Thursday, November 21, 2013

የአፍሪካና የዓረብ አገሮች ለስደተኞች ጉዳይ ትኩረት መስጠት አለባቸው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

(Nov 20, 2013, (አዲስ አበባ))-- «በአሁኑ ወቅት መንግስት በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በችግር ላይ ያሉትን ዜጎቹን ከመታደግ የበለጠ አጀንዳ የለውም» ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

አምባሳደር ዲና ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን የማስመጣቱ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል። እስከ ትናንት ድረስ ከ5ሺ 500 በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት ገብተዋል። ይህንን ስራ ለማጠናከር ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚደረገውን የአውሮፕላን በረራ መጨመሩን ገልፀው፤ «ቢያንስ በቀን ስድስት ጊዜ በረራ አለ» ብለዋል።

ዜጎቹን በፍጥነት ወደ አገር ቤት ለማስመለስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ግበረ ሃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ በዚህ ግብረ ሃይል ውስጥ የግብርና፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን፣ የጤና ጥበቃ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይና የትራንስፖርት ሚኒስቴሮች እንዲሁም የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መካተታቸውንም አመልክተዋል።

«የግብረ ሃይሉ ዋናው ተልዕኮ የሚመለሱትን ዜጎች ማስተናገድና ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው» ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ክልሎችም ለተመላሾች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት። በአጠቃላይ ከሃያ ሺ በላይ ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ዜጎችን የማስመለሱን ሂደት ለማሳካት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አገሪቷ አሰማርታለች። በአቡዳቢና በኳታር የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችም ይህንን ለመደገፍ ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም በጉዳዩ ዙርያ ከሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውንም ነው አምባሳደር ዲና ያስተወሱት።

«ኤንባሲዎችና ቆንስላዎች ለዜጎች ፈጥነው አይደርሱም፤ መንግስት ለዜጎቹ ብዙ አይቆረቆርም የሚል ትችት የሚያቀርቡ አካላት አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት» የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው አምባሳደር ዲና፤ መንግስት ለዜጎቹ ክብርና ደህንነት ይቆረቆራል። ዜጎቹን ለማስመለስ ወደ 50 ሚሊዮን ብር በመመደብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመረባረብ ላይ ይገኛል። ከሁለት ዓመት በፊት በዓረብ አገሮች በተከሰተው ሁኔታ ችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በፍጥነት በመመለስ ለዜጎቹ ተቆርቋሪነቱን በተግባር አሳይቷል። 
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ
Home 

No comments:

Post a Comment