Thursday, November 21, 2013

ምንስ ቢሆን ያጎረሰን ጣት እንዴት ይነክሷል?

(Nov 20, 2013, (አዲስ አበባ))--ሰሞኑን በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ቁጣን የቀሰቀሰ ዜና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገር ተሰማ፡፡ ሕጋዊነትን ካልተከተለ ስደት ጋር ተያይዞ በሳውዲ አረቢያ በኩል የተላለፈው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ ኢትዮጵያውያንን በኃይል የማስወጣት እርምጃ ተጀመረ፡፡ ይሁንና እርምጃው ፍትሐዊነት የተሞላበት ባለመሆኑ የዜጎችን ክቡር ሕይወት እስከመንጠቅ ደረሰ፡፡ ይህ ዜና ከተሰማ ጊዜ አንስቶም በርካታ ኢትዮጵያዊ በተለይም በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ቁጣውን ማስተጋባት ጀመረ፡፡ የድርጊቱን አግባብ አለመሆን በበርካታ መንገዶች ሲያንፀባርቅ ቆይቷል፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ አፅኖት ሰጥቶ ይከታተል ነበር፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት በጠበቀ መልኩ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሳውዲአረቢያ አምባሳደርን ጠርቶ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መጠየቁም ለእዚህ ነበር፡፡ ከማብራሪያው በኋላ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ በዚያች አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰላም ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሥራ ተጀመረ፡፡ ምንም እንኳን የዜጎቻቸው ጉዳይ ያስጨነቃቸው ኢትዮጵያውን ቁጣ ከፍተኛ ቢሆንም መንግሥት ጉዳዩን በሠለጠነ መንገድ ለማስኬድ የተጠቀመበት ስልት ተደንቋል፡፡

በኢትዮጵያና በሌሎች ዜጎች ላይ የደረሰው ድብደባ፣ ሞት እና እንግልት በጣም ያሳዝናል፡፡ ሳውዲ ከእዚህ በፊት ካላቸው ልምድ አንፃር ብዙም አይገርምም፡፡ ይሄ ጉዳይ ሁል ጊዜ የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ነገር አስቀድመው ማስጠንቀቂያና በቂ ጊዜ መስጠታቸው ነው - ሦስት ወር - ተጨማሪ አራት ወር - ጠቅላላ ሰባት ወር፡፡ የሳውዲ መንግሥት በሰባት ወር ውስጥ ሕጋዊ የሥራና የመኖሪያ ፍቃድ አውጡ ከእዚያ በኋላ ያለ ሕጋዊ ዶክመንት እዚህ አገር መቆየት ክልክል ነው ብሎ አሳውቋል፡፡ ከእዚያ በኋላ ሊመጣ የሚችል ነገር ማወቁ እዚያ አገር ላሉ ወገኖች ቀላል ይመስለኛል፡፡ በሰው አገር ሲኖር የአገሪቱ ሕግ ምንም ይሁን ምን አክብረህ መኖር የግድ ነው - የሳውዲም ቢሆን፡፡

እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን ይሄ ነገር ኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሕጋዊ ዶክመንት የሌለው ሰው መሆኑን ነው፡፡ ለምን ታዲያ ችግሩ አሁን ኢትዮጵያውያን ላይ በረታ? - ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሌላ አገር ዜጎች ከቀነ-ገደቡ አስቀድመው ስለወጡ ነው፡፡ በሰባት ወሩ የምህረት ጊዜ በአሥር ሺዎች የሚቁጠሩ ኢትዮጵያውያን ወረቀታቸውን አግኝተዋል፡፡ ሆኖም ግን በቂ መረጃ ካለማግኘት፣ ሌላ የምህረት አዋጅ ይኖራል ብለው በማሰብ፣ ተደብቀን እንደ ድሮው መሥራት እንችላለን ብለው በማሰብ፣ ለአጭር ጊዜ ብቻ የመቆየት ሃሳብ ያላቸው፣ እና በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች ብዙ ዜጎች ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም አላደረገም እያሉ ለሚናገሩ፡ - ምን ዓይነት እርምጃ እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ እነዚህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ የሳውዲ ግዛት ይኖራሉ - ሳውዲ ያለው ኤምባሲው አባላት ግን ኢትዮጵያዊ ባለበት በያንዳንዱ ቦታ መገኘት እና ከጥቃት መታደግ አይች ሉም፡፡መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ ከፍተኛ ልዑክ ወደ ቦታው ልኳል፡፡ ሌላ ማድረግ የሚጠበቅበትም እያደረገ ነው፡፡ ከእዚህ በላይ ከመንግሥት አይጠበቅም፡፡ ምናልባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መወቀስ ካለበት በእነዛ ሰባት ወራት ወረቀታቸውን ማደስ ፈልገው በኤምባሲው አገልግሎት መጓተት ምክንያት የሥራና የመኖሪያ ፍቃድ ሳያገኙ የቀሩ ዜጎች ካሉ ብቻ ነው፡፡ መመለስ አለባቸው ከተባሉ ዜጎች ከአስር እጥፍ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በዛች አገር በሕጋዊ መንገድ እየሠሩና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ነው።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያ ባስተናገደችው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ምጣኔ ጉባዔ ላይ ከርዕሰ ጉዳዩ ወጣ ብለው ጠንካራ ንግግር ማድረጋቸውም ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ይበልጥ የሚያጎላ ነው፡፡ በንግግራቸው ላይ ትኩረት ከሰጡት ጉዳይ መካከል ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ መሰል ጉዳዮችን ለማስተናገድ ብትገደድም በአንድ ወቅት የሳውዲ አረቢያን ስደተኞች በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማስተናገዷን ያስታውሳል፡፡ የዶክተር ቴዎድሮስ ሙሉ ንግግር እንደሚ ከተለው ይቀርባል፡፡

«እንደሚታወቀው ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም፡፡ እነርሱ ሕገወጥ የሚሏቸው የሌሎች አገራት ዜጎችም እየተመለሱ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በተፈጠረው ግጭት በኢትዮጵያውያን በኩል ሦስት ዜጎች መሞታቸው ታውቋል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በመጠለያ ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን በተረጋጋ መልኩ ለማስኬድ በእኛ በኩል የቻልነውን ያህል እየጣርን ነው፡፡ ሳውዲ አረቢያ «ሕገወጦች» ብትላቸው እነርሱም የሚመለሱበት ሃገር አላቸው፡፡

ሂደቱን በመልካም መንገድ የሚያከናውነው ግብረ ኃይል ሥራውን በሚገባ ጀምሯል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው አስገብተናል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ ቀሪዎቹን ለመቀበል መዘጋጀታችንንም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

በቤተሰብ ዕቅድ ጉባዔ ላይ እንዳልነው እኛ ለልጃገረዶች እና ሴቶች ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከመጠለያ በማስጠራት በስልክ ሳናግራቸው ዕርዳታ ፍለጋ የሚያለቅሱ ሴቶች ነበሩ፡፡ ከእዚህ በላይ የባሰ ነገር የለም፡፡

በጣም አዝኛለሁ፡፡ እጅግ ተከፍቻለሁ፡፡ ለዚያም ነው እዚህ መጥቼ ዶክተር ከሰተን ይቅርታ የጠየቅኩት፡፡ ምክንያቱም የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት ጥረት ከጀመርን ሰዓታት አልፈዋል፡፡ እኛ ሕጋዊ ያልሆኑ ዜጎችን መመለስ ብንፈልግ እንኳን ዓለም አቀፉ አሠራር የሚፈልገውን አካሄድ ተከትለን በአግባቡ እናደርገዋለን፡፡ ምክንያቱም ይሄ የጦር ወቅት አይደለምና፡፡ አገራት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ምናልባት በእዚህ መልኩ ዜጎችን ማስወጣት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሰላም ወቅት እንዲህ አይሆንም፡፡ በእዚህ ዘመን ሰዎች ይሄን ሊረዱ ይችላሉ፡፡

ቀደም ብዬ እንዳልኩት ዜጎቻችንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የተቀናጀ ሥራ ጀምረናል፡፡ ምክንያቱም ዜጎቻችንን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ በእዚህ ጉዳይ በመጀመሬ ይቅርታ እጠይቃለው፡፡ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ስለረበሸኝ ነው።

ኢትዮጵያ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የረጅም እና አጭር ጊዜ አቅጣጫ አስቀምጣለች፡፡ ለእዚህም ብዙ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ምክንያቱም ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በጉዳዩ ዙሪያ የሚታዩ የመዋቅር ችግሮች መንስኤዎች መታወቅ አለባቸው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሁለት አኀዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ከጨለማው ባሻገር ብርሃን አለ፡፡ እናውቃለን! ድህነትን እንደምናስወግድ እርግጠኞች ነን፡፡ ወደ ብርሃኑ አቅጣጫ እየተጓዝን ቢሆንም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድነት አሁንም እናምናለን፡፡ ነገር ግን ይሄ ይመጣል ብለን ገምተን አናውቅም፡፡

ለማያውቁት ሁሉ አንድ ነገር ለማጋራት እወዳለሁ፡፡ ነብዩ ሞሐመድ የእስልምና ሃይማኖትን ሲያስፋፉ ተቃውሞ በገጠማቸው ጊዜ ተከታዮቻቸውን (ሰሃባዎች) ወደ ኢትዮጵያ ልከው ነበር፡፡ ታሪክ እንደሚናገረው እነርሱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መልካም አቀባበልና ጥበቃ የተደረገላቸው የመጀመሪያ ስደተኞች ነበሩ፡፡ እስከ ሕይወታቸውም መጨረሻ በሰላም መኖር የቻሉት በኢትዮጵያ ነው፡፡ የመቃብር ቦታቸውም እስከ አሁን ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ይገኛል፡፡ ከፈለጋችሁ ሄዳችሁ መመልከት ትችላላችሁ፡፡

እኔ ራሴ የጎበኘሁት ቦታ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ስደተኞቹን በአግባቡ አስተናግደዋቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም የነብዩ ሞሃመድ እስልምና ማስፋፋት የተቃወሙትና ለተከታዮቻቸ ስደት መንስኤ የሆኑት የወቅቱ መሪዎች በኢትዮጵያ በስደት ላይ የነበሩትን የነብዩ ተከታዮች ተላልፈው አንዲሰጧቸው እንዲሁም ወደ ሃገራቸው በግዳጅ እንዲመለሱ የወቅቱን የኢትዮጵያ ንጉሥ ሲጠይቁ ንጉሡ ስደተኞቹን በግዳጅ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎባቸዋል።

እኔ እንደማስበው ይህ ለዓለም አቀፉ ትብብር ምልክት የሆነው ይሄ ታሪክ የተከሰተው ከ1400ዓመታት በፊት መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ታሪክ በደንብ ማስታወስ ይገባል፡፡ ድጋፍ ስታደርግ ምንጊዜም ዕርዳታ መፈለግ እንዳለ መታወስ አለበት፡፡ አንድ ቀን ድጋፍ ትፈልጋለህ፤ ምናልባትም ሌላ ጊዜ ዕርዳታ ሰጪ ትሆናለህ፡፡ እኛም ትናንት ዕርዳታ ሰጪ ነበርን፡፡ ምናልባትም አሁን ደግሞ የምንቀበልበት ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ የእዚህች ዓለም ትክክለኛ መገለጫው ይሄ ነው፡፡ ለእዚህም ነው ክንዳችንን ማስተባበር ያለብን፤ የተሻለች ዓለም ለመፍጠር፡፡ እርስ በእርስ መደጋገፍ መቼም ቢሆን ሊያስቸግረን አይገባም፡፡

የተሰማኝን ስሜት ሳጋራ ክብር ይሰማኛል፡፡ በጭራሽ ያልጠበቅነው ታሪክ አጋጥሞናል፡፡ ያለፉት አሥር ቀናት በሕይወቴ የማልረሳቸው አሳዛኝ ቀናት አሳልፌያለው፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ሰዎች አለም አቀፉን አሠራር እንደሚከተሉ አምናለሁ፡፡

የቀድሞና የአሁኑ የሥራ አጋሮቼ ምንም እንኳን በተፈጠረው ሁኔታ ባዝንም ሁሌም ከእናነት ጋር ነኝ። ነገር ግን ይህ ለእኛ ትምህርት ነው። በጣም ትልቅ ትምህርት፤ነገር ግን በቀጣይ የተሻለች ዓለም አንድትኖረን ተስፋ አደርጋለሁ። በጋራ ደግሞ ይህንን ማድረግ አንችላልን» በማለት ለጉባዔተኞቹ ገልፀዋል።

ሳውዲ ኣረቢያ ያለው የሥራ እና የኑሮ ሁኔታ ኣሰቃቂ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሕጋዊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሳውዲ ውስጥ ገብተው ይሠራሉ፡፡ የመንግሥት ኦፊሴላዊ ቁጥር የሚያመለክተው ባለፈው ዓመት ብቻ 76ሺ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ሥራ አግኝተው ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጉዘዋል፡፡ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ደግሞ ምን ያህል ሰዎች ሊሄዱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ መንግሥት ማድረግ ያለበት ዜጎች በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱና በሕጋዊ መንገድ እንዲሠሩ ማበረታታት እና የዜጎቹ የሥራ ሁኔታና አያያዝ እንዲስተካከል መሥራት (በጉዳዩ ላይ መንግሥት እየሠራ ነው - ላልተወሰነ ጊዜም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለሥራ መሄድ አግዷል) ነው።

ሳውዲ አረቢያ ያለው የሥራና የኑሮ ሁኔታ እያወቁ አሁንም እዚያ ሄደው ለመሥራት እየተሰለፉ ያሉት አማራጭ ስለሌላቸው ነው፡፡ ወይም ደግሞ አገር ውስጥ ካለው ዕድል የተሻለ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ለምን እኛ «ኩሩ» ሕዝቦች ሆነን ሳለ ዜጎች ወደዚያ ይሄዳሉ ብለን ማውገዝ የለብንም፡፡ ከአገሩ ወጥቶ መኖር የሚፈልግ ማንም ሰው የለም፡፡ ባዶ ኩሩነት እና ኩፈሳ እስከ ዛሬ ዳቦ ሊሆነን አልቻለም፡፡ ራሳችንን ችለን በአገራችን ኮርተን ለመኖርና ክብራችንን ለማስመለስ መጀመሪያ ከድህነት መውጣትና በኢኮኖሚ ጠንካራ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኮፐን ሃገን የአየር ንብረት ጉባዔ አፍሪካን ወክለው ሲደራደሩ ለምን በኃያላን መንግሥታት የቀረበውን የድርድር ሃሳብ ለምን ውድቅ ኣላደረጉትም ተብለው ሲተቹ – በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አቅም ሳይኖርህ በባዶ ኪስህ ከማንም ጋር ተደራድረህ እኮፈሳለሁ ብትል የምትጎዳው ራስህ ብቻ መሆንህን አብራርተው ነበር-አሁን የሆነው እንደዚያ ነው። ስለዚህ መሠረታዊ መፍትሔው ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ማፋጠን ነው።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment