Tuesday, October 08, 2013

« የናይጄሪያን ብሔራዊ ቡድን እናከብራለን »- ሳላህዲን በርጌቾና አበባው ቡጣቆ

(Oct 08, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሐል ተከላካይ ሳላህዲን ቤርጌቾ ጥቅምት ሦስት ቀን ለ 2014 ቱ የብራዚል ዓለም ዋንጫ በአዲስ አበባ ከናይጄሪያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ« ምርጥ ብቃታችንን ሜዳ ላይ ማሳየት ከቻልን የናይጄሪያን ብሔራዊ ቡድንን እናሸንፋለን » በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማሸነፍ አቅም እንዳለው የተናገረው ሳላህዲን ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡ ቡድኑ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ የሚያደርግ ሲሆን ፤ በጠዋቱ ፕሮግራም የታክቲክ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የቴክኒክ ልምምዶችን እየሰራ ነው ብሏል።

«ድሉን ኢትዮጵያውያን ይፈልጉታል ፣ ለእዚህም ጠንካራ ልምምድ በማድረግ ላይ እንገኛለን ፤ በሜዳችን ጥሩ ተጫውተን ድል ማስመዝገብ እንደምንችል እተማመናለሁ » በማለት ተከላካዩ በጨዋታው ዙሪያ ያለውን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥቷል፡፡

በሌላ ዜና የቅዱስ ጊዮርጊስና የዋሊያዎቹ የግራ ተመላላሽ ተጫዋች አበባው ቡጣቆ ከናይጄሪያ ጋር ያለውን ጨዋታ በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ ለመድረስ መጓጓቱን ተናግሯል፡፡አበባው ከአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ ጋር መጫወታቸው ምንም አዲስ ነገር እንደሌለው ገልጾ፤ እርሱና የቡድን ጓደኞቹ ለወሳኙ ጨዋታ በራስ የመተማመን ስሜትን ማጎልበት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

«አሁን ዋናው ትኩረታችን ለመጪው የናይጄሪያ ጨዋታ ነው ፤ የ 2013 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎች በመሆናቸው እናከብራቸዋለን። አሁን ናይጄሪያም እኛም ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ነው ዓላማችን፣ በእዚህ ላይ ታዲያ የቀደመ ታሪክ የሚጠቅም አይመስለኝም » በማለት ለሱፐር ስፖርት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

አበባው በተጨማሪ «ሁለታችንም ጨዋታውን በጣም እንፈልገዋለን። በእግር ኳስ የሚፈጠረው አይታወቅም። በቴክኒክና በታክቲክ በምንሰራው ልምምድ ደስተኛ ነኝ ፣ሁላችንም ለጨዋታው ጠንክረን እየሰራን ነው፤ እዚህ ደረጃ ይደርሳሉ ብሎ ግምት የሰጠን አልነበረም፣ነገር ግን በጠንካራ ሥራና በራስ መተማመን ከአስሩ ምርጥ የአፍሪካ ቡድኖች መካከል አንዱ ሆነናል» ብሏል። ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች እርሱም ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል፡፡

አበባው በጠንካራ የቅጣት መችነቱ ይታወቃል፡፡በተለይ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአዲስ አበባ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በቅጣት በመታት ኳስ ፓርከር በራሱ ላይ ግብ እንዲያስቆጥር ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment