የቻድ ቀዳማዊት እመቤት ሂንዳ ዴቢ ኢትኖ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ሙስጠፋ ሲኪዲ ካሎኮ ጋር የመግባቢያ ሠነድ በተፈራረሙበት ወቅት እንደገለፁት፤ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ የአፍሪካን አምራች ኃይል እየጎዳ ነው። ይህን ችግር ለመፍታትና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት መሥራት ይገባል። የዕለቱ ስምምነትም ማህበሩ ለሚያከናውነው ተግባር የገንዘብ፣ የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን የሚያስገኝ ነው። ሊቀመንበሯ በዘርፉ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማነት በተለይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ዋና ተግባሩ ሊሆን ይገባል። በወባ በሽታ ላይም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዶክተር ሙስጠፋ ሲኪዲ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ መሥራት በኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቁን ተግባር ማከናወን ነው። ለዚህም በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ላይ ከሚከናወኑ ተግባራት ባሻገር የእናቶችና ህፃናት ሞትን መቀነስና በአህጉሪቷ ሰላም ለማስፈን እየተከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

እንደ ዶክተር ሲኪዲ ገለፃ፤ በተለይም ጉባኤው በመሪ ሀሳብነት ይዞ የተነሳውን ፅንሰ ሀሳብ ከግብ ለማድረስ የመሪዎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። የዕለቱ ስምምነትም ይህንን የሚያሳይና ህብረቱ ለማህበሩ ያለውን አጋርነት የሚገልፅ ነው።

በአህጉሪቷ የሚታየውን ያለዕድሜ ጋብቻ አጥብቀው ያወገዙት ዶክተር ሲኪዲ ፤ ይህም ተግባር በህፃናቱ ሥነ ልቦና፣ ጤና እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዕለቱ ጉባኤ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment