Tuesday, September 10, 2013

ዋጋ የማይወጣለት የዋሊያዎቹ የአዲስ ዓመት ስጦታ

(Sept 10, 2013, (አዲስ አበባ))--እየመረረንም ቢሆን ልንውጠው ከጫፍ ደርሶን የነበረው ኃዘን በዋሊያዎቹ አልበገር ባይነት ተለውጦ መላውን ኢትዮጵያዊ በደስታ ሲያስጨፍር አመሸ።

በፌዴሬሽናችን ንዝህላልነትና ዝርክርክነት የተፈጠረው ስህተት እጅግ ውድ ዋጋ ሊያስከፍለንና ልንቀበለው ሁለት ቀናት ብቻ የቀሩትን አዲስ ዓመት ሊያጨልምብን ተቃርቦ ነበር። ለአገራቸው የማይከፍሉት ምንም ነገር እንደሌለና ውዱን ጉልበታቸውን በብራዛቪል ላፈሰሱት ለዋሊያዎቹ ምስጋና ይሁንና ድላችንንና ደስታችንን መልሰ ውልናል።

አዎ! ጨዋታው አስጨናቂ ነበር። ከጨዋታው በፊትም ብዙ ነገሮች ተብለዋል። የፊት መስመር ተሰላፊያችን የጌታነህ ከበደ መጎዳትም አስደንግጦን ነበር። ተጋጣሚያችን መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በሜዳችን ካስተናገድነው እጅጉን ተሽሎ ቀርቧል።

ወደ ዋናውና ከአፍሪካ አስር ብሔራዊ ቡድኖች በደርሶ መልስ ለሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታ ማሸነፍ ቀዳሚ ዓላማው ባደረገው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሳሊፍ ኬይታ በተባለው ተጫዋቹ አማካኝነት ባስቆጠረው ግብ መርቶን አስጨንቆናል።

ከዚያ በተጨማሪ የማለፍ እድል የነበረውና ከምድቡ በሁለተኛነት ዋሊያዎቹን ይከተል የነበረው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚውን ሁለት ለባዶ በመምራት እረፍት መውጣቱ ደግሞ የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ለዋሊያዎቹና አገር ቤት ሆነን ጨዋታውን ለተከታተልን ዜጎች በተስፋ መቁረጥና በተስፋ መካከል ሆነን እንድንከታተል አስገድደውን ነበር።

ምስጋና ለዋሊያዎቹና ለአሰልጣኞቹ ይሁንና ተጫዋቾቻችን ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት በፍጹም ወኔ በመሆኑ 48ኛው ደቂቃ ላይ የግብ አዳኙ ሳላዲን ሰኢድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፎ እኛንም ከጭንቀት አሳረፈን። ሳላዲን ኳስ እንዳያገኝ ሁለትና ሦስት ሆነው ይይዙት በነበሩት የመካከለኛው አፍሪካ ተከላካዮች ላይም የበላይነቱን አሳየ።

መላው ኢትዮጵያ በትናንትናው እለት ምን እንደሚጠብቅ ጠንቅቀው የሚያውቁት ተጫዋቾቻችን ወረራቸውን አጠናክረው በመቀጠል ከአስራ ሦስት ደቂቃዎች በኋላ ማለትም 61ኛው ደቂቃ ላይ በምንያህል ተሾመ አማካይነት ሁለተኛውንና ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳለፈችንን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፈው አስጨፈሩን፤ አስፈነደቁን፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የትናንትናውን ጨዋታ እንዲጠብቅ ያስገደደው ክስተት የተስተዋለው ምንያህል ተሾመ በተመለከታቸው ሁለት የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርዶች ምክንያት አንድ ጨዋታ ማረፍ ሲገባው ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ሦስት ነጥብ ተቀንሶብን መሆኑ ይታወሳል። ተጫዋቹ ራሱ ባስቆጠራት ግብ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ማጣሪያ ማለፍ መቻሉ ደግሞ ግጥምጥሞሹን የተለየ አድርጎታል።

ተጫዋቾቻን በሰላማዊው የስፖርት ሜዳ ላሳዩን ኢትዮጵያዊ ወኔና በአዲሱ ዓመት መባቻ ለሰጡን ዋጋ የማይወጣለት ስጦታ እናመሰግናቸዋለን።

«በደስታ ባሕር እንድንዋኝና አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2oo5 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ሱዳንን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆናችንን በማረጋገጥ የተለኮሰው የአገራችን የእግር ኳስ ችቦ እንደበራ እንዲቀጥል ያደረጋችሁ እናንት የዋሊያዎቹ አባላት አኩርታችሁናልና ክብር ይገባችኋል!»
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment